1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኅብረተ ሰብሰሜን አሜሪካ

የዐማራ ዲያስፖራ ዓለም አቀፍ ጉባኤ

ታሪኩ ኃይሉ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 14 2017

በዐማራ ክልል ለሚታየው አጣዳፊ ሰብዓዊ ቀውስና በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ነው ያለውን ጉዳት ለመታደግ፣ አስቸኳይ ድጋፍ የማሰባሰብ ዘመቻ እንደሚያካሂድ የዐማራ ዲያስፖራ አለም አቀፍ ፎረም አስታወቀ። ከ30 በላይ የዐማራ ማኀበረሰብ ድርጅቶች፣የዐማራ ማኀበረሰብ ተወላጆች፣ምሁራንና አንቂዎች የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በስፕሪንግፊልድ ከተማ ተካኼዷል።

ተፈናቃዮች
በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች በመካሔድ ላይ ከሚገኘው ግጭት ባሻገር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ እና ዕርዳታ የሚሹ ተፈናቃዮች ይገኛሉ። ምስል Alemnew Mekonen/DW

የዐማራ ዲያስፖራ ዓለም አቀፍ ጉባኤ

This browser does not support the audio element.

እንደጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር ከጥቅምት 19 እስከ 20 የተካኼደው የዐማራ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን፣የጉባኤው አዘጋጆች  ከሆኑት አንዱ አቶ ብርሃነመስቀል ነጋ ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል።

አቶ ብርሃነ መስቀል፤ የጉባኤው አጠቃላይ ዓላማ ምን እንደነበር ጠይቀናቸውም እንደሚከተለው መልሰዋል።

"ውጭ ያለው የዐማራ ማኀበረሰብ፣በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ሃገሮችና ክፍለ አህጉሮች ያለውን የሚያቅፍ ነው፤ዓላማው እንግዲህ፣ በመጀመሪያ ደረጃ በዐማራው ማኀበረሰብ መኻከል ያለው ኅብረት እንዴት ነው የሚጠናከረው በዚህ በሚደረገው ትግል ውስጥ ተባብሮ የሚቆምበትን በሁሉም ደረጃ ያለውን እሱን ማየት ነው።በኅብረት ቆሞ ደግሞ፣ ውጭ ያለው ማኀበረሰብ የሚያደርገውን ዕርዳታ፣እሱን ደግሞ በተለያየ በዲፕሎማሲም በሚዲያም በተለያዩ ለተጎዱ ወገኖቻችንም ጉዳት ለደረሰባቸው  የሚደርሰውንም ሰብዓዊ ዕርዳታ በማፋጠን፣የዐለም አቀፍ ማኀበረሰቡም እንዲያየው በማድረግ፣በተለያዩ ሁኔታ እነሱንም ለማየት ነው ዋናው ዓላማው እንግዲህ።"

የዐማራ ክልል ግጭት መስስኤና የወደፊቱ ሁኔታ-ዉይይት

በዐማራ ዲያስፖራ ግሎባል ፎረም አዘጋጅ ኮሚቴ አማካይነት በቀረቡ ሰነዶች ላይ ውይይት መደረጉን የገለጹት አቶ ብርሃነ መስቀል፣ የአሜሪካ ህሕግ አውጪ ምክር ቤት /ኮንግረስ/ዕጩዎችም በጉባዔው ላይ ተገኝተው የዐሳብ ልውውጥ መደረጉን አመልክተዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በአጭር፣መካከለኛና ረጅም ጊዜያት በዲያስፖራው መወሰድ የሚገባቸውን እርምጃዎችና አፈጻጸማቸውን በተመለከተ፣የተለያየ ነጥቦችን ያካተተ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።

አቶ ብርሀነመስቀል በአማራ ክልል እየተካሔደ ባለው ግጭት “በየቀኑ ነው ትምህርት ቤቶች የሚፈርሱት፣ ሆስፒታሎች ክሊኒኮች የሚፈርሱት የልማት ተቋማት ሁሉ እየፈራረሱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ እየተፈናቀሉ ነው” በማለት ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል። ምስል Efratana Gidm woreda Communication

የዐማራ አጠቃላይ ጉባዔ በአትላንታ

በዚሁ መግለጫቸው ከደረሱባቸው ውሳኔዎች መኻከልም፣ በመላው ዓለም የተለያዩ አገራት የሚገኙ የዐማራ ማኀበራት፣ልዩነታቸውን በውይይት እና የህልውና ትግሉን ባስቀደመ ባሉት ህዝባዊ ተጠያቂነት መንፈስ ተባብረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

አስቸኳይ ድጋፍ የማሰባሰብ ዘመቻ

የወቅቱን አጣዳፊ ሰብዓዊ ቀውስና በዐማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰነው ያሉትን ጉዳት ለመታደግ፣አስቸኳይ በሆነና ቅንጅታዊ አሰራርና ተጠያቂነትን ባረጋገጠ ሁኔታ፣ ድጋፍ የማሰባሰብ ዘመቻ እንዲካሄድ ተስማምተዋል።

ለክልሉ ሕዝብ አስቸኳይ ዕርዳታ ለማሰባሰብ የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ አቶ ብርሃነመስቀል የሚከተለውን ተናግረዋል።

"በዕርዳታ አቅርቦት በኩል እንደዚሁ ያሉትን ክፍተቶች አስተካክሎ አንድ ወጥ አሰራር ለመፍጠር፣ እንግዲህ መቼም የደረሰው ጥፋት በዐማራው ሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊ ነው። በየቀኑ ነው ትምህርት ቤቶች የሚፈርሱት፣ ሆስፒታሎች ክሊኒኮች የሚፈርሱት የልማት ተቋማት ሁሉ እየፈራረሱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ እየተፈናቀሉ ነው ያለው።ዕርዳታ ያስፈልጋል እሱን በተቻለ እንዴት ነው የምንደግፈው እኛ የምናደርገው ምንድነው የሚል ነው።"

ዲፕሎማሲን በተመለከተ፣በቅርቡ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እና ኮንግረስ ምርጫዎች፣ የዐማራው ማኀበረሰብ ለትግሉ ድጋፍ ለማስገኘት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ፣ ጉባዔው ጥሪ ማቅረቡን አቶ ብርሃነመስቀል ጠቁመዋል።

እንደጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር ከጥቅምት 19 እስከ 20 የተካኼደው የዐማራ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን፣የጉባኤው አዘጋጆች  ከሆኑት አንዱ አቶ ብርሃነመስቀል ነጋ ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል።ምስል Tariku Hailu/DW

በዐማራ ክልል የሚካሄደውን ጦርነት አስመልክቶ የሳንታ ባርባራ አዉራጃ ውሳኔ

ይህን ጉባዔ በተመለከተ፣ ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ክፍል ስልክ ደውለን አስተያየት ለማግኘት ጥረት ብናደርግም፣ልናገኛቸው ባለመቻላችን ለጊዜው አልተሳካም።

ህግ የማስከበር እርምጃ

ይሁንና በዐማራ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆምና በክልሉ ሰላም ለማስፈን፣ የክልሉ መንግስትና የሃገር መከላከያ ሰራዊት በጋራ በመሆን ህግ የማስከበር ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ባለፈው መስከረም ወር መግለጻቸው አይዘነጋም።

የክልሉ መንግስትና መከላከያ ሰራዊት በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በክልሉ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ግጭት በክልሉ ሕዝብ ላይ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን አስታውቀዋል።

አሁን በክልሉ የተደረገ ያለው ህግ የማስከበር ስራ፣ በክልሉ ብሎም በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለመ መሆኑም ተመልክቷል።

 ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣የተለያዩ አማራጮች በመንግስት በኩል ቢቀርቡም፣ የተደረጉት  ጥረቶች  ውጤት አለማስገኘታቸው ነው በዚሁ ጊዜ የተገለጸው።

ታሪኩ ኃይሉ 
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW