የዒድ አል ፈጥር በዓል አከባበር በሀዋሳ
ዓርብ፣ መጋቢት 11 2018
የዒድ አል ፈጥር በዓል አከባበር በሀዋሳ
የታላቁ የረመዳን ጾም ወር ማብቂያ የሆነው 1 ሺህ 447ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል በሀዋሳ ከተማ ተከብሯል ፡፡ እንደተቀረው የኢትዮጵያክፍል ሁሉ በዓሉ የተከበረው በተለይ ዛሬ ጠዋት በከተማው የሚሊኒየም አደባባይ የጀመኣ ሶላት ወይም የጋራ ፀሎት በማከናወን ነው ፡፡
የበዓሉ ታዳሚዎች ሥሜት
በአደባባዩ በመገኘት በጋራ ፀሎቱ ከተሳተፉት መካከል ለዶቼ ቬለ አስተያየቷን የሰጠችው ቀድሪያ ሙቀዲስ “ አላህ ሳይለየን ከዓመት ዓመት የሚያደርስን ሰዎች ያድርገን፡፡ አላህ ሳይለን በፍቅር በሰላም በጤና አገራችንን ሰላም አርጎልን በሰላም ያቆየን ማለት እፈልጋለሁ “ ብላለች ፡፡
ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡት ኡስታዝ ሙሀባ ከድር በበኩላቸው ‹‹ ሁሉም ሰው በሳምንት አንዴ ዓርብ መስጂድ ውስጥ ተሰብስቦ አምልኮ ይፈፅም ነበር ፡፡ ዛሬ ደግሞ ሁለቱ በዓል አንድ ላይ ሥለተገናኘ በጣም ደስተኛ ሆኛለሁ ፡፡ ለአገር ሰላምና አብሮነት ዱኣ እያደረግን የምናሳልፍበት ቀን ነው ›› ብለዋል ፡፡
የከንቲባው መልዕክት
በጋራ ፀሎት ሥነሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ለእምነቱ ተከታዮች መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ያጣነው ነገር የለም የጎደለን ነገር ቢኖር ፍቅር እና አንድነትነው በማለት የተናገሩት ከንቲባ ጥራቱ “ ይህንን ደግሞ በረመዳን የፆም ወቅት በደንብ አይተነዋል ፡፡ ይህን መተግበር ብቻ ነው ያቃተን ወይንም የተቸገርነው ፡፡ መላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በፆም ወቅት ያደረጋችሁትን መተባበር የከተማችን አስተዳደር እጅግ የሚያከብረው የሚያደንቀው ነው ፡፡ መላው ኢትዮጵዊያንም ከእናንተ ጋር አብረው ያሳለፉ በመሆኑ ለዚህ ትልቅ ክብር እና ኩራት የሚሰማን መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ ” ብለዋል ፡፡
የዒድ አልፈጥር ሶላት ተሰግዶ እንዳበቃም ተክቢራ ወይንም ለፈጣሪ ምሥጋናበማሰማት በዝየራ ወደ የአካባቢያቸው ተመልሰዋል ፡፡ የእምነቱ ተከታዮች ሸሪዓው በሚያዘው መሠረት ዘካተል ፊጥር ወይንም የጾም ፍች ምጽዋት በማውጣት የተቸገሩ ወገኖች የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ አድርገዋል ።
ዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ
ጸሐይ ጫኔ