1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወጣቶች ዓለም

ዓርብ፣ ሚያዝያ 29 2013

ካለፈው ታህሳስ ወር አንስቶ ዶይቸ ቬለ DW  «ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች» በሚል ርዕስ የቪዲዮ ዘገባዎችን በአራት ቋንቋዎች እያቀረበ ይገኛል። ዘገባዎቹ በተለይ እድሜያቸው በአስራዎቹ ለሚገኙ አዳጊ ሴቶች መድረክ የሚሰጥ ነው። በዚህ ዝግጅት እድሜያቸው በአስራዎቹ የሚገኙ አዳጊ ሴቶች ከእኩዮቻቸው ጋር እነሱን በሚስቧቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ።

ሊዲያ መለስምስል M. Teklu/DW

This browser does not support the audio element.

የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ወይም GIRLZ OFF MUTE ዝግጅት ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በእንግሊዘኛ ፈረንሳይኛና ኪሲዋሂሊኛ ይቀርባል።  በዚህ ዝግጅት እድሜያቸው በአስራዎቹ የሚገኙ አዳጊ ሴቶች ከእኩዮቻቸው ጋር በመሆን እነሱን በሚስቧቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ። ዘጋቢ ሌና ለምሳሌ የጋምቢያ ቀዳማዊት እመቤት ልክ እንደሷ እድሜያቸው 16 የነበረ ጊዜ ህይወታቸው ምን ይመስል እንደነበር ማወቅ ስለፈለገች ወደ ቤተ መንግስት ጎራ ብላ ጠይቃለች።  ርዕሶቹ ሁሌ አዝናኝ ብቻ አይደሉም።  በወጣት ሴቶች ላይ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ፆታዊም ይሁን ወሲባዊ ጥቃቶች እንዲሁም እርግዝናን የመሳሰሉ ችግሮችን ዘጋቢዎቹ በማንሳት ለችግሮቹ መፍትሄ ያፈላልጋሉ።  የሊዲያ መለስ የመጀመሪያ  ዘገባ በሴት ልጅ ግርዛት ላይ ነበር።ሊዲያ የድሬደዋ ልጅ ናት። ዘገባውን ለማጠናቀር ከተለያዩ ጉዳዮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይታለች። « ስራው ሴቶችን የሚደግፍ እና ያለብንን ችግሮች የሚፈታ ነው » የምትለው  የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ሊዲያ ከትምህርቷ ጎን ለጎን ለምትሰራው ዘጋባ ከዚህ ቀደም የነበራት ተሞክሮ ረድቷታል።  በድሬ ቲቪ የህፃናት ፕሮግራም ዝግጅት ላይ ፤ በሬዲዮ እና በትምህርት ቤት ደግሞ የሚኒ ሙዲያ ዝግጅቶች ላይ ተካፍላለች። ሌላዋ  የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅት አቅራቢ ሊሻን ዳኜም በቂ ልምድ ቀስማለች። « ለጋዜጠኝነት ሙያ ካለኝ ፍቅር ከ 5 ኛ ክፍል ጀምሮ ከትምህርቴ ጎን ለጎን በልጆች ፕሮግራም በአቅራቢያችን በሚገኘው በደቡብ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት  በራዲዮ እና ቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ እየሰራሁ እገኛለሁ» ሊሻን ከምትኖርበት የሀዋሳ ከተማ በመሆን የተለያዩ የቪዲዮ እና የሬዲዮ ዘገባዎችንም ለ ዶይቸ ቬለ መስራት ጀምራለች። የሰርከስ ትርኢት የሚያሳዩ ፤ ጎዳና ላይ ጫማ እየጠረጉ የሚማሩ እንዲሁም የመዝፈን እና የእጅ ስራ ተሰጥዎ ካላቸው አዳጊ ሴቶች ጋርም ቆይታ አድርጋለች። ሊሻን እስካሁን ድረስ ስለሰራችው ስራዎች ስትናገር  «ደስ ብሎኝ እየሰራሁ ነው » ትላለች። « ሴቶች ያላቸውን ተሰጥዎ አውጥተው እንዲያሳዩ የሚያበረታታ ስራ ነው። ከማቀርባቸው ልጆች ጋርም እንደ ጓደኛ እያወራን እና እየተወያየን ነው የምንሰራው» ሊሻን እድሜዋ 17 ሲሆን የ 11ኛ ክፍል ተማሪ ናት። ለጋዜጠኝነት ሙያ እንድትሳብ ያደረጓት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አርዓያ የምትላቸው ጋዜጠኞች እንደሆኑ ለ ዶይቸ ቬለ DW  ገልፃለች። 
የዶይቸ ቬለ GIRLZ OFF MUTE ወይም የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች እስካሁን ከአፍሪቃ አህጉር 15 ሀገራት ሆነው በተለያዩ ርዕሶች ላይ ዘግበዋል። ከ 50 በላይ አዝናኝ እና አስተማሪ ቪዲዮዎችን ደግሞ ሰርተዋል። ዘጋቢዎቹ እንደ ሊሻን ዳኜ እና ሊዲያ መለስ የመሳሰሉ ከ 13 እስከ 17 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ደፋር ሴቶች ናቸው።  « በዚህ «ፕሮግራም የሴቶች ድምፅ የምሆን ይመስለኛል» የምትለው ሊዲያ  ሌላው ማሳካት የምትፈልገው ነገር የ12ኛ ክፍል ፈተናዋን በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅ ነው።  በየተኛውም ዘርፍ ይሁን ጥሩ ቦታ መድረስ ዋና አላማዋ ነው።  ሊሻን ግን ወደፊትም በጋዜጠኝነት ሙያ መግፋት ዋናው አላማዋ ነው። ሊሻንም ትሁን ሊዲያ በሚሰሩት ስራ ቤተሰባቸው ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ሁለቱም ነግረውናል። 

ሊሻን ዳኜምስል Shewangizaw Wegayehu/DW
ዘጋቢ ሌና ከጋምቢያ ቀዳማዊት እመቤት ጋርምስል Omar Walle/DW

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW