1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዋግኅምራ አካባቢ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 23 2015

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበሩ የጻግብጂና አበርገሌ ተፈናቃዮች በሙሉ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን በአማራ ክልል የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አስተወቀ። የተሰበረው ሁለተኛው የጥራሪ ድልድይ ባለመጠገኑ ርዳታ ለማድረስ መቸገሩን የብሔረሰብ አስተዳደሩ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

Äthiopien Zerstörung in Bahir Dar city
ምስል Waghemra district Communication office

የዋግኅምራ አካባቢ ተፈናቃዮች

This browser does not support the audio element.

 

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የነበሩ የጻግብጂና አበርገሌ ተፈናቃዮች በሙሉ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን በአማራ ክልል የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አስተወቀ።  የተሰበረው ሁለተኛው የጥራሪ ድልድይ ባለመጠገኑ ርዳታ ለማድረስ መቸገሩን የብሔረሰብ አስተዳደሩ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በበኩሉ ባለሙያዎች በሌሎች የጉዳት በደረሰባቸው የድልድይ ግንባታ ሥራዎች ላይ መሰማራታቸውን ጠቁሞ፣ ሆኖም በቅርቡ ሁለተኛው የጥራሪ ድልድይ ጥገና እንደሚደረግለት ገልጿል። 

በሰሜን ኢትዮጵያ ተቀስቅሶ በነበረው ጦርነት ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዱ ሲሆን በርካቶች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በደቡብ ጎንደር፣ በባሕር ዳር፣ እንደዚሁም በሌሎች የብሔረሰብ አስተዳደሩ ባሉ የተለያዩ ሰላማዊ ወረዳዎች ቆይተዋል። በተለይ የአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች ተፈናቅለው በሰቆጣ አካባቢ የቆዩ 70ሺህ የሚሆኑ ወገኖች ከሁለት ዓመት በለይ ከቀያቸው ርቀው ሰንብተዋል። ሰሞኑን የህወሓት ኃይሎች ከወረዳዎቹ አንዳንድ ቀበሌዎች  በሰላማዊ መንገድ በመልቀቃቸው፣ የሁለቱም ወረዳዎች ተፈናቃዮች ሙሉ በሙሉ በመመለሳቸው አሁን መጠለያ ጣቢያዎቹ ተፈናቃይ እንደሌለባቸው የብሔረሰብ አስተዳደሩ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

በዋግኅምራ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት ምስል Waghemra district Communication office

ሆኖም እንደ ዋና ችግር የሆነባቸው መንገዱ በትግራይ ክልል በኩል ተሻግሮ እንደገና ወደ ፃግብጂ ወረዳ የሚያሻግረው የጥራሪ ወንዝ ድልድይ ተሰብሮ መጠገን ባለመቻሉ ርዳታ ለማድረስ አለመቻሉ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።በዋግህምራ ሁለት ወረዳዎች «ሰሚ አጥተዋል» መባሉ

«ጻግብጂን ከአበርገሌ የሚለየው ጉዳይ የእርዳታ ጉዳይ ነው፣ የጥራሪ ድልድይ የተሰበረ በመሆኑ እርዳታ በቀላሉ ወደ ቦታው ማድረስ አልተቻለም፣ መንግስት በአስቸኳይ ድልድዩን እንዲጠግንልን እንጠይቃለን፣ አለዚያ ግን ርዳታ ማቅረብ አይቻልም» ሲሉም አክለዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድልድይና መሠረተልማት ግንባታዎች ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ዘላቀ በርካታ ባለሙያዎች በተለያዩ አካባቢዎች የተሰበሩ ድልድዮችን እየጠገኑ በመሆኑ የባለሙያ እጥረት አጋጥሞናል ብለዋ።፤ ሆኖም የተጀመሩ የሌሎች ድልድዮች ጥገና ሲጠናቀቅ በተጠቀሰው ቦታ የጥገናው ሥራ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።

በዋግኅምራ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት ገጽታምስል Waghemra district Communication office

«በቅርቡ ጉዳት በደረሰበት በጀማ ወንዝ ድልድይ፣ በደቡብም እንዲሁ አንድ ድልድይ፣ በሰሜንም የተሰበሩ ድልድዮች አሉ፣ ባለሙያዎቻችን  በእነዚህ ድልድዮች ጥገና ላይ ናቸው፣ የነዚህን ድልድዮች ጥገና እንዳጠናቀቅን ወደ ቦታው በመሄድ የጥገና ሥራውን እንሰራለን።»

ባለፉት ሳምንታት ወደ አበርገሌ ወረዳ ማዕከል ኔሯቅ ከተመለሱት ተፈናቃዮች መካከል ቀሲስ ኃይለጽዮን ደግፍ ሁሉም አገልግሎቶች ጀምረዋል እርዳታም እየመጣ ነው ሲሉ ለዶይቼ ቬሌ አስተያየት ሰጥተዋል። በአማራ ክልል አሁንም ከ600 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ዓለምነው መኮንን 

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW