1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ መግለጫ በወቅታዊ ጉዳዮች

ዓርብ፣ ሚያዝያ 20 2015

ሱዳን ውስጥ በአገሪቱ መሪዎች መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ኢትዮጵያዊያንን ከጉዳት የሚከላከል፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ የፀጥታ እና የሰብዓዊ ቀውስ ችግር ቢኖር እንዴት ይፈታ የሚለውን የሚመልስ እንዲሁም የሌሎች ሃገራት ዜጎችን የማስተላለፍ ሥራ የሚያከናውን ግብረ ኃይል መቋቋሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

Ethiopia Ministry of Foreign affairs podium | Addis Abeba, Ethiopia
ምስል Solomon Muchie/DW

የውጭ ጉዳይ መግለጫ

This browser does not support the audio element.

ሱዳን ውስጥ በአገሪቱ መሪዎች መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ኢትዮጵያዊያንን ከጉዳት የሚከላከል፣ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ የፀጥታ እና የሰብዓዊ ቀውስ ችግር ቢኖር እንዴት ይፈታ የሚለውን የሚመልስ እንዲሁም የሌሎች ሃገራት ዜጎችን የማስተላለፍ ሥራ የሚያከናውን ግብረ ኃይል መቋቋሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የሱዳን ሰላምና መረጋጋት እጦት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ጭምር ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስካሁን ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን፣ አውሮጳውያን እና አሜሪካዊያን ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የሚኒስቴሩ ቃል ዐቀባይ ተናግረዋል። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ( IOM ) ግን እስካሁን 3500 የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በድንበር በኩል መግባታቸውን አስታውቋል። 
የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያዊያንን ከሱዳን ጦርነት ለመታደግ ፣ በኢትዮጵያ ድንበር በኩል የሚወጡ የሌሎች አገሮች ዜጎች ምን አይነት ድጋፍ ይደረግላቸው? የቆንስላ አገልግሎት እንዴት ይሰጥ? የሚለውን መልስ እንዲሰጥ ታስቦ ግብረኃይል መቋቋሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።
«በኢትዮጵያ በኩል ካርቱም ያለው ኤምባሲም አገልግሎት ይሰጣል፣ ገዳሪፍ ያለውም ኤምባሲ  (ቆንስላ) አገልግሎት ይሰጣል። ከፀጥታ አንፃር እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ከመቋረጣቸው አንፃር የተወሰኑ ዲፕሎማቶቻችንን ወደ ገዳሪፍ አምጥተናል።»
ኢትዮጵያዉያኑም ሆነ የሌሎች ሃገራት ዜጎች በኢትዮጵያ ድንበር ከሱዳን መውጣት መጀመራቸውን የጠቀሱት መለስ «ሥራው ከአቅርቦት አንፃር ፈታኝ» መሆኑን አስታውቀዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ከሱዳናውያን ጎን መሆኗን፣ የሱዳናውያንን እንባ የማበስ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላት ጎረቤት እንደሆነችም ጠቅሰዋል። ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ተመልሰዋል ለሚለው ጥያቄ ግን በግልጽ ምላሽ አልሰጡም። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ( IOM ) በበኩሉ እስካሁን 3500 የተለያዩ አገራት ዜጎች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በድንበር በኩል መግባታቸውን አስታውቋል።
«የሱዳን ሰላም እና መረጋጋት እጦት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውም ብዙ ትርጉም አለው።» ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።
እንዲያም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግሥት ኦነግ ሸኔ ብሎ በአሸባሪ ድርጅትነት ከፈረጀው አካል ጋር ጀመረው ስለተባለው የድርድር ሂደት የተጠየቁት ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ኢትዮጵያ ከታጣቂ ቡድኖች ጋር የምታደርገውን ድርድር የአፍሪቃ ሕብረት መቀመጫ ከሆነችው አዲስ አበባ ውጪ የምታደርግበት የተለየ ግብ ስለመኖር አለመኖሩም ከዶቼ ቬለ ተጠይቀው ነበር። ኢትዮጵያ ከውስጥ ታጣቂዎች ጋር የምታደርገውን የሰላም ድርድር ተጠያቂነት ሳይኖር ለአፍሪቃዊ ችግር አፍሪቃዊ መፍትሔ መስጠት በሚል ላልተገባ ጥቅም እያዋለች አይደለም ወይ ተብለውም ተጠይቀዋል። አምባሳደር መለስ ዓለም «የተለየ ግብ ለማሳካት አይደለም» ብለዋል።
የአውሮጳ ሕብረት ሰኞ ዕለት ከተሰበሰበ በኋላ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ቀንድ ያላትን ስልታዊ ጠቀሜታ እና አስፈላጊነት የበለጠ ያሰመረ መሆኑንና ጉዳዩም በበጎ የሚታይ ነው ተብሏል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW