1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዉይይት ርእስ ሆኖ የቀጠለው የኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ

ሰለሞን ሙጬ
ሰኞ፣ ጥቅምት 25 2017

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን "ሁሉም ለድርድር በመተማመን በሩን እንዲከፍት"ተጠየቀ። ተቋማት አንድም "የመግዣ፣ በሌላ በኩል መንግሥትን የማውረጃ መሣሪያ" ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ያሉ አስተያየት ሰጭ፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም የመንግሥት መሣሪያ ከመሆን የሚወጣ አይደለም ብለዋል። ኮሚሽኑ በበኩሉ ገለልተኛ መሆኑን ገልጿል።

የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መታሰቢያ ፋዉንዴሽን አራተኛ ዓመታዊ ጉባዔ
የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መታሰቢያ ፋዉንዴሽን አራተኛ ዓመታዊ ጉባዔምስል Solomon Muche/DW

የዉይይት ርእስ ሆኖ የቀጠለው የኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ

This browser does not support the audio element.

የዉይይት ርእስ ሆኖ የቀጠለው የኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ 

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን "ሁሉም ለድርድር በመተማመን በሩን እንዲከፍት" የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መታሰቢያ ፋዉንዴሽን ጠየቀ። ፋዉንዴሽን "ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን የሰላም ችግር በምክክር እና በውይይት ለመፍታት ምን መደረግ እንዳለበት መንገድ ለመጠቆም" ያግዛል ያለውን አራተኛ ዓመታዊ ጉባኤውን ትናንት አከናዉኗል። 

ተቋማት አንድም "የመግዣ፣ በሌላ በኩል መንግሥትን የማውረጃ መሣሪያ" ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ያሉ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ፣ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንም የመንግሥት መሣሪያ ከመሆን የሚወጣ አይደለም ብለዋል።  የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ግን ገለልተኛ እንደሆነና ተጽዕኖ ደርሶበት እንደማያውቅ ገልጿል። 

የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መታሰቢያ ፋዉንዴሽን "ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲታወቅ፣ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እና ከሀገሪቱ ረሃብ እንዲነቀል"ይሠራል ተብሏል። ይሄው ተቋም ትናንት ባዘጋጀው ውይይት ላይ ከተሳተፉት ሰዎች መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ምብቶች ኮሚሽን የቀድሞው ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ አንዱ ሲሆኑ "ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ከገጠመን ችግር አንፃር ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ተከስቷል" ብለዋል። ሆኖም ችግሩ "ከኢትዮጵያውያን አቅም በላይ ነው ብየ አላምንም" የሚል እምነታቸውንም አጋርተዋል። በኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታ እና በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ባጠነጠነው ውይይት ኮሚሽኑ እስካሁን የገጠመው ዋናው እንቅፋት የፀጥታ ችግር መሆኑን ገልጿል። 

"ምክክር ምን ያህል ሰላም ያመጣል" የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ሀሳብ የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዶክተር ዮናስ አሽኔ የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱት በምክክር ብቻ ሳይሆን በድርድር፣ በውይይት እና በክርክር ነው የሚል አቋም አራምደዋል። በኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ የባህል እና የተቋም ግንባታ ዐይን "የምንሠራቸው ተቋማት ያን ያህል ነፃ ይሆናሉ ብለን መጠበቅ የለብንም" ያሉት ባለሙያው ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት እንደ ማህበረሰብ ነፃ ተቋም መገንባት ተቸግረናል ብለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቋማት በሁለት ጫፍ የሚገኙ ማለትም "አንደኛው የመግዣ ምሣሪያ፣ ሁለተኛው ደግሞ መንግሥትን የማውረጃ መሣሪያ ሆነው ነው የሚሰሩት" በማለት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ከዚህ የሚርቅ እንዳልሆነ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።

 

"የፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ የሚካሄድ ምክክር ነው"

ባለሙያው ኮሚሽኑየፖለቲካ ባሕልን የማሳደግና የማልማት፣ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ መሰረት መጣል የሚሉ ዓላማዎቹን ትቶ በምክክር ላይ ብቻ ስለማተኮሩም አብራርተወል። ኮሚሽነር መላኩ ወልደ ማርያም ግን ይህ በሂደት የሚታይ ውጤት መሆኑንን "አዲስ የፖለቲካ ባህል መገንባት ማለት አሁን በተጀመረው ሂደት ሕዝቡ የፖለቲካ ባህል እየገነባ እንዲሄድ ማስቻል ነው። መጨረሻ ላይ ምን አይነት የፖለቲካ ሥርዓት እንዲኖር እንደሚፈልግ ሕዝቡ ራሱ የሚወስነው ጉዳይ ይሆናል" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። መንግሥት ከሕዝብ የሚቀርብለትን የምክክር ውጤት ለማስፈፀም ቁርጠኛ መሆኑን እንደገለፀላቸውም በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል። "ሕዝበ ዉሳኔ እንኳን የሚጠይቅ ቢሆን - የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ያንን የማስፈፀም ግዴታ አለብን የሚል ምላሽ ነው ያገኘነው"

የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መታሰቢያ ፋዉንዴሽን አራተኛ ዓመታዊ ጉባዔምስል Sololomon Muchie/DW

ዶክተር ዮናስ አሽኔ የምክክር ሂደቱ በሰላሌ "ማረስ አልቻልንም፣ ግጭት አቁሙና ለማረሻ ጊዜ እና ፋታ ስጡን" በሚል የቀረበውን ጥያቄ፣ የጋሞ አባቶችን የሰላም አማራጭ መንገድ፣ ባህር ዳር ላይ ገበሬዎች ማዳበሪያ ስጡን በሚል ያቀረቡትን የአደባባይ ጥሪ" ያልሰማና አካታችነት የጎደለው" መሆኑን ገልፀዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን መንግሥት ከሕወሓት ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ወደ ፕሪቶሪያ፣ ከኦነግ ጋር ለመነጋገር ወደ ዳሬ ሰላም ሲጓዝ እንኳን የምክክር ኮሚሽኑ ባለቤት አለመደረጉ እና ተሳታፊ አለመደረጉን ላቀረቧቸው ትችቶች አስረጂ አቅርበዋል። ይህም በመሆኑ ሌላ አማራጭ የሰላም መምገድን ጠቁመዋል።

"የኢትዮጵያ የጋራ የሰላም ፍኖተ ካርታ ወይም ማዕቀፍ ያስፈልጋል" 

የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መታሰቢያ ፋዉንዴሽን የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ የኔመንግሥት ደምሴ ፕሮፌሰር መስፍን ከ 34 ዓመት በፊት "የጅምላ አፈና ለነፃ አውጪ ቡድኖች መበራከት አስተዋጽዖ ማድረጉን" መግለፃቸውን በመጥቀስ ዛሬስ ሲሉ ጠይቀዋል። 

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW