1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዋግ ሕምራ ተፈናቃዮች ሮሮ

ረቡዕ፣ ሰኔ 26 2016

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ተፈናቅለው በወረዳው ማዕከል "ኒሯቅ” ከተማ የተጠለሉ አቤቱታ አቅራቢዎች ወደ ቀያችን እንዳንመለስ የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዴን) እንቅፋት ሆኖብናል አሉ ። የንቅናቄው ሊቀመንበር በበኩላቸው ስምታው ሐሰት ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል ።

Alamata Flüchtlingsunterkünfte Jara in Region Amhara
ምስል Alamata City Youth League

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ እንዳልቻሉ ተናግረዋል

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ተፈናቅለው በወረዳው ማዕከል "ኒሯቅ” ከተማ ተጠልለው ያሉ ተናቃዮች ወደ ቀያችን እንዳንመለስ የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዴን) እንቅፋት ሆኖብናል አሉ ። የንቅናቄው ሊቀመንበር በበኩላቸው ስምታው ሐሰት ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል ። 

ከሦስት ዓመት በፊት ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ በአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች ከመንግስት ጋር የትጥቅ ትግል ሲያደርግ በነበረው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ኃይሎች ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በአበርገሌ ወረዳ ማዕከል ኒሯቅ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች አሁንም ወደ አካባቢያቸው ሄደው ለመኖር የንቅናቄው ተዋጊዎች ችግር እየፈጠሩባቸው እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

አንድ ተፈናቃይ እንዳሉት ወደ ቀያቸው ተመልሰው ቢሄዱም የአዴን ኃይሎች በማስገደድ ስራ እያሰሯቸውና የገንዘብ ቅጣት እየጣሉባቸው በመሆኑ በርካታ ነዋሪዎች እንደገና ለመፈናቀል ተገድደዋል፡፡

የአዴን ኃይሎች አድርስታል ያሉትን ሲገልፁ፣ "ማህበረሰቡ በቅጣትና እሰሩና እየደበደቡ ህዝብ ተፈናቅሎ ወረዳው ማዕከል ኒሯቅ ነው ያለው፣ ርዳታ የሚሰጥም የለም ምንም የለም፣ አንድ ግለሰብ የራሱን ስራ እንዳይሰራ ለእነርሱ ታጣቂ አባል ለሆነው ማህበረሰቡን በማስገደድ ያሰራል፣ በሆነ አጋጣሚ በስራው ላይ ካልተገኘህ ደግሞ 5 ሺህ ብር ቅጣት ይጣልብሀል፣ በዚህ ምክንያት በርካታ ነዋሪ እየተፈናቀለ ነው፡፡” በሰላም ስምምነቱ ላይ የሁለቱ የአገው የፖለቲካ ድርጅቶች እሰጣ ገባ

ሌላ ተፈናቃይም የአዴን ኃይሎች ግርፋትና ማንገላታት እያደረሱ በመሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፣ አስፈላጊ የምግብ ግብዓቶችም ባለመኖራቸው ህብረተሰቡ በችግር ላይ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

የአማራ ክልል ተፈናቃዮ መጠለያምስል Alamata City Youth League

የርዳታ አህል ጥያቄን በተመለከተ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ የርዳታ እህል ግዢ  መፈጸሙን አመልክተው በቅርብ ስርጭት ይካሄዳል ብለዋል፡፡

"400 ኩንታል እህል ተገዝቷል፣ ከሁለት ቀናት በኋላ ይሰራጫል፣ክረምት ስለሆነ ያንን ይዘው ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እየመከርን ነው፣ ወቅቱ የግብርና ስራ የሚሰራበትና ክረምት በመሆኑ በሚቀጥለው ዓመት ለእርዳታ እህል እንዳዳረጉ እየመከርን ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይሉ ግርማይ የቀረበውን ስሞታ በተመለከተ "በጉዳዩ ላይ እየተወያየንበት ነው” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የአገው ድሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ኪሮስ ሮምሐ ታጣቂዎቻቸው ስነምግባር የታነፁ መሆናቸውንና ለህዝብ እንደሚሰሩ ጠቅሰው ስሞታውን አጣጥለውታል፡፡

"ከ2000 በላይ የመንግስት ሰራተኛ እኛ ጋ ነው እየሰራ ያለው፣ ከፖለቲካ ስራ ውጪ ያሉ መንግስታዊ ልሆኑ ድርጅቶች፣ የግብርና፣ የትምህርትና ሌሎች ባለሙያዎች አብረውን እየሰሩ ነው፣ ምንም እንከን ሳኖር ነው ስራቸውን እየሰሩ ያሉት፣ የተፈናቃዮች የራሳቸው ፍሎጎት ሊኖር ይችላል፣ እኛ ህዝብ እንዳይጎዳ ነው የምንሰራው ታጣቂዎቻችን በስነምግባር የታነፁ ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት፣  የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ባለፈው ታኅሳስ 2016 የደረሱበት የሰላም ስምምነት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የተጠየቁት አቶ ኪሮስ የስምምነቱ ትግበራ የዘገየ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ውስጥ እየተወያዩበት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የአማራ ክልል ተፈናቃዮ መጠለያምስል Alamata City Youth League

"...አሁንፌደራል መንግስትን ጨምሮ ውይይት ላይ ነው ያለነው ውይይቱ አንዱ የሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ትንሽ ዘግይቷል አሱ ይገመገማል፣ ወደ ተግባር እንዲገባ ማድረግ ነው፣ የአማራ ክልል መንግስት ወደ ተግባር አልገባም፣ በሱ ላይ እንወያያለን፣ ሌላው በሁለታችን በኩል ያሉ ሚሊሻዎች  ሶስት ዓመት ሙሉ ያላረሱ ስለሆነ መሳሪያውን እያስቀመጠ ሁሉም ወደየስራው እንዲገባ ነው የምንወያየው፡፡” ነው ያሉት አቶ ኪሮስ፡፡

የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች በትጥቅ ትግል ከመንግስት ጋር ሲዋጋ የነበረ ድርጅት ነው፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW