የዋሊያና ቀይ ቀበሮ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔት ተመናምኗል ተባለ
ዓርብ፣ ጥቅምት 29 2017የዋሊያና ቀይ ቀበሮ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔት ቀንሷል ተባለ
በተለያዩ ጊዜዎች የሚፈጠሩ ጦርነቶች በሠዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በዱር እንስሣት ላይም ስደትና ሞት እያስከተለ እንደሆነ የእንሣት ጥበቃ ባለሙያዎች ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ብቸኛ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ዋሊያ አይቤክስና ቀይ ቀበሮ ቁጥራቸው ቀደም ሲል ከነበረው በግማሽ መቀንሳቸውን የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክአስታውቋል። የኢትዮጵያ የዱር እንሣት ጥበቃ ባልስልጣን በበኩሉ የእንሣቱን ቁጥር ለመጨመር እቀድ ቢወጣም አሁን ያለው የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ ካልተሻሻለ ለመተግበር እንደሚቸገር አመልክቷል።
ቀድም ሲል በኢትዮጵያ መንግሥትና በኢህአዴግ፣ በቀርቡ ደግሞ በህወሓትና በኢትዮጵያ መንግሥት በነበሩ ጦርነቶች፣ አሁን ደግሞ በክልሉ ባለው ያልተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ የዱር እንስሣት ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሣት ጥበቃ ባልስልጣን አመልክቷል።
“የብርቀዬ እንስሣት” ቁጥር እየቀነሰ ነው
በባለስልጣኑ የምርምርና ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፈቀደ ረጋሳ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የነበረው የዋሊያ አይቤክስ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል። አደን በአካባቢው የተወገዘ ቢሆንም አሁን ያለውን የአካባቢው ወቅታዊ የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ ዋሊያም ሆን ቀይ ቀበሮ እየታደኑ እየተገደሉ እንደሆን ነው ያመለከቱት።
ሁለቴ በተካሄደ ቆጠራ የዋሊያ አይቤክስ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን የግለፁት ዶ/ር ፈቀደ፣ የዱር እንስሳቱ ቁጥር የቀነሱበት ዋናው ምክንያት አደን መሆኑን አስረድተዋል። የአካባቢው ህብረተሰብ አደን እንደማያበረታታ ቢታወቅም፣ በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ለህገወጥ አደን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጠዋል። ህብረተስቡ ለዋሊያ ልዩ ፍቅር እንዳለው የተናገሩት ኃላፊው በኢትዮጵያ ታሪክ ዋሊያ የገደለ አንድ ግለሰብ በ25 ዓመት እስራት እንዲቀጣ የተፈረደበት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ እንደሆነም አስረድተዋል።
የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ ማሩ ቢያድግልኝ በበኩላቸው ከዚህ በፊት 865 ደርሶ የነበረው የዋሊያዎች ቁጥር በ2016 ዓ ም በተደረገ ሁልት ቆጠራ ወደ 306 መውረዱን ገልጠዋል። ቀይ ቀበሮም ቢሆን በአንድ ወቅት ቁጥሩ ከ130 በላይ ደርሶ የነበረ ቢሆነም ከዚያ በኋል ወደ 70 መውረዱን አስታውሰዋል።
ግጭቶችና ሌሎች ምክንያቶች ለዱር እንሣቱ መቀንስ ተጠቃሾች ናቸው
ለእንሣቱ ቁጥር መቀነስ ግጭቶች፣ የተሽከርካሪ ድምፆች፣ አደነና ሌሎችም ምክኛቶች እንደሚጠቀሱ አቶ ማሩ ተናግረዋል። እንስሣቱ ቀደም ሲል ከኖሩበት አካባቢም እየራቁና እየሸሹ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
የባለስልጣኑ የምርምርና ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፈቀደ ረጋሳ የእንሣቱን ህልውና ለመመለስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እቅድ ታቅዶ እንደሚሰራ ጠቁመው የአካባቢው ሠላም ወደነበረበት ካልተመለሰ ግን እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ከባድ እንደሚሆን አልክተዋል። የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በ1969 እ አ አ የተመሰረተ ሲሆን በውስጡ 5ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ 25 አጥቢ እንሣትና 16ቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ 130 አእዋፋትን በውስጡ የያዘ ነው።
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ