የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ
ሐሙስ፣ መጋቢት 21 2015ኢትዮጵያ ወደተሟላ ሰላም እንድትገባ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ "በቁርጠኝነት እየደገፈ ነው" ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።ሚኒስቴሩ የሰላም ስምምነት የፈረሙት የፌዴራል መንግሥት እና የሕወሓት አመራሮች ተቀራርቦ ለመሥራት እያሳዩት ነው ያለው ዝግጁነት "የመተማመን መንፈስ እየፈጠሩ" ስለመሆኑ ማሳያ ነው ሲል ገልጿል።በሌላ በኩል የኮሞሮስ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር አዛሊ ኡስማኒ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና ከአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጋር በልዩ ልዩ ጉዳዮች ለመምከር ትናንት ምሽት አዲስ አበባ ገብተዋል ተብሏል። የኢትዮጵያ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ግንኙነት "ጥሩ የሚባል ነው" ያለው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአረብ ሊግ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ያለማቋረጥ እያራመደ ያለው አቋም ግን አፍራሽ እንደሆነበት አስታውቋል። ሥራው ከተጀመረ አንድ አመት በሞላው በሳውዲ አረቢያ በስቃይና መከራ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የማስመለስ ተግባር እስካሁን 125 ሺህ ኢትዮጵያውያንን መመለስ ተችሏል ያለው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሌላ በኩል በመቶዎች የሚቆጠሩ ኡጋንዳዊያን "የምፅዐት ቀንን ሽሽት" የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ደቡብ ኢትዮጵያ ያንጋቶም ወረዳ ውስጥ እየኖሩ መሆኑን ማረጋገጡን ገልጿል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ የጀመረችው የሰላም ስምምነት ፍሪያማ እንዲሆን ፣ መልሶ ግንባታ እና ካሳ ለተጎጅዎች ሁሉ እንዲደርስ፣ ብሔራዊ እርቅ እውን እንዲሆን እና ተጠያቂነት በትክክል ተፈፃሚ እንዲደረግ ዓለም አቀፍ በሚባሉት መንግሥታት፣ ድርጅቶችና ተቋማት ዘንድ ፍላጎት መኖሩን አይተናል ብለዋል።
በእነዚሁ አካላት ዘንድ "የበለጠ ለማገዝ እና ለመደገፍ ትልቅ ፍላጎት ያለ መሆኑን ተገንዝበናልም" ሲሉ ተስተዋለ ያሉትን በጎ ነገር ገልፀዋል።የሰላም ስምምነቱን አስመልክተው "ትልቅ ሥራ ተሰርቷል" ያሉት አምባሳደር መለስ ሆኖም ብዙ ሥራዎች የሚቀሩ መሆኑንም ተናግረዋል ።"ከሰላም አንፃር ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ኢትዮጵያ ወደተሟላ ሰላም የምታደርገውን ጉዞ በቁርጠኝነት እየደገፈ እንደሆነ መግለጽ እንፈልጋለን"። ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከአፍሪካ ሕብረት አመራሮች ጋር በልዩ ልዩ ጉዳዮች ይመክራሉ የተባሉት በደቡብ ምስራቅ አፍሪካ በሦስት ደሴቶች የተዋቀረችው የኮሞሮስ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር አዲስ አበባ ውስጥ መሆናቸውን በአዎንታ ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ዘገባ ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ጦርነት ሁሉም ተፋላሚ ኃይላት የጦር ወንጀል ፈፅመዋል ማለቱን መንግሥታቸው " ፖለቲካዊ እንደምታ የሌለው" አድግጎ መመልከቱን አብራርተዋል። የኢትዮጵያን እና የመካከካከኛው ምስራቅ አገራትን ግንኙነት መልክ የተጠየቁት ቃል ዐቀባዩ "ጥሩ የሚባል ነው" ሲሉ አጭር መልስ ሰጥተዋል።የመካከለኛው ምሥራቅ ከአፍሪካ ቀንድ ተለይቶ የማይታይበት የላቀ ትስስር ያለበት ዘመን ላይ መደረሱንና ከአካባቢው አረብ አገራት ጠንካራ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ትስስር መኖሩን ገልፀዋል።ሆኖም የአረብ ሊግ አፍራሽ እና ተቀባይነት የሌለው ያሉትን አቋም ከሕዳሴ ግድብ ጋር አያይዞ አቋሙን በመግለጫ ማውጣት መቀጠሉን እና ሰመነኛ የግብጽ የመገናኛ ብዙኃን የሚያወጧቸው መግለጫዎች የተለመዱ እና "ዓመታዊ ናቸው" ብለዋል። ምክንያት ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሕግጋት የማትገዛ አገር ናት የሚል ስእል ለመስጠት የሚሞከር ሂደት መሆኑን ጠቀስ በማድረግ የመግለጫዎች መብዛት የግድቡ አራተኛው ዙር የውኃ ሙሌት መቃረቡን ተከትሎ ስለመሆኑ ጠቆም አድርገው አልፈዋል። ከሳውዲ አረቢያ ዜጎችን የማስመለሱን የአንድ አመት ሥራ ውጤት በቁጥር ገልፀዋል።"ከሳውዲ አረቢያ ዜጎቻችንን ማውጣት የጀመርነው የዛሬ ዓመት ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ 125 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገር ውስጥ መመለስ ተችሏል"።
ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም "በአካባቢያችን የምፅዐት ቀን ይኖራል ፣ ሞት መፈናቀል ይኖራል" ብለው ሥጋት ያደረባቸው ያሏቸውና በትክክል ቁጥራቸውን ያልገለጿቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዩጋንዳዊያን ከምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍለ አገር ተነስተው ወደ ኢትዮጵያ አቆራርጠው በመግባት በደቡብ ክልል ያንጋቶም ወረዳ እየኔሩ መሆናቸውን አረግልግጠዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር