1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወባ ወረርሽኝ ፈተና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል

ሰኞ፣ ሰኔ 17 2016

በኢትዮጵያ ካለው አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 75 በመቶ ያህሉ ለወባ በሽታ ሥርጭት አመቺ መሆኑ ይነገራል፡፡ አሁን ላይ በኦሮሚያ ፣ በአማራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ 222 ወረዳዎች ላይ የበሽታው ሥርጭት በስፋት እንደሚስተዋል ከፌዴራሉ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡

የወባ ትንኝ
የወባ ትንኝምስል James Gathany/AP/picture alliance

የወባ ወረርሽኝ ፈተና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል

This browser does not support the audio element.

የወባ ወረርሽኝ ፈተና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል


በኢትዮጵያ ካለው አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 75 በመቶ ያህሉ ለወባ በሽታ ሥርጭት አመቺ መሆኑ ይነገራል፡፡ አሁን ላይ በኦሮሚያ ፣ በአማራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ  222 ወረዳዎች ላይ የበሽታው ሥርጭት በስፋት እንደሚስተዋል ከፌዴራሉ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቤንች ሸኮ ዞን የሚገኘው የጉራፈርዳ ወረዳ የወባ ወረርሽኝ ከበረታባቸው አካባቢዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳል ፡፡ ነዋሪዎች እንደሚሉት በተለይ በዚህ ዓመት በወረዳው ተስፋፍቷል ባሉት በሽታ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች  ህይወታቸው አልፏል ፡፡ አሁን ላይ  በሽታው የአልጋ ቁራኛ ያደረጋቸው ሰዎች ቁጥርም ቀላል አይደለም ነው የሚባለው ፡፡


“ታክሞ መዳን ብርቅ እየሆነ ነው “


በቤንች ሸኮ ዞን የጉራፈርዳ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ማሞ ቦኒ በግብርና ሥራ እንደሚተዳደሩ ይናገራሉ ፡፡ በወባ በሽታ ህይታቸው ያለፉትን አጎታቸውን ከሳምንት በፊት መቅበራቸውን ለዶቼ ቬለ የገለጹት ማሞ እሳቸውና ልጃቸውም በተመሳሳይ ታመው እንደሚገኙ ተናግረዋል ፡፡
ጤና ጣቢያ የወሰዱት አጎታቸውን የጭንቅላት ወባ እንዳለባቸው በሐኪሞች እንደተነገራቸው የጠቀሱት ማሞ “ ያም ሆኖ ከሦስት ቀናት በኋላ ህይወቱ አልፏል ፡፡ እሱን ቀብሬ ስመለስ እኔም ታምሜ ተኛሁ ፡፡ ቆይቶ ልጄም ትኩሳት ሲጀምረው ወደ ህክመና ይዤው ሄድኩኝ ፡፡ አሁን ሁለታችንም ተኝተን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡
በሽታው መድሃኒቱን የተለማመደ ይመስለኛል የሚሉት ሌላው የወረዳው ነዋሪ ሰይድ ገብሬ “ የምንሰማው ሁሉ ሞተና ታመመ ነው ፡፡ ከአንድ ቤት እስከ አምስት  የሚደርሱ ሰዎች በበሽታው ተኝተው ያሉበት ሁኔታ አለ ፡፡  እዚህ ታክሞ መዳን ብርቅ እየሆነ መጥቷል “ ብለዋል፡፡


የበሽታው ምጣኔ
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ የወባ በሽታ ስርጭት የታየበት አካባቢ ነው ፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ  ይፋ ባደረገው አሃዛዊ መረጃ በክልሉ ባለፉት 11 ወራት የወባ ምልክት ታይቶባቸው ከተመረመሩ 959 ሺህ , 944  ሰዎች መካከል 538 ሺህ , 327  ወይም 56% በመቶ የሚሆኑት በደማቸው የወባ አማጭው ተህዋስ ተገኝቶባቸዋል ፡፡ ምንም እንኳን መረጃው በበሽታው ህይወታቸው ያለፉ ሰዎችን ቁጥርን ባያካትትም፡፡  
አሁን ላይ በክልሉ በየዞኑ ከአሥር እስከ ሃያ ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በወባ መታመማቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የቢሮው ምክትል ሃላፊና የፕሮግራም ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሀይሌ ዘውዴ የመረጃው ዋና  ዓላማ ቁጥሩ ሳይሆን የወባ ምጣኔው ከፍተኛ መሆኑን ለማሳየት የተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምስል privat


የመፍትሄው እርምጃ
በአገርአቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የወባ በሽታ ሥርጭት ያሳሳበው የጤና ሚኒስቴር በዚሁ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሚዛን አማን ከተማ በጉዳዩ ዙሪያ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ አካሂዷል ፡፡የአየር ንብረት መለዋወጥና ቀደምሲል በቀበሌ ደረጃ ሲሰጥ የነበረው የጤና ኤክስቴንሽን ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች ሥራ መቀዛቀዝ  ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት መሆኑን በምክክር መድረኩ ላይ ተጠቅሷል ፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በክልላቸው ወባ በእያንዳንዱ ቤት ሥለመግባቱ ነው የገለጹት ፡፡ ክልሉ ያለውን የፋይናንስ እና የሰው ሀይል በመጠቀም በሽታውን ለመከላከል ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ፡፡
አሁን ላይ ክልሉ የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ ከክልል እስከ ቀበሌ የተዘረጋ ግብረ ሃይል ተዋቅሮ ወደ ሥራ መገባቱን የጠቀሱት የክልሉ ጤና ቢሮው ምክትል ሃላፊና የፕሮግራም ዘርፍ ሃላፊው አቶ ሀይሌ ዘውዴ “ የአልጋ አጎበር ፣ የመመርመሪያ ቁሳቁሶች እና የፈውስ መድሃኒቶችን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶች  አቅርቦት ወደ ወረዳዎች እየተሰራጨ ይገኛል ፡፡ ይህን አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ የበሽታው ሥርጭት መጠንን ለመቀነስ ያስችላል ብለን እየሰራን እንገኛለን “ ብለዋል፡፡


ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW