የዐቢይ መልዕክት ለትግራይ፣ ሐዘን የፈጠረው ግድያና የአሜሪካ ርዳታ መቋረጥ ሥጋት ለኢትዮጵያ
ሐሙስ፣ ጥር 29 2017
ጠቅላይሚ ኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለትግራይ ሕዝብ እና ልሒቃን ያስተላለፉት መልዕክት ባለፉት ቀናት መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ሲጀምር የትግራይን ሕዝብ ታሪክ እና በኢትዮጵያ ውስጥ የተጫወተውን ሚና የሚያወድስ ነው። ዐቢይ በመልዕክታቸው የትግራይ ሕዝብ “ካለፈው ቁስል ሳያገግም አሁንም በጦርነት ሥጋት እና ሽብር ላይ” እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የትግራይ ልሒቃን በመካከላቸው ያለውን መከፋፈል “በመግባባት እና የትግራይን ሕዝብ አንድነት በሚያረጋግጥ መንገድ” ሊፈቱት እንደሚገባ ምክር ለግሰዋል። ልሒቃኑ “ከፌድራል መንግሥት ጋር ያላቸውን ልዩነት በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ እንዲሆኑ” ጥሪ አቅርበዋል።
ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች አንዷ የሆኑት ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር የዐቢይ መልዕክት “ልዝብ የሚመስል ግን ደግሞ በውስጡ ተጠንቀቁ የሚል ማስፈራርያ ያለው ስለሆነ ወደ ጦርነት ያስገባል የሚል ሥጋት በሕዝብ ዘንድ ፈጥሯል” ሲሉ ተናግረዋል።
ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በጥቅምት 2013 የተቀሰቀሰው ዐቢይ የሚመሩት ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት እንዲህ በመግለጫ ሲወነጃጀሉ ቆይተው በመሆኑ አሁንም የሁለቱን አካሔድ በጥርጣሬ የሚመለከቱ ጥቂት አይደሉም።
በፌድራል መንግሥቱ እና በትግራይ ክልል መካከል ያለው ግንኙነት በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ በሚገኝበት ወቅት በትግርኛ ቋንቋ የተላለፈውን መልዕክት ያነበቡ ከዚህ ቀደም ዐቢይ የተናገሩትን እና የሠሩትን እያስታወሱ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ እንደሚስማሙ የገለጹት ናሖም አምባው “ይህን ሁሉ እንደሚያምኑበት እጠራጠራለሁ። የትግራይ ቀዳሚ ችግር የተፈናቀሉ ሰዎቻችን እና ቤቶቻቸው ናቸው። ይህ ካልተፈታ እዚህ የጠቀሷቸው በሙሉ ትርጉም አልባ ናቸው” ብለዋል።
ስምዖን ኃይለ “ለሰላም ቁርጠኛ ከሆኑ የፕሪቶሪያውን ውል ተግባራዊ በማድረግ ከቤታቸው ያባረሯቸውን ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ይመልሱ” የሚል አስተያየት ጽፈዋል። ተወልደ ገብረማርያም “ሕገ-መንግስቱ ይከበር። የትግራይ ሉአላዊ ግዛት ይመለስ፤ አከራካሪ የሚባሉ ቦታዎች ካሉም በማስረጃና ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ አገባብ እልባት” እንዲበጅለት ሐሳብ ሰንዝረዋል።
እንደ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች “ተፈናቃይ ወገኖች ደህንነታቸዉ ተጠብቆ ይመለሱ” የሚሉት ተወልደ “በትግራይ ሕጋዊ እና ቋሚ መንግሥት ይመረጥ፤ ትግራይ አገር መሥራች ሆና ሳለ እንደ ባዕድ በሀገሯ ምክር ቤት ተወካይ የሌላት ሆናለች። ስለዚ በአፋጣኝ ብሔሩን የሚወክሉ ዜጎች በፌደራል ምክር ቤት ይኑሯት” ብለዋል።
መንገሻ ወልደሚካኤል “የአንድ ቀን ስህተት ያለ ዘጠኝ ወር አይመዘዝ ይባላል። ጦርነቱ ያስከተለው ድቀት ነገሮች በቀላሉ ወደ ነበሩበት እንዳማይመለሱ እና ተጨማሪ አዳዲስ ተግዳሮት ሊፈጥር ይችላል። የክልሉ ፖለቲከኞች እና የፌድራል መንግሥቱ ለአጠቃላይ የሀገሪቱ ሰላም ሲባል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል” ሲሉ መክረዋል።
“የመሀይም ብልጠት፣ የፈሪ ሰው በቀል
በሽታን ታቅፎ፤ መድሐኒትን መንቀል”
የምትል ባለ አንድ ስንኝ ግጥም ዮናስ አባተ በፌስቡክ ጽፈው በባሕር ዳር ከተማ የተገደሉት ዶክተር አንዱዓለም ዳኜ በሰላም እንዲያርፉ ተመኝተዋል። ግድያውን ያወገዘው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበር “የትምህርት ተቋማት ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ዓላማ እንደሌላቸው እየታወቀ በመምህራን ላይ ኢ ሰብአዊ ድርጊት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ሕጋዊ ተጠያቂነት አለመኖሩ ሀዘናችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል” ብሏል።
አለሙ ቦጋለ “የተገዛ ዶክትሬት የሚኖርባት፤ የተማረ ዶክተር የሚገደልባት ያልታደለች ሀገር” ሲሉ ኢትዮጵያ የምትገኝበት መራር እውነታ ተችተዋል። ዳግም “አቤት ይቺ አገር ስንት ንፁሀን ነው ምትበላው?” ሲሉ ይጠይቃሉ። “ከስመኘው እስከ አምባቸው፣ከጄኔራል ሰዓረ እስከ አርቲስት ሀጫሉ፣ ሰሞኑን ደግሞ ሕጻን ሲምቦ እና ዶክተር አንዷለም…ብቻ እንደ ሕዝብ ያለንበት ሁኔታ መኖር አያስመኝም” እያሉ ይብሰለሰላሉ።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባሰራጨው መረጃ መሠረት ዶክተር አንዷለም በዩኒቨርሲቲው ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጠቅላላ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት እና የጉበት፣ የቆሽት እና የሃሞት መስመር ሰብ ስፔሻሊት ሐኪም ነበሩ። በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር የነበሩት የ37 ዓመቱ ዶክተር አንዷለም ዳኘ በባሕር ዳር ከተማ በጥይት ተመተው የተገደሉት ባለፈው ቅዳሜ ነው።
ታላቋ ኢትዮጵያ የሚል ስም የሚጠቀሙ ግለሰብ “አንዳች ፋይዳ የሌለው ግጭት በአማራ ክልል ከተከሰተ ጀምሮ ስንቱ ምሁር ተገደለ? ስንቱ ክልሉን ለቆ ወጣ? ስንቱ ተዘርፈ? ስንቱ ድህነት ውስጥ ገባ?” ሲሉ በፌስቡክ ጽፈዋል።
“ስንት ሰው ነው የተገደለው?”
ሲሉ የሚጠይቁት ሐውለት አሕመድ “ዶክተር አንዱዓለምን የመሠለ ብቁ ሐኪም ለማፍራት፤ Super genius የሆነ ሕፃን መወለድ አለበት፣ በትምህርት፣ በጥበብና በዲሲፕሊን ቀጥተው የሚያሳደጉ ወላጆችና አያቶች እንዲሁም ደጋፊ ዘመዶች መኖር አለባቸው፤ 'በርታ' እያለ ሲያበረታታ የነበረ የቅርብ ማኅበረሰብ (society) ያስፈልጋል” ሲሉ መልስ ይሰጣሉ።
ሐውለት “ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሰብ ስፔሻሊቲ ትምህርትና ሥልጠና ድረስ እውቀትና አቅማቸውን አንጠፍጥፈው የሚሰጡ ስመ-ጥር መምሕራንና የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች ያስፈልጋሉ፤ መጠነ-ሰፊ ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ኢነርጂና የሙያ ፍቅር ኢንቨስት ሊደረግበት ግድ ነው” ሲሉ በግል የፌስቡክ ገጻቸው ጽፈዋል። “የእርሱን የሕክምና እገዛ የሚሹ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን፤ የእውቀት ሽግግሩ በእጅጉ የሚያስፈልጋቸው የአሁንና የወደፊት የሕክምና ተማሪዎችን…
ይህን ሁሉ ስናስብ
“አንድ ሐኪም ሳይሆን አንድ ማኅበረሰብ ተገድሏል” በማለት መራሩ ሐቅ ዋጋው ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል። “ፍትህ ግን በጥሪ ትገኛለች?” በማለት የጠየቁት ሐውለት “አፈር እየበላች ስለመሠለኝ ነው” በማለት መልሰዋል።
አብርሀም አማረ “ደግሞ እኮ እንደብዙዎቻችን ሀኪም ብቻ አልነበረም። የተለየ ሰው፤ የተለየ ሀኪም ነው። ሙያ፣ እዉቀት፣ ሥነ-ምግባር ሁሉም የታደለዉ፤ ሲያዩት የሚያሳሳ ሰው ነበር። በሱ ደረጃ ያሉ ሌሎች ሀኪሞች ቀዶ ህክምና ይዘው ገብተው ኬዙ ካስቸገራቸዉ ድረስልን የሚሉት፤ ሁሉም በዕዉቀቱ በክህሎቱ የሚመኩበት ሀኪም ነበር” የሚል ሐሳብ ሲጨምሩላቸው ሐውለት አሕመድ “ወይኔ” እያሉ የበለጠ ይንገበገባሉ።
የአሜሪካ ርዳታ መቋረጥ በኢትዮጵያ እና በዜጎቿ ላይ ምን ዐይነት ተጽዕኖ ያሳድራል?
አሜሪካ ሰብአዊ ርዳታ ስታቆም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች፤ ድርቅ እና የከባቢ አየር ለውጥን የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ ችግሮች የሚፈታተኗቸው ኢትዮጵያውያን ተረጂዎች ምን ይሆናሉ የሚለው ጉዳይ እያነጋገረ ነው። የ78 ዓመቱ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ሲመለሱ ያቆሙት ሰብአዊ ርዳታን ብቻ አይደለም። ለጤና አገልግሎት ማጠናከሪያ፣ ለዴሞክራሲ እና የሥርዓት ማሻሻያዎች የሚሰጡ ድጋፎችም ተጽዕኖ አርፎባቸዋል። ጉዳዩ ኢትዮጵያ እና ዜጎቿ እስከ መቼ ርዳታ እየጠበቁ ይኖራሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት ያጫረ ችምር ነው።
አሜሪካ የምትሰጠው በተለይ የሰብአዊ ርዳታ መቋረጥ “ያለ ቅድመ ዝግጅት እጅግ የከበደ ይሆናል” የሚል ሥጋት እንዳላቸው ታደለ ሽፈራው ጽፈዋል። በሆስፒታል፤ በተለይ በወረዳ እና ቀበሌ ያሉ ጤና ጣቢያዎች የሚገለገሉባቸው ቁሳቁሶች እና መድኃኒቶች አብዛኛዎቹ በተራድዖ ድርጅቱ የሚገኙ ናቸው” የሚሉት ታደለ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት የምግብ ዋስትና እጦት ለገጠማቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚያቀርበው ሰብአዊ ርዳታ መቋረጥ የከፋ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል። “ያለ ምንም ቅድመ ዝግጅት በእርዳታ ጎርሶ የሚያድረው እና በድርጅቱ መድኃኒት የሚፈወሰው ጎልማሳ ወይም ደካማ እናቶች፣ ሕጻናት እና ኢኮኖሚው ያላንሰራራው ወገኔ ምኑ ይዋጠው?” ሲሉይ ጠይቃሉ።
ቴዎድሮስ ካሳሁን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ “ዲሞክራሲ፣ ሰላም እና ሰብአዊ መብት ሲጀመር የሉም። ከተቀጣሪ ሠራተኛ ውጪ በሌሉ ነገሮች የሚመጣ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሊኖር አይችልም። ጤና ፣ ግብርና፣ ትምህርት እና ሰብአዊ ድጋፎች ላይ ግን ከፍተኛ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል የማይካድ ሀቅ ነው” የሚል ሐሳብ አስፍረዋል።
ብርሀን አበባው “ሰላም መፍጠር፤ ጠንክሮ መስራት እና ሌብነትን ማቆም ያስፈልጋል። የልመና ጥገኝነት ህይወት እንደዚህ ነው።መረበሽ መጨነቅ አያስፈልግም። ፍቅር ቢኖረን መጠላላት መገፋፋት ባይኖር ሀገራችን እንኳን ለእኛ ለሌላም ትተርፍ ነበር” ይላሉ።
ታዲዮስ ኡታሎ “እርዳታ ላይ ብቻ መንጠልጠል እንዲቆም እና አይናችም እንዲበራ ስለሚያደርግ መልካም አጋጣሚ” እንደሆነ ያምናሉ።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ