የዒድ አል ፊጥር በዓል በብሔራዊ ደረጃ በአዲስ አበባ ተከበረ
ዓርብ፣ መጋቢት 11 2018
የዒድ አል ፊጥር በዓል በብሔራዊ ደረጃ በአዲስ አበባ ተከበረ
1447 ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል ፊጥር በዓል ዛሬ አርብ መጋቢት 11 ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል። ለአንድ ወር በፆምና ፀሎት የቆዩት ሙስሊሞች በዓሉን
በብሔራዊ ደረጃ በአዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ እና በዙሪያው በመሰባሰብ በጋራ በስግደት አክብረውታል።
ሃይማኖቱ በሚያዘው መሠረት ምዕመኑ ለዒድ አል ፊጥር ስግደት ከመውጣቱ በፊት ዘካተል ፊጥር የሚባለውንና አቅም ላነሳቸው ድጋፍ የማድረግ ግዴታን ይወጣል። የጋራ ዒድ ሶላቱ ከማለዳው 2:30 ላይ የተከናወነ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ በሰላም መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።
የሮመዳን ፆም ፍቺ ሃይማኖታዊ በዓል ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሃይማኖቱ መሪዎች፣ በርከት ያለ ምዕመን በተገኘበት በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደ ከዚህ በፊቱ ተከብሯል። ሙስሊሞች ከንጋቱ 12 ጀምሮ ስግደቱ እስከሚፈፀምበት 2:30 ድረስ በስታዲየሙና በዙሪያ የሃይማኖቱን ሥነ - ሥርዓት በጋራ ተካፍለዋል።
እስልምና ሃይማኖት ፈጣሪ አንድ መሆኑን ማመንን፣ የሰላት ስግደት መስገድ ግዴታ መሆኑን ማመንና መፈፀምን፣ ቤተሰቡን ማስተዳደር የሚችል፣ ያንን ማድረግ ላልቻሉት ድጋፍ ማድረግ ወይም ዘካ ማውጣት እንዲሁም አቅሙ ያለው ሰው ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሐጂ ጉዞ ማድረግ እንዲሁም ለአንድ ወር ተፁሞ ዛሬ እንደተጠናቀቀው የረመዳን ፆምን መፆም ይጠይቃል።
የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና እና የአረብ ሀገራት ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል ከኢራን ጋር በገቡበት ጦርነት ምክንያት ቀውስ ውስጥ ገብቷል። አካባቢው ምንም እንኳን ችግር ውስጥ ቢሆንም ወቅቱ ሙስሊሞች የሐጂ ጉዞ የሚያደርጉበት እንደመሆኑ ባለፈው ሳምንት ብዙ ኢትዮጵያዊያንይህንን ሃይማኖታዊ ጉዞ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን የውጭ ምንዛሪ ላማውጣት ሲንቀሳቀሱ ተመልክቻለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንኳን ረደረሳችሁ ብለው በጻፉት መልካም ምኞች የመንግሥታቸውን ትልም የቀየጠ መልዕክት አስተላልፈዋል። "ሮመዳን ቤተሰብ የሚገናኝበት፣ ኅሊና የሚሰበሰብበት፣ ሰውነት የሚገራበት እና መንፈስ የሚቀናበት ወር ነው" ሲሉም "ዒድ አል ፈጥር የሰውን ልጅ ጤናማ ግንኙነቶች የሚያመለክት በዓል ነው" ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የዛሬው የስግደት ሥነ - ሥርዓት በሰላም መጠናቀቁን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በበኩሉ በመላ ሀገሪቱ የተከበረው የዒድ አል ፈጥር በዓል በሰላም ስለመጠናቀቁ ገልጿል።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ
ጸሐይ ጫኔ