1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የግል ተቋማት

ሰለሞን ሙጬ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 14 2017

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ግዢ እና ሽያጭ እንዲያከናውኑ ፈቃድ ከሰጣቸው ባንክ ያልሆኑ የግል ተቋማት መካከል የተወሰኑት ሥራ ጀምረዋል።ስድስት ግለሰቦች በ180 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ድርሻ ያቋቋሙት "ኢትዮ ፎሬክስ" ሥራ ከጀመረበት ከአንድ ወር ተኩል ጊዜ ወዲህ ስድስት መቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለደንበኞች ማቅረቡን ገልጿል።

Äthiopien Addis Abeba | EthioForex | Echtzeit-Wechselkurse in Äthiopien
ምስል Solomon Muchie/DW

የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የግል ተቋማት

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ግዢ እና ሽያጭ እንዲያከናውኑ ፈቃድ ከሰጣቸው ባንክ ያልሆኑ የግል ተቋማት መካከል የተወሰኑት ሥራ ጀምረዋል።ስድስት ግለሰቦች በ180 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ድርሻ ያቋቋሙት "ኢትዮ ፎሬክስ" የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ሥራ ከጀመረበት ከአንድ ወር ተኩል ጊዜ ወዲህ ስድስት መቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለደንበኞች ማቅረቡን ገልጿል።በየ እለቱ አቅርቦትና ፍላጎትን መሠረት አድርጎ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ እንደሚወስን ያስታወቀው ድርጅቱ ዛሬ አርብ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ130 ብር ገዝቶ በ133 ብር ሲሸጥ በአንፃሩ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ119 ብር እየገዛ በ121 ብር እየሸጠ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግብይት በገበያ እንዲመራ ካደረገ ወዲህ በመደበኛ እና በትይዩ ገበያ መካከል የነበረው ልዩነት ጉልህ በሚባል ደረጃ የጠበበ ሲሆን፤ ባንክ ያልሆኑት የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ልዩነቱን የበለጠ ያጠባሉ ተብሎ እምነት ተጥሎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ .ም "የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትን ተደራሽነትን ለማስፋፋትና የሀገሪቱን በሚል የውጭ ምንዛሪ ቢሮ መክፈት የሚያስችል ፈቃድ ለግል ድርጅቶች ሰጥቷል ምስል Solomon Muchie/DW

የግል የውጭ ምንዛሪ ተቋማት ከባንኮች ምን የተሻለ አማራጭ ይዘዋል?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ .ም "የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትን ተደራሽነትን ለማስፋፋትና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማዳበር ያግዛሉ" በሚል የውጭ ምንዛሪ ቢሮ መክፈት የሚያስችል ፈቃድ ከሰጣቸው ድርጅቶች አንዱ፣ ስድስት ግለሰቦች ተሰባስበው በ180 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ድርሻ ያቋቋሙት "ኢትዮ ፎሬክስ" አንደኛው ነው። የተቋሙ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ከዶቼ ቬለ የቀረበላቸውን ድርጅቶቹ ከውጭ ምንዛሪ አስተዳደር እና ፍሰት አንፃር ከባንኮች የሚለዩት በምንድን ነው የሚለውን በማብራራት ይጀምራሉ።

"ቀላል አገልግሎት ለደንበኞቻችን የምናቀርብበት ዕድል ከእነሱ ይለየናል። በተለይ እኛ ጋር የሚመጡ ደንበኞች በስልክ ይደውላሉ፣ አዘጋጅታችሁ ጠብቁን ይላሉ፣ ይዘው የሚሄዱበትን እድል እያመቻቸን ነው። እና ነገሮች የሚሄዱበት አካሄድ የእኛ በጣም ቀላል እና ተገማችም ነው"

የእለታዊ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን እንዴት ይሠራል?

እነዚህ የግል የውጭ ምንዛሪ ተቋማት ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ሀገር ጥሬ ገንዘቦችን በመግዛትና በመሸጥ እንዲሁም ከባንኮች ጋር በመቀናጀት ለወጪ እና ገቢ ንግድ የሚውል የውጭ ምንዛሪ የማመቻቸት ኃላፊነት ይወጣሉ ተብሎ በመንግሥት ታሳቢ ተደርጓል። ተቋማቱ የሚያካሂዱት "የውጭ ምንዛሪ ሽያጭም ሆነ ግዢ ወዲያውኑ የሚፈፀም ብቻ ይሆናልም" ተብሏል። በዛሬው እለት የባንኮች እና የእነዚህ ተቋማት የውጭ ምንዛሪ ግብይት አንድ የአሜሪካ ዶላር በምን ሁኔታ እንደሚገበያይም አቶ ኤፍሬምን ጠይቀናቸዋል።

"ለነፃ ገበያ ስለተተወ ለገቢ ንግድም፣ ለውጭ ምንዛሪም የሚፈልገው የሚያገኝበትን እና የተሻለ የሚያዋጣው እድል ተፈጥሯል። እኛ በየ ቀኑ ዋጋ የምንወስነው አቅርቦትና ፍላጎቱን በማየት ነው። ዛሬ አሁን እኛ የምንገዛበት 130 አካባቢ ነው። በንኮች 24ትም፣ 25ትም እያየሁ ነው። የአምስት እና የስድስት ብር ልዩነት እየመጣ ነው። አሻሻጣችንም ላይ ተመሳሳይ ነው" ብለዋል።

አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ፤የኢትዮ ፎሬክስ የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ምስል Solomon Muchie/DW

የገንዘብ ባለሙያዎች እና የተጠቃሚዎች አስተያየት

በጉዳዩ ላይ ቀደም ብለን ያነጋገርናቸው የገንዘብ ባለሙያ "የወጭ ንግድ እንዲያድግ ከተፈለገ የሀገሪቱ የሰለም ጉዳይ መፈታት እንዳለበት፣ የንግድ ሚዛን ጉድለት የሚስተካከለውም ይህንን መሠረት በማድረግ በሚስፋፋ የሀገር ውስጥ ምርት መሆኑን" በመግለጽ የውጭ ምንዛሪ በገበያ መመራቱ ብቻ ዘላቂ ችግር ፈቺ እንዳልሆነ አንድ የገንዘብ ባለሙዬ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል። ዛሬ የውጭ ሀገር ገንዘብ ሲሸጡ ያገኘኋቸው አንድ ደንበኛ ስለዚሁ አገልግሎት ተከታዩን ብለዋል።"ዛሬ ለመጀመርያ ጊዜ ነው ወደ ዉጭ ምንዛሪ ቢሮ የመጣሁት። እና የባንኩን ምንዛሪ እና የዚህ የፎሬክስ ምንዛሪውን ስመለከተው በአንድ ዶላር በትንሹ ከ አሥር ብር የማያንስ ልዩነት አይቸበታለሁ። ስለዚህ እኛ ሻጮች ተጠቃሚ ነን" ሲሉ መልሰዋል።

የግል የውጭ ምንዛሪ ተቋማቱ ጥቁር ገበያን ያዳክሙት ይሆን?

ሌላኛው የገንዘብ ባለሙያ የተቋማቱ ወደ መስኩ መግባት "የገንዘብ እጥበትን ለመቀነስ፣ የትይዩ ገበያውን እንቅስቃሴ ለማዳከም እና የውጭ ምንዛሪ ግብይቱን ተወዳዳሪ ለማድረግ ያግዛሉ" ይላሉ። የኢትዮ ፎሬክስ የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ በበኩላቸው ተከታዩን ብለዋል።

"ሕጋዊ ተግባር ኖሮት ግን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የማይችለው እና ጥቁር ገበያ ውስጥ ይሄድ የነበረው በነፃ ገበያ ስለተባለ፣ ባንኮችም ፍላጎት እና አቅርቦትን ተከትለው ስለሚያቀርቡ ሌላ ታክስ የመሰወር ፍላጎት ከሌላቸው በስተቀር፣ ምንም እዚህ ጥቁር ገበያ ውስጥ የሚያመጣቸው ነገር የለም"። 

በ180 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ድርሻ ያቋቋሙት "ኢትዮ ፎሬክስ" የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ሥራ ከጀመረበት ከአንድ ወር ተኩል ጊዜ ወዲህ ስድስት መቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለደንበኞች ማቅረቡን ገልጿል።ምስል Solomon Muchie/DW

ይህ ዘርፍ ወደ ፊት የት ይደርስ ይሆን ?

አስፈላጊ ከሆነ ድርጅታቸው ወደ አነስተኛ የገንዘብ ተቋም ወይም ወደ ባንክ ሊያድግና ዘርፉን ሊጠናከር እንደሚችል የሚገልፁት ኃላፉው፣ የካፒታል ገበያ እያደገ ከመጣም የቦንድ ሽያጭ ውስጥ እየገባን ሥራውን ልናስፋፋው እንችላለን የሚል ተስፋ አላቸው። አሁን 45 ሚሊየን ብር መነሻ ሀብት ማስመዝገብ ብቻ የሚጠይቀው ይህ የሥራ ዘርፍ ወደፊት የትምህርት ዝግጅት፣ የአሥተዳደር ብቃት እና ሌሎችም መስፈርቶች ሊጠይቅ እንደሚችልና ውድድር በዝቶበት ለደንበኞች ሰፊ እድል ሊፈጥር እንደሚችል የአንድ ወር ከ 15 ቀን የሥራ ጅምራቸውን አዝማሚያ በመጥቀስ አስረድተዋል።

"በዚህ አንድ ወር ከ 15 ቀን ውስጥ 650 ሺህ ዶላር ለደንበኞቻችን አቅርበናል። ቢያንስ ከ 400 በላይ ተገልጋዮች ከእኛ አገልግሎቱን ወስደዋል - በመሸጥ ማለት ነው። የገዛናቸው ደግሞ ከዚያ በላይ ናቸው። እና ጥሩ ነው ልምምዱ"የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መንግሥት ያደረገውን የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ተከትሎ በትይዩ ገበያ እና በባንክ መካከል የነበረው የምንዛሪ ተመን ከ 3 በመቶ በታች መውረዱንና ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ በንግድ በንኮች ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ማደጉን መግለፁ ይታወሳል።

ሰለሞን ሙጨ
ታምራት ዲንሳ
ፀሀይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW