1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወጣቱ ፖለቲካዊ ተሳትፎ

ዓርብ፣ የካቲት 23 2010

ኢትዮጵያ ባለፉት ሳምንታት የተለያዩ ክስተቶችን አስተናግዳለች። ህብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ እስረኞች እንዲለቀቁ ጥያቄውን በተለያየ መንገድ ሲያቀርብ ነበር። ይህም ለእስረኞች መፈታት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉ ይነገራል። በሌላ በኩል ወጣቱ በቁጣ ንብረት አውድሟል እየተባለም ስሙ ይነሳል ።

Äthiopien Tote bei Anti-Regierungs-Protesten in Bishoftu
ምስል DW/Y. Gegziabher

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በይበልጥ የሚሳተፉት ወጣቶች ናቸው። ጥያቄያቸው ተመሳሳይ ነው። ያለ አግባብ የታሰሩ እስረኞች ይፈቱ፣ የሰብዓዊ መብት ይከበር ፣ፍትህ እና መልካም አስተዳደር ይስፈን፣ የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው።  የነገ ሀገር ተረካቢ ነው የሚባለው ወጣት ከዚህም አልፎ በተደጋጋሚ የስርዓት ለውጥ እንደሚፈልግ ጠይቋል።  በተለይ በኦሮምያ እና አማራ ክልል በተደጋጋሚ የተካሄዱት ተቃውሞዎች በመንግሥት ላይ ጫና እንደፈጠሩ እና ባለፉት ሳምንታት ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ለተለቀቁ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች መፈታት ምክንያት እንደሆኑ ራሳቸው ተቃዋሚዎቹ እና የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

ስሙን ያልገለፀልን አንድ የቄሮ ወይም የወጣቶች ተቃውሞ ተሳታፊ እንደሚለው ወጣቱ ተቃውሞውን ካሰማ በኋላ ጥያቄው 50 በመቶ ተሰሚነት አግኝቷል። ግን ይላል« መንግሥት ለኛ አዝኖ ያደረገው አይመስለኝም»ይሁንና የወጣቶቹ ተሰሚነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመልሶ ወደነበረበት ቦታ ተመልሷል ይላል ወጣቱ። ወቅታዊው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በወጣ ማግስት እሱ እና ሌሎች 150 የሚጠጉ ወጣቶች  ጭራሽ ስራ አጥ ሆነዋል። « መንግሥት በዘረጋው መንገድ ስራ አጦች ተደራጅተን እየሰራን ነበር በቤተሰቦቻችን ማሳ ላይ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መከታ አድርገው ግን  ወታደሮች መጥተው ከቦታው አባራሩን»

ምስል REUTERS/File Photo/T. Negeri

ጎንደር አካባቢ የሚኖረው ሱልታንም የወጣቱ ተሳትፎ በከፊልም ቢሆን መፍትሄ አስገኝቷል ከሚሉት አንዱ ነው። በሌላ በኩል በወጣቱ የወደሙ ንብረቶች አግባብ አይደሉም ይላል። « የመንግሥት ገንዘብ ማለት የህዝብ ገንዘብ ነው። » ይሁንና የህዝቡን ቁጣ ለማስቆም የተደነገገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መፍትሄ ነው ብሎ አያምንም። እሱ እንደሚለው በአሁኑ ሰዓት ወጣቱ በአንዱ በኩል የሚቀየር ነገር የለም ብሎ ተስፋ በመቁረጥ በሌላ በኩል ደግሞ በአዋጁ ምክንያት ዝም ተሰኝቶ ነው ያለው። « ዘመናዊ ቅኝ ግዛት ላይ ነው ያለነው። ወጣቱ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አያደርግም። ፍርሃት ላይ ነው ያለው።» 

ቢቢ ዱባይ አገር በስራ ላይ የምትገኝ ኢትዮጵያዊት ወጣት ናት። ሀገሯ ውስጥ የተደረጉትን የወጣቶች ተቃውሞዎች በቅርበት ተከታትላለች። ወጣቱ በእሷ ዓይን ከፍተኛ ተሳትፎ ቢያደርግም ተሰሚነት ሊያገኝ ግን አልቻለም። የወጣቱም ጥያቄ የሷም ጥያቄ ነው።

ምስል Reuters/T. Negeri

ምስጋናው« ከ20 ዓመት በታች ያለው ወጣት ነው ከመንግሥት ጋር ፊት ለፊት እየተጋፈጠ ያለው» ይላል። ትዝብቱን ሲናገር። « ወጣቱ ለለውጥ ዝግጁ መሆኑ ይታያል። በተለይ በኦሮምያ እና አማራ ክልል። እኔም የለውጡ አካል ነኝ።» ምስጋናው  ሹፌር ስለሆነ በተለያዩ አካባቢዎች በተዘዋወረበት ጊዜ ተቃውሞዎችን ታዝቧል። እሱ እንደሚለው ወጣቱ በሰላማዊ መንገድ ሀሳቡን ገልጿል። አልፎ አልፎም ስሜታዊነት ታይቶበታል። 

ይህም  ስሜታዊነት በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩትን ኢትዮጵያዊ መሀመድ ያስቆጣ ጉዳይ ነው።  « ወጣቱ ከህግ በላይ መሆን የለበትም። መንገድ መዝጋት፣ ፋብሪካ ማቃጠል፣ ዘር እየለዩ መምታት አያስፈልግም። ምርጫ ቅርብ ነው። ህዝቡ የማይፈልገው ከሆነ በምርጫ ሊወርድ ይችላል መንግሥት»

ነፃ ምርጫ ተካሂዷል ወይም ይካሄዳል ብለው ግን ብዙዎች አያምኑም። ይህም ነው የቄሮውን ወጣት ለምሳሌ ወደ ተቃውሞ ሰልፍ የገፋፋው። በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የወጣቱን ተሳትፎ የቃኘው የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅትን በድምፅ መከታተል ይችላሉ።

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW