1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለትግራይ ክልላዊ መንግሥት ወቀሳ መልስ ሰጠ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 13 2012

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ለሥራ ጉብኝት ወደ ትግራይ ክልል ጉዞ ሊያደርጉ የነበሩ የቻይና የሻንሺ ግዛት ልዑካን አባላት በፌደራል መንግሥት ትዕዛዝ ወደ ክልሉ እንዳይጓዙ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ እገዳ ተደርጎባቸዋል ለሚለው የትግራይ ክልል መንግሥት ቅሬታ ከሱ ዕውቅና ውጪ መሆኑን አስታወቀ::

Äthiopien Markos Tekle, Staatsminister für Außenpolitik
ምስል DW/S. Muchie

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ

This browser does not support the audio element.

ሰሞኑን ለሥራ ጉብኝት ወደ ትግራይ ክልል ጉዞ ሊያደርጉ የነበሩ የቻይና የሻንሺ ግዛት ልዑካን አባላት በፌደራል መንግሥት ትዕዛዝ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይጓዙ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ እገዳ ተደርጎባቸዋል የሚለው የትግራይ ክልል መንግሥት ቅሬታ የመገናኛ ብዙሃን ዓበይት የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ቆይቷል። ዶይቼ ቨለም "DW" የተፈጠረውን ክስተት ለማጣራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃላፊዎችን አነጋግሯል:: ለመሆኑ የልዑካን ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በፌደራል መንግስቱ ዕውቅና እና አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ነው ? ለሚለው ጥያቄ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚስትር ሚኒስትር ዴ´ ኤታ አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ የፌደራል መንግስቱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤዥያ እና ፓስፊቅ አገራት ጉዳዮች መምሪያ እና ቻይና ፔኪንግ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሚስዮን አማካኝነት ከወራት በላይ ከግዛቲቱ ሃላፊዎች ጋር የደብዳቤ ልውውጥ እና ውይይት አድርጎ ለትግራይ ክልልም በደብዳቤ አሳውቆ በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን አረጋግጠውልናል::

በቻይና የሻንሺ ግዛት ምክትል ሊቀመንበር የሚመራው ስድስት ዓባላት ያሉት ይኸው የቻይና የሻንሺ ግዛት ልዑካን ቡድን ከትግራይ ክልላዊ መንግስት ጋር  በልማት እና አቅም ግንባታ ዙሪያ ልዩ ልዩ የትብብር የመግባቢያ ሰነዶችንም እንዲፈራረሙ የውጭ ጉዳይ ሚስቴር መስሪያ ቤቱ ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱንም አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ገልፀዋል:: ይሁንና ከፌደራል መንግስቱ ጋር የነበራቸውን የስራ ቆይታ አጠናቀው ወደ መቀለ በአውሮፕላን ለመጓዝ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሱ በኋላ ግን ወደ ትግራይ እንዳይጓዙ ተከልክለዋል ሲል የክልሉ መንግሥት ቅሬታውን አሰምቷል:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴ ኤታው አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ግን ችግሩ የተከሰተው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳይሆን ከሱ ዕውቅና ውጭ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የጥበቃ  አካላት ዘንድ የመረጃ መናበብ ክፍተት የፈጠረው ችግር ይመስላል :: ጉዳዩን ከኤርፖርት የጥበቃ አካላት እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በመነጋገር የምናጣራው ይሆናል ሲሉ ገልፀዋል:: ችግሩ ከተከሰተ በኋላም የቻይናው የልዑካን ቡድን በትዕግስት እንዲጠብቅ በማድረግ እና ከትግራይ ክልል መስተዳድር ሃላፊዎች ጋር በመነጋገር በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የትግራይ ክልል የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አብረሃም ተከስተ የመግባቢያ ሰነዱን አዲስ አበባ ድረስ መተው እንዲፈራረሙ በማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሃላፊነቱን በአግባቡ ተወጥቷል ሲሉም ዶክተር ማርቆስ ገልፀዋል::
የትግራይ ክልል መስተዳደር ሃላፊዎች ከለውጡ በኋላ በአገሪቱ ተፈጥረው ለቆዩ የመብት ጥሰት እና ልዩ ልዩ ችግሮች መንግሥት ሕወሃትን ብቻ ተጠያቂ እያደረገ ነው የብልፅግና ፓርቲ ውህደትን በተመለከተም ከፌደራል መንግሥቱ አመራሮች ጋር በተፈጠረ የፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ክልሉን በምጣኔ ሃብት ለማሽመድመድ የውጭ አገራት ልዑካን የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የተቋማት ሃላፊዎች የውጭ አገር ዜጎች እና ምሁራን ወደ ትግራይ ክልል እንዳይመጡ ልዩ ልዩ ጫና እየተደረገ ይገኛል ሲሉ በክልሉ መገናኛ ብዙሃን እና ማህበራዊ ሚድያዎች ጭምር ተደጋጋሚ ስሞታ እያቀረቡ ይገኛሉ:: ከሶስት ወራት በፊትም የኤዥያ አምባሳደሮች የልዑካን ቡድን አባላት ወደ ትግራይ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤት ሃላፊዎች እንዲታገድ ተደርጓል ተብሎ በልዩ ልዩ ማህበራዊ የመገናኛ አውታሮች የተሰራጨው መረጃስ ምን ያህል ዕውነትነት አለው ስንል እንዲያብራሩልን ሚኒስት ዴ´ኤታውን  አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ጠይቀናቸው ነበር:: አምባሳደሩ በሰጡት ምላሽ በየትኛውም አገር እንደሚደረገው የውጭ አምባሳደሮች ወደ ፌደራል ክልሎች ለመሄድ ሲፍልጉ ህጋዊ አግባብን ተከትለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ማሳወቅ ቢኖርባቸውም የኤዥያ አምባሳደሮች የልዑካን ቡድን አባላት ግን ወደ ትግራይ ክልል ከሄዱ በኋላ መልዕክት መላካቸውን ይፋ አድርገዋል::
ያም ቢሆን በወቅቱ የልዑክ ቡድኑ ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳያሳውቅ ወደ ትግራይ ክልል ከሄደ በኋላ መረጃ መላኩ ጥያቄ ቢያስነሳም ጉብኝታቸውን ግን በተሳካ ሁኔታ አካሂደው መመለሳቸውንም ዶክተር ማቆስ አስረድተዋል::
የፌደራል መንግሥቱን ስልጣን እና ተግባራት በሚደነግገው በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 51/4/ መሰረት የውጭ ግንኙነትን ስትራቴጂን መንደፍ ፖሊሲ ማውጣውና እና ማስፈፀም የሚኒስቴር መስሪያቤቱ ስልጣን እና ሃላፊነት መሆኑን የገለፁት  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሁሉንም ክልሎች በዕኩል ዓይን እንደሚያይ እና ከውጭ አገራት ጋርም ህጋዊ በሆነ መልኩ አስፈላጊው የልማት እና የኢንቨስትመንት ትብብር እንዲካሂዱ አስፈላጊውን ሁኔታ ሁሉ እንደሚያመቻች ለዶይቼ ቨለ "DW" ጨምረው አብራርተዋል::
እንዳልካቸው ፈቃደ
ሸዋዬ ለገሠ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW