የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምላሽ
ቅዳሜ፣ መስከረም 18 2017ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላት አላማ "የጋራ እድገት እና ብልጽግና ነው" ሲሉ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በ79ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተናገሩ።
"የኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ስምምነት በሶማሊያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፣ የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ "መሠረተ ቢስ ውንጀላ" መሰንዘሩንና ያንንም እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአፍሪካ ቀንድ ክልል ውጭ ያሉ ተዋናዮች "ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶችን" እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው አለም አቀፉ ማህበረሰብ በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ የተገኘ ያሉትን ውጤት ከመጥፋት ለመከላከል ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቀዋል።//
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ 15 ደቂቃ ግድም በወሰደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ንግግራቸው አለም አቀፍ፣ አሕጉራዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮችን ዳሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ከአቅሙ በላይ እየሆኑ ያሉ ጥቂት የማይባሉ ፈተናዎችን እንዲጋፈጥ እንደሚያስፈልግ ያስታወሱት ሚኒስትሩ ድርጅቱ በሁሉም አባል ሀገራቱ መካከል ገለልተኛነት፣ ነፃነት፣ ብቃት እና ታማኝነትን በማሳየት ሚናውን በልኩ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
አለም የተጋረጠበት የጦር መሣሪያ እሽቅድድም፣ አስከፊ ያሉት ድህነት፣ ኢ-ፍትሐዊነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት እና የዘላቂ ልማትን በሚመለከት የተደቀኑ ሥጋቶንም በማሳያነት አንስተዋል። የአፍሪካ በድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት ሊኖራት የሚገባ ውክልናም በንግግራቸው የተዳሰሱ ዐቢይ ነጥቦች መካከል ናቸው።
ኢትዮጵያ ሶማሊያን ከአሸባሪ ቡድኖች ቁጥጥር ሥር ለማውጣት በተደረገው ጥረት የከፈለችውን መስዋዕትነት የሶማሊያ መንግሥት እንደሚገነዘብ እምነታቸው መሆኑን ገልፀው፣ ኢትዮጵያ ከራስ ገዝ ሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የባሕር በር ማግኛ የመግባቢያ ስምምነትን ተከትሎ የተነሳው ውዝግብ ያስከተለውን ውንጀላ ሀገራቸው እንደማትቀበለው ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ስምምነት በሶማሊያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። አላማችን በቀጣናው ውስጥ የጋራ እድገት እና ብልጽግና ነው። ተመሳሳይ ስምምነቶች በሌሎች ሀገሮች የተፈረሙ ሲሆን የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት የውስጥ የፖለቲካ ውጥረቶችን ለመሸፈን ከማሰብ በቀር ጠላትነት የሚቀሰቅስበት ምንም ምክንያት የለም። ስለዚህ በሀገሬ ላይ የቀረበውን መሠረተ ቢስ ውንጀላ አልቀበልም። የኢትዮጵያ ስም ከየትኛውም ውንጀላዎች ጋር ፈጽሞ ሊያያዝ አይችልም"።
ግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ውስጥ ዘልቃ የመግባቷ ሀቅ በተለይ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ በማቅረብ በግላጭ መንፀባረቅ ጀምሯል። ሶማሊያ ውስጥ የሚደረግ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ የትኛውም እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደማይኖረው አስቀድመው ያስታወቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንኑ ገዳይ በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይም አስተጋብተውታል።
"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአፍሪካ ቀንድ ክልል ውጭ ያሉ ተዋናዮች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እነዚህን ጥረቶች ያውካል። ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ካላት ቁርጠኝነት ወደኋላ አትመለስም። ስለዚህ እነዚህ ተዋናዮች የሚፈጽሙትን ግድየለሽ ተግባር በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እንጠይቃለን። በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከእነዚህ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶች ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ተገንዝቦ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ የተገኘውን ውጤት ከመጥፋት ለመከላከል ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ እንጠይቃለን"።
ቱርክ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብቦ ለመፍታት የጀመረችው ጥረት የቀጠለ ቢሆንም ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል ለማለት ገና ነው። ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ግብጽ፣ የአረብ ሊግ እና የሶማሊያ ወዳጅ ነን ያሉ ሀገራት የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የግድ ሊከበር የተገባው ስለመሆኑ አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል። ይህ ሁኔታ የፖለቲካ እና የተፈጥሮ ችግሮች መነሃሪያ ለሆነው የአፍሪካ ቀንድ ተጨማሪ አደጋ ሳቢ መሆኑን ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ ገልፀዋል።
"በቀጣናው ግን ወደፊት በጣም አስቸጋሪ የሆነ ሽኩቻ ፣ጭራሽ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ቀውስ ውስጥ የሚገባ ቀጣና ነው የሚሆነው"
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር