የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ እንቅስቃሴ
ረቡዕ፣ ኅዳር 12 2016
የኢትዮጵያየውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ የሦስት ወራት ሥራዎቹን ሲያቀርብ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም የውስጥ ችግሮች መሻሻል አለባቸው ብሏል ። በሌላ በኩል ሱዳን በወረራ የያዘችውን የኢትዮጵያ መሬት እስካሁን እንደወረረችው መሆኑ እና «የሁኔታ ለውጥ» አለመኖሩ ተገልጿል። መንግሥት ይህንን ጉዳይ ሱዳን ከገባችበት ጦርነት ከወጣች በኋላ በድርድር ለመፍታት በይደር እንደያዘውም በዚሁ ወቅት ተነግሯል። ኢትዮጵያ የእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭትን በተመለከተ ስላላት አቋም፤ ስለዲያስፓራ ማኅበረሰብ እንዲሁም የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ን በተመለከተ ማብራሪያ ተሰጥቷል ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አልተገኙም
ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በቀር አብዛኞቹ የመሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት እና የመሥሪያ ቤቱ የሦስት ወራት የሥራ አፈፃፀም በቀረበበት ስብሰባ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሥራ እያደገ ስለመሆኑ፣ በተለይ ከአውሮጳ ሀገራትና ሕብረት ጋር ሻክረው የነበሩ ግንኙነቶች ስለመሻሻላቸው ተገልጿል።
ያም ሆኖ ግን ምእራባዊያን የሚያቀርባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ተለዋዋጭነት ለግንኙነት መሻሻል አሁንም ችግር መሆኑ ተነግሯል። በፓርላማው የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በዛ ያሉ ጥያቄዎችን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ያቀረቡ ሲሆን ሱዳን በወረራ የያዘችው የኢትዮጵያ መሬት ጉዳይ አንዱ ነው። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሩካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ፍሥኃ ሻውል "የሁኔታ ለውጥ" የለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በእስራኤል - ፍልስጤም ጦርነት የመንግሥት አቋም
አምባሳደር ፍሥኃ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ለኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት ቀና መሆኑንም በማሳያ ጭምር ገልፀዋል። መንግሥት በእስራኤል - ፍልስጤም ጦርነት ነባር አቋሙን ይዞ እንደሚቀጥል በሚኒስቴሩ የአለም አቀፍ ድርጅቶች ዳይሬክተር ጀነራል ልዑልሰገድ ታደሰ ተናግረዋል።
በውጪ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የአቋም መዋዠቅ እንደሚያሳይ እና የኢትዮጵያን ክብር የሚጎዳ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን በተመለከተ ለቀረበ ጥያቄ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሞሃመድ እንድሪስ ምላሽ ሰጥተዋል።
"በአለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይሄነው የሚባል መሠረታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል እና የዲያስፖራውን ማህበረሰብ ሰንጥቆ እኛ እና እናንተ የሚል ጎራ ሊፈጥር የሚችል እንቅስቅልሴ" የለም በማለት። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለውጭ ግንኙነት ሥራ መሳለጥ የውስጥ ሰላም የግድ መሆኑን በማስታወስ ምክር ቤቱ ሰላም እንዲመጣ እንዲያግዝ ጠይቀዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር