የዋና ኦዲተር ጋዜጣዊ መግለጫ
ዓርብ፣ ሰኔ 23 2015
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኦዲት ወይም የሒሳብ ምርመራ የሚመላከቱ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የበጀት አጠቃቀም ጉልህ ግድፈቶች እንዲታረሙ፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት እንዲወጣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ጠየቀ።ዋና ኦዲተር ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የአመቱ የሒሳብ ምርመራ ዘገባ ወደ ስድስት ዋና ዋና የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ የተፈቀደላቸውን በጀት መጠቀም ሲገባቸው ባለመጠቀማቸው 35 ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ ሳይውል መቅረቱን አመልክቶ ነበር።
የፌዴራል የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት የሒሳብ ምርመራ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ያስታወቀው ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት መከላከያን ጨምሮ ኦዲት እንዳይደረጉ በአዋጅ ያገዱ የደህንነት ተቋማት ደንባቸውን አሻሽለው ለተሻለ ግልጽነት ኦዲት መደረግ እንዲችሉ "ሕገ መንግሥት በደንብ ወይም መመሪያ ሊከለከል አይችልም" በሚል እንደተነገራቸው የፌዴራል ዋና ኤዲተር መሰረት ዳምጤ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ዋና ኦዲተሯ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስካሁን በጀታቸው በምክር ቤቱ ሲፀድቅ ያልተስተዋለባቸውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚሰሯቸው ፕሮጀክቶች መረጃ ከቀረበላቸው ኦዲት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር በዚሁ ሳምንት መጀመርያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የአመቱ የሒሳብ ምርመራ ዘገባው ዋና ዋና የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የተፈቀደላቸውን በጀት ባለመጠቀማቸው 35 ቢሊዮን ብር በበጀት ዓመቱ ጥቅም ላይ ሳይውል መቅረቱን አመልክቶ ነበር።
ተሰብስቦ ለመንግሥት ገቢ መደረግ የነበረበት ነገር ግን ሊፈፀም ያልቻለም 13.4 ቢሊዮን ብር ውዝፍ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ዕዳ ገቢ አለመደረጉን የጠቀሱት ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ግልጽ ወንጀል ነው ያሉት በዓመቱ የታየው የ1.3 ቢሊያን ጥሬ ብር ጉድለትን ጨምሮ ያለ አግባብ የሚባክንን የሕዝብ ኃብት ለመጠበቅ ተጠሪ የሆኑለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በጉዳዩ ላይ ሙያዊ አስተያየት የጠየቅናቸው የፋይናንስ ታክስ እና ማኔጅመንት መምህር እና አማካሪ ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ታደሰ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በላቀ መጠናከር እንዳለበት ገልፀው ተቋሙ በየ ዓመቱ በሚያወጣቸው ዝርዝር የሒሳብ ምርመራ የሚያሳያቸው ግድፈቶችን ተቀብሎ ፓርላማው ተጠያቂነት ማስፈን ይገባል ብለዋል።
የተፈቀደላቸውን በጀት በትክክል መጠቀም ተስኗቸው ከፍተኛ ኃብት ሲንከባለልባቸው ከቆዩት ተቋማት መካከል የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ፣ የጤና ሚኒስቴር ፣ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፣ትምህርት ሚኒስቴር እና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ይገኙበታል። ይህ ልምን ሊከሰት እንደሚችል ባለሙያውን ጠይቀናቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚሰሯቸው ፕሮጀክቶችን የገንዘብ ምንጭ ፣ የሒሳብ ፍሰት ምርመራ ጉዳይ በተመለከተ መረጃ ከቀረበላቸው ኦዲት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ዋና ኦዲተሯ አረጋግጠዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የፌዴራል የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት የሒሳብ ምርመራ እየተደረገላቸው አለመሆኑን አስታውቋል። መከላከያን ጨምሮ ኦዲት እንዳይደረጉ በደንብ ያገዱ የደህንነት ተቋማት ደንባቸውን አሻሽለው ለተሻለ ግልጽነት ኦዲት መደረግ እንዲችሉ "ሕገ መንግሥት በደንብ ወይም መመሪያ ሊከለከል አይችልም" በሚል እንደተነገራቸው የፌዴራል ዋና ኤዲተር መሰረት ዳምጤ በመግለጫ ተጠይቀው መልሰዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ