1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወጣቶች የአዲሱ ዓመት ተስፋ እና ስጋት

ማክሰኞ፣ መስከረም 8 2016

«በ2016 ሰላማዊ የሆነች ምድርን ማየት እናፍቃለሁ።ሰላማዊት ኢትዮጵያን እናፍቃለሁ።አንድነቷ አብሮነቷ ተጠብቆ የሚቆይባትን ሀገር እናፍቃለሁ።»ጋዜጠኛ መክሊት ወንድወሰን።ሌላዋ ወጣት ቤተልሄም ሀይሉ በበኩሏ«በ2016 ዓ/ም ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቀሉ፣ረብሻ ተፈጠረ ጦርነት አለ የሚሉ ዜናዎችን ባንሰማ»በማለት ምኞቷን ገልፃለች።

የኢትዮጵያ ዓዲስ ዓመትን ለመቀበል የአበባአየሁሽ ጭፈራ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች
የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት የልጃገረዶች የአበባአየሁሽ ጭፈራ በአዲስ አበባ ምስል Author Hana Demissie/DW

የአዲሱ ዓመት ተስፋ እና ስጋት

This browser does not support the audio element.

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ሁለት ወጣት ሴቶችን በእንግድነት ጋብዟል።ወጣቶቹ  ከአራት ቀናት በፊት የተቀበልነውን አዲስ ዓመት በተመለከተ ያላቸውን ዕቅድ፣ ተስፋ እና ስጋት አጋርተውናል ።
አሮጌውን 2015 ዓ/ም ሸኝተን አዲሱን 2016 ዓ/ም ከተቀበልን እነሆ አራተኛ ቀን ተቆጥሯል።አዲስ አመት ሲመጣ  አዲስ ዕቅድ እና ተስፋ መሰነቅ የተለመደ ነው።በተለይ በወጣቶች ዘንድ።የ23 ዓመቷ  ወጣት ቤተልሄም  ሀይሉም  ከአራት ቀናት በፊት በተቀበልነው 2016 ዓ/ም የራሷ ዕቅዶች አሏት። በ2013 ዓ/ም በጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ከቡሌ ሆራ ዩንቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን የያዘችው ወጣቷ፤ ላለፈው አንድ አመት ተኩል  በአንድ ድርጅት ውስጥ የሚዲያ ይዘት እና ስርጭት ቡድን ውስጥ  በመስራት ላይ ትገኛለች። ቤተልሄም  የሁለተኛ ዲግሪዋን ለመያዝም ትምህርት ጀምራለች።  የጀመረችውን ትምህርት በጥሩ ሁኔታ ማጠናቀቅ እና በስራዋ የተሻለች መሆን የአዲሱ ዓመት 2016 ዓ/ም የግል ዕቅዷ እና ምኞቷ ነው። ያም ሆኖ ከግሏ ስኬት እና ምኞት ይልቅ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የሰላም እጦት ያሳስባታል።

«በአዲሱ ዓመት ተስፋዬ እንግዲህ በስራም በትምህርትም የተሻለ ነገር ለመስራት ነው። ያው ነገሮችን ለማሻሻል በትምህርት ራስን ማብቃት ስለሚያስፈልግ ተስፋዬ እንግዲህ እሱ ነው።እማራለሁ በደንብ እሰራለሁ የሚል ተስፋ አለኝ።»ካለች በኋላ ስጋቷን እንዲህ ስትል ትገልፃለች።«ስጋቴ ደግሞ ሀገራችን አሁን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ በየአካባቢው የሚታዩ ነገርች ስጋቴ ነው።በዚህ ዓመት እንደዚህ አይነት ነገሮችን ባንሰማ። እኔ ብቻ ሳይሆን በእኔ እድሜ ያሉት ወጣቶች እንደዚህ አይነት ነገሮችን ባንሰማ ደስ ይለናል።ለመስራትም፣ ለመማርም፣ ለመኖርም የምንኖርበት ሀገር ሰላም ወሳኝ ስለሆነ፤የተረጋጋች ሀገር ካለችን መማርም መስራትም ስለምንችል ስጋቴ እሱ ነው።»በማለት ገልፃለች።የአዲሱ ዓመት የወጣቶች ዕቅድና ተስፋ 
በመሆኑም በተሸኘው 2015 ዓ/ም በኢትዮጵያ የተከሰቱ  ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች በአዲሱ 2016 ዓ/ም መሻገር የለበትም የሚል ምኞት አላት።
«መሻገር የለበኅም ብዬ የማስበው ነገር በቃ እንደዚህ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቀሉ ረብሻ ተፈጠረ ጦርነት አለ የሚሉ ዜናዎችን ባንሰማ በ2016።እኔ በግሌ ኢኮኖሚ አደገ ሳይሆን መስማት የምፈልገው ሰላም ነው።በኢኮኖሚ አቅም ማደግ አንድ ሀገር ሰላሟ ከተረጋጋ የትኛውም ሀገር ያለ ሰው መጥቶ ይሰራባታል ሰላሟ ከተረጋገጠ።ኢትዮጵያ ደግሞ የምንም ችግር የለባትም።በተፈጥሮ የኃደለች ሀገር ነች።ብቸናው ነገር እንዳትበለፅግ የሚያደርጋት የሰላም እጦት ስለሆነ፤ በአሁኑ አመት ላይ ሙሉ ለሙሉ ይህን ያህል ሰው ታመመ፣ከመኖሪያ መንደሩ ተፈናቀለ የሚሉ አሳዛኝ ክስተቶችን 2016 ላይ ባንሰማ እመርጣለሁ።» በማለት ምኞቷን ተናግራለች።

ወጣት ቤተልሄም እንደምትለው አሁን በሀገራችን እየታዬ ያለው የሰላም እጦት «ሁሉም ዘሩን በመምረጡ ነው»። በመሆኑም፤ በዘር ማንነት ላይ ከማተኮር ይልቅ ኢትዮጵያዊነት ላይ ቢሰራ ለችግሩ መፍትሄ ነው የሚል እምነት አላት።
በሌላ በኩል «ወጣትነት እንዲሁም ሴትነት ብዙ ፈተና ዓለው» የምትለው ቤተልሄም ከተመረቀች በኋላ  ስራ በመፈለግ ብዙ ውጣውረዶችን እንዳሳለፈች ገልፃለች።ያም ሆኖ ወጣቶች በዓዲሱ ዓመትም ይሁን በአጠቃላይ በህይወታቸው ለሚገጥማቸው ፈተና ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው ትገልፃለች።ከልምዷ በመነሳትት።

ቤተልሄም ሀይሉ «2016 ዓ/ም ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቀሉ፣ረብሻ ተፈጠረ ጦርነት አለ የሚሉ ዜናዎችን ባንሰማ»በማለት ምኞቷን ገልፃለችምስል Privat

«እንግዲህ እኔ የማስበው ብዙ ፈተና አለ።በሁሉም ቦታ ፈተና አለ ከባድ ነው።ነገር ግን እነዚህን ችግሮች ለማለፍ ትዕግስት በጣም ያስፈልጋል። እኔ ከራሴ  ልምድ ስነሳ በእርግጥ ትንሽ ጊዜ ነው በስራ ሳልሰማራ የቆየሁት ግን ስራ ለመፈለግ ለፍቻለሁ ተንከራትቻለሁ እውነት ለመናገር።እና ትዕግስት ነው የሚያስፈልገው።ቤት መቀመጥ አያስፈልግም በፈለግን ቁጥር አማራጮች ይመጣሉ።ትምህርት ላይ ያሉም ቢሆኑ  ወጣቶች በአጠቃላይ።» ትልና፤ «ብዙ «ቻሌንጆች» ሀገራችን ውስጥ ስላሉ፤ ተስፋ የሚያስቆርጡ ብዙ ምክንያቶች አሉ።የምንኖረውም በተስፋ ስለሆነ ተስፋ መቁረጥ በፍፁም አያስፈልግም።እነዚህን ነገሮች በትዕግስት ከታለፈ ከታሰበበት ቦታ ይደረሳል።»በማለት አብራርታለች። 

በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ወጣቷ ጋዜጠኛ መክሊት ወንድወሰን በበኩሏ፤በዓዲሱ ዓመት በግሏ የራሷ እቅዶች አሏት። በ2014 ዓ/ም የመጀመሪያ ዲግሪዋን የያዘችው መክሊት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ በጋዜጠኝነት ሙያ በመስራት ላይ ትገኛለች።መክሊት አሮጌውን 2015 ዓ/ምን የተሻገረችው ተስፋ እና ስጋት ይዛ ነው።
«ሁለት ነገሮችን ይዤ ነው የምሻገረው። የመጀመሪያ ተስፋ አደርጋለሁ።ምንድነው ተስፋ የማደርገው ፤ሀገሬ ምድሬ ሰላም ሰፍኖባት ብዙዎችም ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተጠብቆላቸው እንደገና ደግሞ ሰዎች ስራ ፈልገው የሚገኙበት ዓመት እንዲሆን እንደዚያ  አይነት ነገሮችን አስባለሁ።ነገር ግን አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታዎች የሚያመክቱት እንደምናየው ከሆነ ማለት ነው፤እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች የሚያድጉ ከሆነ በፊት እንደተፈጠረው ያለ ችግሮች እንዳይፈጠሩ የሚል ስጋትም አለኝ።በሰሜኑ በኩል የነበረው የሁለት ዓመት ጦርነት የምናውቀው ነው ብዙ ሰው አሳጥቶናል።ብዙ የሰውም የንብረትም ውድመት አድርሶብናል።»ካለች በኋላ፤ ከዚያ አንፃር አሁን በሀገሪቱ የሚታዩ አለመረጋጋቶች የሚቀጥሉ ከሆነ ልክ እንደ ሰሜኑ ጦርነት የሰው እና የንብረት ውድመት  ሊያሳጣን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላት መክሊት ገልፃለች።ኢትዮጵያና የአዲሱ ዓመት ተስፋ
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ104  ሚሊዮን በላይ  ከሚገመተው የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ 41 በመቶው እድሜው ከ15 አመት በታች ነው።ከ28 በመቶ በላይ የሚሆነው ከ15 እስከ 29 አመት እድሜ ያለው ነው።ይህ  ወጣት ሀይል ለሀገሪቱ  ከፍተኛ ሀብት እና ያልተነካ የእድገት ምንጭ ቢሆንም፤ የወጣቶች ስራ አጥነት ወደ 27 በመቶ እንደሚሆን ይገመታል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ለወጣቶች የምትመች እና ወጣቱ ተስፋ የሚሰንቅባት ሀገር እንድትሆን በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ እንዲሁም ለወጣቱ የስራ ዕድል መፍጠር መክሊት እንደምትለው በመንግስት በኩል በ2016 ዓ/ም ሊተኮርበት የሚገባ ጉዳይ ነው።ያ ካልሆነ ግን ወጣቱ ለፖለቲከኞች መጠቀሚያ ይሆናል የሚል ስጋት አላት።ከዚያ አለፍ ሲልም ወጣቱ በሀገሩ ተስፋ በማጣት በህገወጥ መንገድ ጭምር ለስደት ይዳረጋል ። ይህ ደግሞ ሀገሪቱን አምራች ዜጋ  ሊያሳጣ የሚችል መሆኑን  ጨምራ  አስረድታለች።በሌላ በኩል በ2015 ዓ/ም የተሰሩ እንደ ችግኝ ተከላ ያሉ አንዳንድ የልማት ስራዎች ቢቀጥሉ መልካም መሆኑን ትናገራለች። 

መክሊት ወንድወሰን ጋዜጠኛ «በ2016 ሰላማዊ የሆነች ምድርን ማየት እናፍቃለሁ።ሰላማዊት ኢትዮጵያን እናፍቃለሁ።አንድነቷ አብሮነቷ ተጠብቆ የሚቆይባትን ሀገር እናፍቃለሁ።»ምስል Privat

«እንግዲህ ከ2015 ከነበረን ነገር መሻገር አለበት ብለን የምንለው ነገር።አንዳንድ የልማት ስራዎች ተሳክተዋል እነኝህ የልማት ስራዎች ለምሳሌ የህዳሴው ግድብ ሙሌት የ«ግሪን ሌጋሲ» ጉዳይ እንደዚህ እንደዚህ ያሉ ትልልቅ ስራዎች ተሰርተዋል እና እነዚህ ነገሮች በ2016 ተሻግረው መቀጠል አለባቸው።ነገር ግን «ፖለቲካል» የሆነው ነገር «አንስቴብል»የሆነው ነገር ግን መቀጠል የለበትም።ምክንያቱም ብዙ ነገር ነው እያሳጣን ያለው።ኢኮኖሚያችን በየጊዜው እየወረደ ነው የሚመጣው።ሁሉንም ነገር የሚይዘው ሀገሪቱ ላይ ያለው ሰላም እና የመረጋጋት ሁኔታ ነውና  የሰላም እና መረጋጋት ሁኔታው  እንግዲህ ፈጣሪ ፈቃዱ ቢሆንልን በ2016 ሰላማዊ የሆነች ምድርን ማየት እናፍቃለሁ።ሰላማዊት ኢትዮጵያን እናፍቃለሁ።አንድነቷ አብሮነቷ ተጠብቆ የሚቆይባትን ሀገር እናፍቃለሁ።»በማለት ጋዜጠኛ መክሊት ወንድወሰን በ2016 ዓ/ም ያላትን ተስፋ እና ምኞት ገልፃለች።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
 

ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW