የውጪ ዜጎች የሚሳቀቁባት ደቡብ አፍሪቃ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 27 2018
«ትናንት ሌሊትም የኢትዮጵያውያንን ሱቆች ለመዝረፍ መጥተው ነበር፤ ነገሮች ከጊዜ ወደጊዜ እየከፉ መጥተዋል» ያለን ደቡብ አፍሪቃ ሊምፖፖ ግዛት ከቤተሰቡ ጋር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነው። እንዲያም ሆኖ ትናንት ዓርብ በአንዳንድ የከተማ አካባቢዎች መንቀሳቀስ እንደሚቻልና ለጊዜው ያን ያህል የጎላ የሚባል ችግር እንደሌለም ገልጸውልናል። በትናንሽ ከተሞች ግን አሁን ለጥቃት አሰፍስፈው እየተጠባበቁ እንደሆነም አመልክተዋል።
እሳቸው በሚኖሩባት ፕሪቶሪያ ከተማ ከሰሞኑ ዛሬ የተሻለ መረጋጋት መኖሩን የገለጹልን ላለፉት 21 ዓመታት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚገኙት ሌላኛው የፕሪቶሪያ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ልጆቻችን በመሳቀቅ ትምህርት ቤት መሄድ አልቻሉም በማለት የሚገኙበትን የሰቀቀን ኑሮ አጋርተውናል።
የኢትዮጵያውያን ሁኔታ
ደቡብ አፍሪቃ ዛሬ የውጭ ዜጎች በተለይም የሌላ አፍሪቃ ሀገር ዜጎች በነጻነት ቀና ብለው የሚሄዱባት ሀገር እንዳልሆነች በየዕለቱ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይም ሕጋዊ የመኖሪያ ሰነድ የሌላቸው አፍሪቃውያን ከጎርጎሪዮሳዊው ሰኔ 30 ቀን 2026 ዓም በፊት ሀገራቸውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ያስተላለፉት የእንቅስቃሴው አስተባባሪዎች አመጽ እንደሚቀሰቅሱ ተጠብቋል። አልቀረም፤ በአንዳንድ የደቡብ አፍሪቃ ከተሞች የውጪ ዜጎች እንዲወጡ ከጠየቀው የተቃውሞ ሰልፋቸው ጎንለጎን ዘረፋዎች መፈጸማቸው ተሰምቷል።
በማኅበራዊ መገናኛው ከሚዘዋወሩ ቪዲዎች ዱላየያዘ አንድ የሀገሬው ወጣት የአንድ ሱቅን መስታወት መትቶ ሲያረግፈው ውስጡም ገብቶ ሱቁ ውስጥ ገብቶም ዝጉ ውጡ እያለ በመጮህ ተከትሎት እንደታዘዘው በሩን ሊዘጋ ያለውን ኢትዮጵያዊ ድንገት ፊቱ ላይ በመምታት ሲጥለው ያሳያል። ድርጊቱ እዚያ የሚኖሩ ወገኖች በምን ዓይነት መሳቀቅ ውስጥ እንዳሉ በግልጽ ያመለክታል። በተለያዩ የደቡብ አፍሪቃ ግዛቶች የሚኖሩት ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን ከገለጹልም ያሉበትን የመሳቀቅ ኑሮ መረዳት ይቻላል።
ለ21 ዓመታት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ኖረዋል፤ እራሴን በራሴ ቀጥሬ አስተዳድራለሁ ሱቅ አለኝ አሉ። በፊት የሚያውቋት የደቡብ አፍሪቃ ይዞታ አሁን የለም። ከ10 ቀናት በፊት በተቀሰቀሰው የውጭ ዜጎች ይውጡልን ተቃውሞ ተዘርፈዋል። የዘረፋ ኢላማ የሆኑት ሁሉም አፍሪቃውያን የውጪ ዜጎች መሆናቸው የሚናገረው የሊምፖሎ ግዛት ነዋሪው ኢትዮጵያዊ ፈቃድ የሌላቸው ብዛ ሳይሆኖ ያላቸውም ይውጡልን እንደሚሉ ነው የገለጸው።
የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት በጸጥታ ኃይሎች አማካኝነት አመጹን ለመቆጣጠር እየሠራ መሆኑን ይናገራል። የሊምፖፖው ግዛት ነዋሪ ኢትዮጵያዊም እርዳታ ሲጠየቁ ለመተባበር እየሞከሩ መሆኑን ነው የነገረን። ሁኔታው ግን ከእነሱ አቅም በላይ ነው ባይ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ የምርጫ ጊዜ ተቃርቧልና መንግሥት በዚህም በኩል የቅስቀሳ ሥራ ስለሚኖርበት አፍሪቃውያን ስደተኞችን በሀገሪቱ ማየት ለማይፈልጉት ቡድኖች ወቅቱ አመቺ ሁኔታን መፍጠሩን አስተውሏል።
በውጭ ሀገር እንደመኖራቸው ጉዳያቸውን በኤምባሲ በኩል የሚያገኙት ድጋፍም ሆነ የመረጃ ቅብብል ይኖር ይሆን? ማለታችን አልቀረም። የጆሀንስበርጉ ነዋሪ ሀገር ቤት አለ ያሉት ክፍፍል ወደ ስደቱም ሀገር ተዛምቷል ነው ያሉት። የሊምፖፖው ነዋሪ በበኩሉ የሌሎች አፍሪቃ ሃገራት ለዜጎቻቸው እያደረጉ ያለውን በመጥቀስ ከእኛ በኩል ግን እስካሁን የሰማነው የለም ይላል።
የሀገሬውን ትኩረት የሚስቡ ያልተገቡ ድርጊቶች
በሌላ በኩል ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ኢትዮጵያውያንንም ለመጤ ጠሎች ጥቃት ያጋለጠው የእራሳችን ያልተገባ እንቅስቃሴ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ላለፉት 17 ዓመታት የቆየውና ማኅበረሰቡን ለማንቃት የሚያስችል ፕሮጀክት ነድፎ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የገለጸልን አቶ ገዛኸኝ ሱማሞ በሀገርኛ ቋንቋ ሲመለስ ከትውልድ ወደ ትውልድ ንቅናቄ የተሰኘ ተቋም መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው። አቶ ገዛኸኝ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ 17 ዓመታት ሲኖር ሁለቱን ዓመት ብቻ ነው በግል ሥራ ላይ የቆየው።
ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ መጤ ጠልነት በይፋ መገለጽ ከጀመረ ሰነበተ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ተሰዳጆች መበራከታቸውን ተከትሎ ነባሮቹ ላይ ሳይቀር ዘረፋና ጥቃት መደጋገሙ ይሰማል። ይህን ድርጊት አንዳንዶች የፖለቲካ ግፊት አለበት ሲሉ ሌሎች ከሥራ አጥነትና ወንጀል ጋር ያገናኙታል። አቶ ገዛኸኝ ግን ከመነሻው ሰላማዊ የነበረውን የደቡብ አፍሪቃውያን እና የመጤዎች ግንኙነት ያሻከረው ተሰዳጆቹ በሰው ሀገር በሚያሳዩት ትኩረትን የሚስብ ያልተገባ ድርጊት አማካኝነት ነው ባይ ነው።
በነገራችን ላይ ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ወገኖች የሚያስተናግዳቸው ሀገር ተወላጆች ዓይን እንዲጥሉባቸው የሚያደርጉ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ የሚለውን የሊምፖፖ ከተማ ነዋሪው ኢትዮጵያዊም እውነት ነው ሲል ያረጋግጣል።
መደረግ የሚገባው
ማኅበረሰቡን ለማንቃት ብዙ ጥረቶች ማድረጉን የገለጸልን አቶ ገዛኸኝ በዚህ መሀል በተለያዩ ጊዜያት ለጥቃት ተጋልጦ እንደነበር ይናገራል። በአንጻሩ በተገቢው መንገድ አንገታቸውን ደፍተው እየሠሩ ለሚኖሩበት ሀገርም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው የሚተርፉ እንዳሉም ይገልጻል። አሁን ያለው ችግር መፍትሄ እንዲያገኝ መሥራት ጉልህ ሚና መጫወት የሚገባው መንግሥት እንደሆነም ያመለክታሉ።
በዚህ መሀል ኑሮው የሰቀቀን የሆነባቸውና ሌላው ቀርቶ በሰው ሀገር ትውልት ማፍራታቸው በገጠማቸው ችግር ምክንያት ለጸጸት የዳረጋቸው አሉ ይላል አቶ ገዛኸኝ። አብዛኞቹ የመኖሪያ ሰነዳቸው አለመታደሱና ተያያዥ የኢምግሬሽን ጉዳዮች የመንግሥትን ትኩረት እንደሚፈልጉም አጽንኦት ሰጥቷል። የደቡብ አፍሪቃ የመጤ ጠል እንቅስቃሴ አብዛኞቹን የአፍሪቃ ሃገራት መንግሥታት አስቆጥቷል። ናይጀሪያ እና ኬንያን ጨምሮ በርካቶቹ ዜጎቻቸውን ለማውጣት እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ደክመው ያፈሩት ሀብት ለተዘረፈ ለወደመባቸውም ካሣ እንደሚጠይቁ እየገለጹ ነው። በዚህ መሀል እዚያ ያሉ ወገኖች ሰቀቀን ከፍቷል። የሊምፖፖ ግዛቱ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ በሀገር ቤትም ሆነ በመላው ዓለም ለሚገኙ ወገኖቹ መልእክት አለው። «የመጨረሻ ሊምፖፖ «እንግዲህ ኢትዮጵያውያን ሁሉም ጸሎተኛ ነውና በጣም የከፋ ደረጃ ውስጥ ስላለን በጸሎታቸው እንዲያስቡን።» የሚል።
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ