የውጭ ዜጎችን የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት የሚያደርገው ረቂቅ ሕግ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች
ረቡዕ፣ ግንቦት 13 2017
የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበት ረቂቅ ሕግ "የዜጎችን የመሬት ይዞታ የማግኘትና የመጠቀም መብት በማያጣብብ መልኩ" እንደሚከናወን በረቂቁ ላይ ተጠቅሷል። ሕጉ የውጭ ዜጎች የውጭ ካፒታል በኢትዮጵያ ሥራ ላይ እንዲያውሉ ለማበረታት፣ የቤት ልማት እና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማነቃቃት፣ እየሰፋ የመጣ የተባለውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ሚዛን በተገቢ መንገድ ለማስጠበቅ እንደሚያግዝም ታምኖበታል።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ መሠረት የተወሰኑ ሀገራት ዜጎች ወይም ዜግነት የሌላቸው የተባሉ የውጭ ሀገር ሰዎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ እንዳይሆኑ ሊከለክል ይችላልም ተብሎ ተቀምጧል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 "የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥት እና የሕዝብ ብቻ ነው" ይላል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ "መንግሥት ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወሰን ክፍያ የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል" ሲልም ደንግጓል።
የሕግ ባለሙያው አቶ አምደ ገብርኤል አድማሱ የውጭ ዜጎች በዚህ ረቂቅ ሕግ "የኪራይ ውል" የሚያገኙ መሆኑን ጠቅሰው ኢኮኖሚን ከማነቃቃት አንፃር በበጎ ተመልክተውታል። ጉዳዩ "ትኩረት የሚሰጠው እና ውይይት የሚፈልግ ነው" ቢሉም ከሕገ መንግሥት ጋር ግን የሚጋጭ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል።"የመሬት ባለቤት መሆን እና የኪራይ መብት ባለቤት መሆን ያለያያሉ"
በረቂቁ ላይ የተለያዩ ባለሙያዎች አስተያየት
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ተወያይቶ የወሰነውና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት የተወያየበት ይህ ረቂቅ አዋጅከሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን እንዳይሆን ሥጋት ስለመኖሩ፣ የቤት ዋጋን እንዳያንረው፣ የካፒታል ማሸሽን እንዳያበረታታ፣ ለታክስ ስወራ፣ ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ለብሔራዊ ደኅንነት ችግር እንዳይፈጥር የሚሉ ሥጋቶች ተነስተውበታል። የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሽዋፈራሁ ሽታሁንም ይህንኑ ሥጋት ከዚህ በፊት ለዶቼ ቬለ ገልፀው ነበር።
"ከእኛ የተሻለ የውድድር አቅም አላቸው። ስለዚህ ኢኮኖሚያችን ውጠውት የሀገር ባለቤትነት ስሜት ላይ ሌላ ጥያቄ ያስከትላል"
የኢኮኖሚ አማካሪ እና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ዳዊት ታደሰ በዛ ያሉ የምክር ቤት አባላት እንዳሳዩት ድጋፍ ለረቂቅ ሕጉ አወንታዊ ምልከታ ይዘዋል።
"አሁን ጊዜው ይመስላል። ምክንያቱም ብዙ ነገር ከፍተናል"
የሕግ ባለሙያው አቶ አምደ ገብርኤል አድማሱ ሕጉ ሊገጥመው የሚችል የአፈፃፀም ችግር አይኖርም ማለት እንዳልሆነና ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
"አዋጁን ተከትለው የሚወጡት መመርያ እና ደንቦች አሉ። በዚያ ሂደት ውስጥ ዜጎች ይበደላሉ። የሀገር ዜጎች እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚሆኑበት አጋጣሚዎች አሉ"
ለዚህ መብት የተቀመጡ መስፈርቶች ምንድን ናቸው?
የውጭ ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ የመሬት ባለይዞታ ለመሆን የሊዝ ሙሉ ዋጋውን ጨምሮ ለአንድ መኖሪያ ቤት ግንባታ ወይም ግዢ አነስተኛ 150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር መመደብ አለበት በሚልም ተደንግጓል። ከዚህ በኋላ ፈቃድ የሚያገኘው የውጭ ዜጋ ራሱና ቤተሰቡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖሩ እንዲሁም እንዲመላለሱ መብት ያገኛሉ ይላል። ነገር ግን እነዚህ የውጭ ዜጎች ባለ ይዞታ የማይሆኑባቸው "ልዩ ቦታዎች ወይም የድንበር አካባቢዎች" ይኖራሉ ተብሎም ተቀምጧል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጁ በዋናነት በከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በሌሎችም ተመርምሮ ዳግም ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ መርቶታል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ