1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

በወቅታዊ ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ

ሐሙስ፣ ጥር 16 2016

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብፅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም ኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር ትሠራለች አለ። የሚኒስቴሩ ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ «የመግለጫ ጋጋታ ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረው ነገር የለም» ብለዋል።

 ፎቶ ከማኅደር፤ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር
የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብፅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም ኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር ትሠራለች ሲል ወቀሰ። ፎቶ ከማኅደር፤ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር

«የመግለጫ ጋጋታ ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረው ነገር የለም»

This browser does not support the audio element.


የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብፅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም ኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር ትሠራለች አለ። የሚኒስቴሩ ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ «የመግለጫ ጋጋታ ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረው ነገር የለም» ብለዋል። አክለውም በግብፅ በኩል ከዚህ በፊትም ከሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ ብዙ መግለጫ ይወጣ እንደነበረ በማስታወስ የግድቡ ግንባታ መቀጠሉን ገልጸው «በመግልጫ የሚሸበር፣ የሚረበሽ ሀገር እና ሕዝብ አይደለም» ብለዋል። የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ከቀናት በፊት የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ጥረት «ግዛትን በኃይል የመቆጣጠር ሙከራ» እንደሆነ ገልጸው በማንኛውም ሁኔታ ከሶማሊያ ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከ 25 ቀናት በፊት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት ያስችለኛል በሚል የፈረመችውን የመግባቢያ ስምምነት ሶማሊያ በሉዓላዊነቷ ላይ የተቃጣ አደጋ አድርጋ ስትወስደው፣ ግብፅደግሞ ግዛትን በኃይል የመቆጣጠር ሙከራ አድርጋ እንደምታየው በመሪዎቿ በኩል ገልጻለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ለዚህ ምላሽ ሲሰጡ ግብፅ ኢትዮጵያ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንዳትረጋጋ ትሠራለች በማለት ወቅሰዋል።  
የሶማሊላንድ መንግሥት ማንኛውንም የውጭ ጣልቃገብነት በጽኑ እንደሚቃወምና ግብፅ የያዘችውን አቋም እንደማይቀበል ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል። አካባቢያዊ ጉዳዮችን በውይይት እና በትብብር የመፍታት ቁርጠኝነት እንዳለውም አስታውቋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ይህንን ስምምነት ተከትሎ ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ወደ ሶማሊያ እንዳልገባች ገልጸዋል። ሶማሊያ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት እንደምትገነዘብ ያስታወቁት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ ሞሃመድ  መንግሥታቸው ከአዲስ አበባ ጋር ለመነጋገርና ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ያሳዩበትን አቋም አሳይተዋል። ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላም በውይይት ለመፍታት ሁልጊዜም ዝግጁ መሆኗን ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገልፀዋል። 

ኢትዮጵያ ወታደራዊ እና የንግድ እንቅስቃሴ ለማከናወን የሚያስችላትን የባሕር በር የሚያስገኝላት ነው የተባለው ስምምነት ከተፈረመ ከአንድ ወር በኋላ ሂደቱ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረሱ በስምምነቱ ወቅት ተገልጾ ነበር። የእስካሁን ሂደቱ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የተጠየቁት አምባሳደር መለስ ዓለም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። 
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያ በራስ ገዟ ሶማሊላንድ ውስጥ ወታደራዊ የጦር ሠፈር እና (ኮሜርሻል ማሪታይም) የባሕር መርከብ ሠፈር እንዲኖራት ይፈቅዳል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW