1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወባ በሽታ ስርጭት በመተከል ዞን

ዓርብ፣ ጥቅምት 1 2017

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ወባ በሽታ በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ። በዞኑ በተለይ ቡሌን እና ድባጤ በተባሉ ወረዳዎች ውስጥ በስፋት ስርጭቱ መኖሩን የጤና ጣቢያ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የወባ ትንኝ
የወባ ትንኝ ምስል James Gathany/AP/picture alliance

የወባ በሽታ ስርጭት በመተከል ዞን

This browser does not support the audio element.

ቡሌን ወረዳ ውስጥ በዚህ ሳምንት የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ዶቼ ቬለ ያነጋርናቸው ባለሙያዎችና ነዋሪዎች አመልክተዋል። በመስከረም ወር ብቻም በቡሌን ወረዳ 10 ሰዎች በወባ ምክንያት መሞታቸውን አንድ የህክምና ባለሙያ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። ከአጎራባች ክልሎች ጋር የሚያገናኙ የመጓጓዣ አገልግሎት መዘጋትም ለመድኃኒትና ዕቃ አቅርቦት እንቅፋት መሆኑን ከዚህ ቀደም የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጾ ነበር።

የወባ በሽታ ስርጭት በዚህ ዓመት በስፋት ከተስተዋለባቸው አካባቢዎች መካከል የመተከል ዞን አንዱ ሲሆን በዚህ ዞን ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ወባ መስፋፋቱ ተገልጿል። በመተከል ዞን ስር ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል አንዱ ቡሌን ወረዳ ውስጥ በዚህ ሳምንት የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የህክምና ባለሙያ ተናግረዋል። ከአንድ መቶ በላይ ሰዎችም በዚህ ሳምንት በአንድ ቀበሌ በወባ መያዛቸውን አመልክተዋል። በዚህ ክረምት ወባን ለመከላከል የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች አነስተኛ መሆን ለወባ በሽታ መስፋፋት አንዱ ምክንያት እንደሆነ ነው ባለሙያው የሚናገሩት። በወባ በሽታ አንድ የቤተሰባቸው አባል ሕይወት ማለፉን የነገሩን ሌላው ነዋሪ ደግሞ የወባ በሽታ ስርጭት በአካባቢው በዚህ መልኩ ተስፋፍቶው እንደማያውቅ በመጠቆም ትኩረት እንደሚሻ ተናግረዋል።

ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ከተማ ፎቶ ከማኅደር ምስል Negassa Dessakegen/DW

 በመተከል ዞን ድባጤ በተባለ ወረዳም በዚህ ዓመት ወባ በብዛት ሰዎችን ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን  ያነጋርናቸው አንድ ነዋሪ ገልጸዋል። ወባ በሽታን ለመከላከል ለነዋሪው የተሰጠው አጎበር ቁጥር በዚህ ዓመት ማነሱን የተናገሩት ነዋሪው በበወረዳው በርበር፣ ጋላሳ እና ጊጶ የሚባሉ ቦታዎች በክረምቱ በወባ በሽታ የሰው ሕይወት ማለፉንም አመልክተዋል። በዚህ አካባቢ ከዚህ ቀደም በሰላም እጦት ምክንያት ሥራ አቁመው የነበሩ የጤና ተቋማት ሥራ መጀመራቸው የተገለጸ ቢሆንም የወባ ስርጭት ግን መጨመሩና በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ አክለዋል።

በክልሉ መተከል ዞን በስፋት ተስውሏል የተባለውን የወባ ስርጭትን በተመለከተ ከክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ የመርሀ ግብር ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልሙኒየም አልበሽር ከዚህ ቀደም በሰጡን ማብራሪያ በክልሉ 22 ወረዳዎች ወባ በወረርሽኝ መልክ መስፋፋቱን አመልክተዋል። ከሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ሐምሌ ወር የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉንም የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

በቤኒሻንጉል ጉመዝ ጉሙዝ ክልል ሁሉም ወረዳዎች ውስጥ ወባ በስፋት መታየቱን የክልሉ መንግሥት ከዚህ ቀደም ይፋ አድርጓል። ከሰኔ 2016 ዓ.ም ወዲህ በክልሉ በ15ሺህ በላይ ሰዎች ላይ ወባ መገኘቱን የክልሉ ጤና ቢሮ መረጃ ገልጿል።  

ነጋሳ ደሳለኝ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW