1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የዐቢይ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ “መጥፎ” በተባለ ሥምምነት ወደ ንግድ ብድር ሊመለስ ነው?

ረቡዕ፣ ሰኔ 24 2018

ውድ ወለድ የሚከፈልባቸው የንግድ ብድሮች እንዳቆሙ በተደጋጋሚ ምለው የሚገዘቱት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ቃላቸው የሚፈተንበት ሥምምነት ከቦንድ ባለቤቶች ጋር አድርገዋል። ሥምምነቱ ኢትዮጵያ እስከ 9% ወለድ የሚከፈልበት ቦንድ እንድታወጣ የሚያደርግ ነው። ኢትዮጵያ ቦንዱን ካላወጣች ለግል አበዳሪዎቿ እስከ 90 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ትገደዳለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልባቸው የንግድ ብድሮች መውሰድ ማቆሙ “ከፍተኛ ምሥጋና የሚገባው ጠንካራ የፖሊሲ አቅጣጫ” እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ቀደም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። ምስል፦ Ludovic Marin/AFP

የዐቢይ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብ “መጥፎ” በተባለ ሥምምነት ወደ ንግድ ብድር ሊመለስ ነው?

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልባቸው የንግድ ብድሮች በማቆም የተከተለው አካሔድ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ከፍተኛ ምሥጋና የሚገባው ጠንካራ የፖሊሲ አቅጣጫ ነው።”

የመንግሥትን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ እንዳሉት እንዲያውም ውሳኔው ያኮራቸዋል።

ባለፈው ሣምንት በተካሔደ ስብሰባ “የንግድ ብድር ላይ እገዳ ተጥሎ ነበር” ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዢ “ባለፉት ስምንት ዓመታት አንድ ሣንቲም የውጭ ንግድ ብድር አልተበደርንም፤ አንድም ዶላርም አልተበደርንም” ሲሉ ተናግረዋል።

የዐቢይም ይሁን የማዕከላዊው ባንክ ገዢ የኩራት ምንጭ የሆነው አቋም ግን መንግሥት ከግል አበዳሪዎች ጋር በመርኅ ደረጃ ባደረገው የዕዳ ሽግሽግ ሥምምነት አጣብቂኝ ውስጥ ወድቋል። አቶ አሕመድ ሽዴ የሚመሩት የገንዘብ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ዶላር የተበደረችበት ቦንድ ባለቤቶችን ከሚወክል ጊዜያዊ ኮሚቴ ጋር የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ በመርኅ ደረጃ ከሥምምነት መደረሱን ያስታወቀው ሰኔ 22 ቀን 2018 ነበር።  

ከ12 ዓመታት በፊት መንግሥት ያወጣው ቦንድ 45 በመቶው ገደማ ባለቤት የሆኑ የግል አበዳሪዎችን ከሚወክል ኮሚቴ ጋር ሥምምነት የተደረገው ከረዥምና ውስብስብ ድርድሮች በኋላ ነው። በአበዳሪ እና ተበዳሪ መካከል በተደረገው በዚህ ሥምምነት መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለት ዐይነት ቦንዶች የሚያወጣ ይሆናል።

የመጀመሪያው የመክፈያ ጊዜው ያለፈበትን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ የሚተካ ነው። “አዲስ የገንዘብ ዋስትና ሰነድ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሁለተኛ ቦንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአበዳሪዎቹ የሚሰጠው መተማመኛ እንደሚሆን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በመተማመኛነት የሚወጣው የዕዳ ሰነድ ከመጀመሪያው ቦንድ ጋር የተቆራኘ ቢሆንም ለብቻው ተነጥሎ ሊሸጥ ወይም ሊለወጥ የሚችል እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር መግለጫ ይጠቁማል። “አዲስ የገንዘብ ዋስትና ሰነድ” የተባለውን ቦንድ ውሎች “ለግምገማ” ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ማቅረቡን የገለጸው የገንዘብ ሚኒስቴር “ለኢትዮጵያ ከተቀመጡት የዕዳ ዘላቂነት ግቦችና መለኪያዎች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን” ማረጋገጫ እንዳገኘ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነውን ቦንድ በማውጣት አንድ ቢሊዮን ዶላር የተበደረችው የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማስፋፋት ነበር። ምስል፦ Eshete Bekele Tekle/DW

ፈረንሳይና ቻይና ተቃውሞ እንደሌላቸው ቢገልጹም ኢትዮጵያ ቦንዱን ማውጣት የምትችለው በሰፊው ኦፊሴያል አበዳሪ ኮሚቴ ሲጸድቅ ብቻ እንደሚሆን አሳውቀዋል። ፈረንሳይ እና ቻይና የመጨረሻውን ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ ተባባሪ ሊቀ-መንበሮች ናቸው። 

እስከ 9% ወለድ የሚከፈልበት “አዲስ የገንዘብ ዋስትና ሰነድ”

በመርኅ ደረጃ የተደረገው ሥምምነት በኦፊሴያል አበዳሪ ኮሚቴ ተቀባይነት አግኝቶ ከጸደቀ ኢትዮጵያ የምታወጣውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ የግል አበዳሪዎች “የመግዛት የተወሰነ መብት” ይሰጣቸዋል። ይህ ቦንድ ከ8.5% እስከ 9% ወለድ የሚከፈልበት እንደሚሆን ኢ-ፍትኃዊ ዕዳ እና መንስኤዎቹን ለማስወገድ የሚሟገተው ዴብት ጀስቲስ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አስታውቋል።

የቦንድ ባለቤቶች በዕዳ ሽግሽግ ከሚከፈላቸው በተጨማሪ ኢትዮጵያ ሌላ ቦንድ እንድታወጣ ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለጹት የዴብት ጀስቲስ የፖሊሲ ዳይሬክተር ቲም ጆንስ “በሥምምነቱ መሠረት የቦንድ ባለቤቶች ገንዘቡን ለማበደር ማቅረብ አለባቸው። ከዚያ ከፈለገች ኢትዮጵያ ትበደራለች” ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት አዲስ ቦንድ በማውጣት ለመበደር ከወሰኑ አገሪቱ “ለሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ግምት ወደ 9% የሚሆን ወለድ ለመክፈል ትገደዳለች።”

“ነገር ግን ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልበትን ብድር ላለመበደር ቢወስኑ ለቦንድ ባለቤቶቹ እስከ 90 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይኖርባቸዋል” ሲሉ ቲም ጆንስ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ሊወጣ የሚችለው ቦንድ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ላይ ሣሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማስፋፋት ኢትዮጵያ የተበደረችውን አንድ ቢሊዮን ዶላር አከፋፈል ለማሸጋሸግ በመተማመኛነት የሚቀርብ ነው።

የመክፈያ ጊዜ ያለፈበትን ቦንድ የሚተካው የ880 ሚሊዮን ዶላር የዕዳ ሰነድ

አገሪቱ የተበደረችውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ኅዳር 2 ቀን 2017 መክፈል ነበረባት። ይሁንና በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግ መንግሥት ጥያቄ ባቀረበ በሦስተኛው ዓመት ማለትም ታኅሣሥ 16 ቀን 2016 ለቦንድ ባለቤቶች የሚጠበቅበትን 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ መክፈል አቆመ።

ባለፈው ሰኞ የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መግለጫ መሠረት መንግሥት የመክፈያ ጊዜ ያለፈበትን ቦንድ የሚተካ አዲስ ቦንድ ያወጣል። ይህ የዕዳ ሰነድ መንግሥት ከቦንድ ባለቤቶች ከተበደረው አንድ ቢሊዮን ዶላር በ12 በመቶ ዝቅ ብሎ የ880 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ እንዲኖረው ሥምምነት ላይ ተደርሷል።

በሥምምነቱ መሠረት በዓለም ገበያ የተሸጠው ቦንድ የሚከፈልበት ወለድ ከ6.625 በመቶ ወደ 6.15 በመቶ ዝቅ ብሏል። ይህ ወለድ የሚከፈለው በጥር እና ሐምሌ ወራት በዓመት ሁለት ጊዜ ነው።

“አዲስ የገንዘብ ዋስትና ሰነድ” የተባለውን ቦንድ ውሎች ለግምገማ ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ማቅረቡን የገለጸው የገንዘብ ሚኒስቴር “ለኢትዮጵያ ከተቀመጡት የዕዳ ዘላቂነት ግቦችና መለኪያዎች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን” ማረጋገጫ እንዳገኘ አስታውቋል።ምስል፦ Ministry of Finance Ethiopia

የኢትዮጵያ መንግሥት የቦንድ ባለቤቶችን ዕዳ በዓመት አንድ ጊዜ በሐምሌ ወር በሚፈጸም ክፍያ ከ2018 እስከ 2021 ለማጠናቀቅ እንደታቀደ የገንዘብ ሚኒስቴር መግለጫ አሳይቷል። በመግለጫው መሠረት የመጀመሪያው 180 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ የሚፈጸመው ሐምሌ 8 ቀን 2018 ነው። የመጨረሻው 300 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ በሐምሌ 2021 እንዲከናወን ታቅዷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ወለድ መክፈል ካቆመበት ጊዜ ጀምሮ የተጠራቀመ 99.4 ሚሊዮን ዶላር፣ “የሥምምነት ክፍያ” 5 ሚሊዮን ዶላር ለቦንድ ባለቤቶች የሚከፍል ይሆናል። የቦንድ ባለቤቶችን የሚወክለው ጊዜያዊ ኮሚቴ የነበሩበትን “አንዳንድ ወጪዎችና ክፍያዎች” ለመሸፈን የኢትዮጵያ መንግሥት 10 ሚሊዮን ዶላር “ካሳ” እንዲከፍል መስማማታቸውን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። ቲም ጆንስ በሥምምነቱ “የቦንድ ባለቤቶች ከሚገባቸው በላይ” እንዳገኙ ይተቻሉ።

“ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥፋት አይደለም” የሚሉት ቲም ጆንስ የደሐ አገሮችን የዕዳ ጫና ለማቃለል የጋራ ማዕቀፍ የተባለ መርሐ-ግብር የዘረጋውን ቡድን 20 “ከቦንድ ባለቤቶች ጋር በሚደረገው ድርድር በቂ ድጋፍ ባለማቅረቡ” ይወቅሳሉ። በዴብት ጀስቲስ የፖሊሲ ዳይሬክተር አባባል የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥትም ጥፋት አለበት።

“ምክንያቱም የቦንድ ባለቤቶች በዩናይትድ ኪንግደም ‘ክስ እንመሰርታለን’ ብለው በማስፈራራት ለራሳቸው ጥሩ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ መጥፎ የሆነ ሥምምነት ለማግኘት ችለዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

በዴብት ጀስቲስ ስሌት መሠረት ኢትዮጵያ ከታኅሣሥ 2016 ጀምሮ ያለባት የቦንድ ባለቤቶች የተጣራ ዕዳ 900 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል። በተቋሙ ስሌት መሠረት ከ2008 እስከ 2016 ኢትዮጵያ የከፈለችውን ወለድ ሳይጨምር የቦንድ ባለቤቶች ለመንግሥት ካበደሩት 90 በመቶው ተመልሶ ይከፈላቸዋል።

ለቦንድ ባለቤቶች የሚከፈለው ፈረንሳይና ቻይናን የመሳሰሉ የመንግሥት አበዳሪዎች ከሚከፈላቸው በ9 በመቶ ገደማ የሚበልጥ ነው። ኢትዮጵያ “አዲስ የገንዘብ ዋስትና ሰነድ” የተባለውን ቦንድ ሳታወጣ ቀርታ እስከ 90 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ከወሰነ ግን ለቦንድ ባለቤቶች ተመልሶ የሚከፈለው ዕዳ ከመንግሥታት አበዳሪዎች በ17 በመቶ ሊበልጥ እንደሚችል ቲም ጆንስ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤቶች እነማን ናቸው?

የቦንድ ባለቤቶችን የሚወክለው ጊዜያዊ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመርኅ ደረጃ ከሥምምነት መደረሱን አረጋግጧል። ኮሚቴው ሥምምነቱ በገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ከተደረገ በኋላ ሁሉም የቀድሞው ቦንድ ባለቤቶች በመርኅ ደረጃ በተደረገው ሥምምነት የቀረበውን ምክረ-ሐሳብ እንዲሁም በዕዳ ሽግሽጉ ውስጥ በመሳተፋቸው የሚያገኙትን ጥቅምና የሚገጥማቸውን ሥጋት በገለልተኝነት እንዲገመግሙ መክሯል።

ለትርፍ ቅድሚያ ከሚሰጡ መሰል የቦንድ ባለቤቶች ጋር ለዕዳ ሽግሽግ ሲካሔድ የቆየው ድርድር የመንግሥትን “ትዕግሥት” የተፈታተነ እንደነበር የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ከፍተኛ አማካሪ ከዚህ ቀደም ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ቦንድ 45 በመቶው ባለቤቶችን በሚወክለው ጊዜያዊ ኮሚቴ ውስጥ ሞርጋን ስታንሌይ ኢንቨስትመንት ማኔጅመንት፣ ፋራሎን ካፒታል ማኔጅመንት እና ቪአር ካፒታል ግሩፕ የተባሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች ይገኙበታል።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ ጥብቅ የበጀት ቁጥጥር፣ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግና ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተገኙ ውጤቶች የአገሪቱን የዕዳ ጫና “ዘላቂ” ወደሚባለው ደረጃ ዝቅ እንዳደረጉ በቅርቡ ተናግረው ነበር።ምስል፦ Eshete Bekele/DW

“እነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ አበድረው አያውቁም። የብድር ሰነዱን የገዙት ኢትዮጵያ ዕዳ መክፈል ካቆመች በኋላ ነው። ቦንዱን በርካሽ ከገዙ በኋላ ከፍተኛ ትርፍ ለማጋበስ ሲያደቡ ቆይተዋል” የሚሉት የዴብት ጀስቲስ የፖሊሲ ዳይሬክተር “ሥርዓት እንዲይዙ መደረግ አለባቸው” የሚል አቋም አላቸው።

ኢትዮጵያ ከመንግሥታት አበዳሪዎች ከሰጡት የክፍያ እፎይታና ከግል አበዳሪዎች ጋር ከተደረገው ሥምምነት በኋላም ቢሆን “ከፍተኛ የዕዳ ቀውስ ስጋት ውስጥ” እንደምትሆን ቲም ጆንስ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ ግን ጥብቅ የበጀት ቁጥጥር፣ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግና ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተገኙ ውጤቶች የአገሪቱን የዕዳ ጫና “ዘላቂ” ወደሚባለው ደረጃ ዝቅ እንዳደረጉ በቅርቡ ተናግረው ነበር።

በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ ለረዥም ዓመታት ሲካሔድ የቆየው ድርድር ተጠናቆ ገቢራዊ ሲሆን ግን አገሪቱ የሁለት ዓመት የዕዳ ክፍያ ግዴታ በአንድ የበጀት ዓመት ለመፈጸም ልትገደድ ትችላለች። የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከሚፈታተኑት ጦርነት፣ ግጭት እና ዓለም አቀፋዊ ቀውሶች ጋር ተደማምሮ የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ ክፍያ በመንግሥት በጀት ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር ነው።

መንግሥት ከሚቀጥለው ዓመት በጀት ውስጥ ለዕዳ ክፍያ 542 ቢሊዮን ብር በላይ የመደበ ሲሆን በዓመቱ ነዳጅ ለመሸመት ብቻ እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገዋል። በነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ምክንያት ወደ ነጠላ አሐዝ ዝቅ ብሎ የነበረው የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት በግንቦት ወር 13.4 ሆኖ እንደተመዘገበ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታውቋል።

ባለፉት ዓመታት የዓለም ኢኮኖሚን የተፈታተኑት የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የጂዖፖለቲካዊና የአየር ንብረት ቀውሶች በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩት ጫናም ከፍተኛ ነው። የኢትዮጵያ የዕዳ ጫና በተደራራቢ “ተግዳሮቶች ምክንያት ድጋሚ ወደ ቀውስ እንዳያመራ፣ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የዕዳ እፎይታ ማግኘት” እንዳለባት የዴብት ጀስቲስ የፖሊሲ ዳይሬክተር ቲም ጆንስ አስረድተዋል።

አርታዒ አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW