1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጥያቄ አልተመለሰም

ሐሙስ፣ ግንቦት 29 2016

የዎላይታ ዞን ላለፉት ሦስት ወራት ያለደሞዝ የቆዩ የመንግሥት ሠራተኞች አሁን ላይ የሃምሳ በመቶ ክፍያ ብቻ እየተፈጸመላቸው እንደሚገኝ ለዶቼ ቬለ ተናገሩ ።የክልሉ መንግሥት በበኩሉ ደሞዝ ባለመክፈል የመንግሥት ሠራተኛውን እያስራቡ ይገኛሉ “ ባላቸው የዞንና የወረዳ የሥራ ሃላፊዎች ላይ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል

የመንግሥት ሠራተኞች አሁንም ድረስ ዉዝፍ ደሞዛቸዉ እንዳልተከፈላቸዉ አስታዉቀዋል
የዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች ያልተከፈለ ደሞዝ እንዲከፈላቸዉ በመጠየቅ ካደረጉት የአደባባይ ሠልፍ አንዱምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጥያቄ አልተመለሰም

This browser does not support the audio element.

 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ላለፉት ሦስት ወራት ያለደሞዝ የቆዩ የመንግሥት ሠራተኞች አሁን ላይ የሃምሳ በመቶ ክፍያ ብቻ እየተፈጸመላቸው እንደሚገኝ ለዶቼ ቬለ  ተናገሩ  ፡፡

የክልሉ መንግሥት በበኩሉ  “ ደሞዝ ባለመክፈል የመንግሥት ሠራተኛውን እያስራቡ ይገኛሉ “ ባላቸው የዞንና የወረዳ የሥራ ሃላፊዎች ላይ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል  ፡፡

ለወረዳዎቹ በቂ የበጀት ሀብት ፍሰት ማስተላለፉን የጠቀሰው የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ በበኩሉ አንዳንድ የወረዳ ሃላፊዎች ለሠራተኛው ግማሽ ደሞዝ በመክፍል ቀሪውን ለሌላ የወጭ ርዕስ ይጠቀሙበታል ሲል ወቅሷል ፡፡

 

ያልተመለሰው የሠራተኞች የደሞዝ ጥያቄ በዎላይታ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች የመንግሥት ሠራተኞች ከደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ቅሬታቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ ፡፡ የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄው ከሌሎች አካባቢዎች ይልቅ በዎላይታ ዞን ጎልቶ ይስተዋላል ፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ የዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች የሦስት ወራት ደሞዝ እንዲከፈላቸው ከባለፈው የመጋቢት ወር ጀምሮ ጥያቄያቸውን በሠልፍ ጭምር ሲያቀርቡ ቆይተዋል ፡፡ ከያዝነው ሳምንት መግቢያ አንስቶ ግን የክልሉ መንግሥት ጥቄያቸውን ተቀብሎ ምላሽ መስጠት መጀመሩን አስታውቋል ፡፡ ሠራተኞቹ ግን “ ምላሹ አጥጋቢ ያልሆነ ፣ የሠራተኛውን ሥነ ልቦናም የጎዳ ነው “ ይላሉ ፡፡

የደሞዝ ቅሸባ 

በዎላይታ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እየተከፈለ ይገኛል የተባለው ደሞዝ በዞኑ መንግሥት ሠራተኞች ዘንድ አጥጋቢ ምላሽ ተደርጎ አልተወሰደም ፡፡  ወርሃዊ ደሞዛቸው ባልተለመደ ሁኔታ ተቆራርጦ  እየተከፈላቸው እንደሚገኝ ለዶቼ ቬለ የተናገሩ ሦስት የዎላይታ ሶዶ ዙሪያ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች ጥያቄው ተመልሷ ለማለት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል ፡፡

በአብዛኞቹ ወረዳዎች እየተከፈለ የሚገኘው የደሞዛቸውን ከ40 እስከ 50 ፐርሰት ያህል መሆኑን የጠቀሱት ሠራተኞቹ “ ደሞዛችን እንደተፈለገ ተቆረጦ እየቀረ ነው ፡፡ አከፋፈሉ የፋይናንስንም ሆኖ የመንግሥት ሠራተኛ አስተዳደር መመሪያን የሚጻረር ነው ፡፡ ድርጊቱ የደሞዝ ቅሸባ እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም ፡፡ ምክንያቱም እንዲህ አይነት የደሞዝ አከፋፈል በትኛውም ዓለም ሰምተን አናውቅም “ ብለዋል ፡፡

የፋይናንስ ቢሮው የመፍትሄ አቅጣጫ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሠራተኞች ደሞዝ ጉዳይ አሁንም የመነጋገሪያ እንደሆነ ቀጥሏል ፡፡ የክልሉ  ፋይናንስ ቢሮ ዎላይታ ሶዶ ላይ እያካሄደ በሚገኘው የፋይናንስ ባለሙያዎች ሥልጠናዊ ውይይት ላይ ይኼው የደሞዝ ጉዳይ በሠራተኞቹ ተነስቷል፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙት የቢሮው ሃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ  ቢሯቸው ለወረዳዎች በቂ የበጀት ሀብት እያስተላለፈ እንደሚገኝ አሃዛዊ መረጃዎችን በመጥቀስ አብራርተዋል  ፡፡

የሰራተኞቹ ተደጋጋሚ ሰልፍ ከተደረገባቸዉ አካባቢዎች አንዱ የዎላይታ ሶዶ ከተማ ነዉምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ዎላይታን ጨምሮ በክልሉ አንዳንድ ወረዳዎች የፋይናንስ ቁጥጥር / ኦዲት / መደረጉን የጠቀሱት ሃላፊው “ ወደ ወረዳዎች የሚወርደው የበጀት ሀብት የመንግስት ሠራተኛ ደመወዝ ለመክፈል የሚያስችል ነው ፡፡ ይሁንአንጂ አንዳንድ ወረዳዎች ከአሠራር ውጭ ደሞዝ በፐርሰንት እየከፈሉ ሠራተኛው እንዲራብ ፣ በክልሉ ላይም እንዲያማርር እያደረጉ ይገኛሉ ፡፡ ክልሉ በቀጣይ በእነኝህ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ እርምጃ የሚወስድ ይሆናል ፡፡ በተጨማሪም ለሽብረቃ የሚወጡ አላስፈላጊ ወጪዎችን ለመገደብ የሚያስችል የወጭ ቅነሳ መመሪያም ተግባራዊ ይደረጋል “ ብለዋል ፡፡

በደቡብ ክልል ዎላይታ ዞን የመንግሥት  ሠራተኞች ደሞዝ አልተከፈለንም በሚል ጥያቄያቸውን በሠልፍ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወቃል ፡፡ አሁን ላይ ዞኑ ከአፈር ማዳበሪያ ዕዳና ከአስተዳደራዊ መዋቅር መስፋት ጋር ተያይዞ የበጀት አለመጣጣም መከሰቱ ይነገራል ፡፡  ዞኑ የበጀት ክፈተቱን ለመሙላት ከቀጣዩ የ2017 ዓም በጀት ብድር በመጠየቅ የደሞዝ ክፍያውን እየፈጸመ እንደሚገኝ የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ ቀደምሲል ለዶቼ ቬለ መግለጻቸው አይዘነጋም ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW