የዒድ አከባበር በድሬ ደዋ ከተማ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2014ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወጣቶችን ጨምሮ ለዶይቼ ቬለ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎች በጎንደር በተከሰተው ድርጊት ማዘናቸውን ገልጠው መንግስት በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።
በዛሬው የኢድ አል - ፊጥር በዓል አከባበር ላይ ከተገኙ ተሳታፊዎች አንዱ የሆኑት አቶ ካሚል ኢብራሂም በጎንደር የተፈጠረው ድርጊት አሳዛኝ ፤ ነገር ግን ህዝብን የማይወክል መሆኑን ገልፀው ሙስሊሙ ማህበረሰብ እንዲህ ያለ ጠብን በጥፋት መመለስ የለበትም ብለዋል።
ከቀናት በፊት በድሬደዋ ተከስቶ በነበረው ሁከት የሳተፉት" መስጊድ የማይመጡ ፣ የእምነቱ አባቶች እና መንግስት የሚለውን የማይሰሙ ጥቂት አካላት ያደረጉት ነው" ያለው በድሬደዋ የእስልምና እምነት ተከታይ ወጣቶች አስተባባሪ አብዱልአዚዝ ሻፊ ይህንንም በሂደት መቅረፍ እንደሚያስፈልግ እና እነሱም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፃል።
"እያንዳንዱ ሰው ጥረት አድርጎ ሰላም ማስፈን አለበት ያለው ወጣት ራይት ዩሱፍ በማህበራዊ ሚዲያ የሚራገቡ ነገሮችን ማስቆም አለብን" ብሏል ።
መሀመድ ሙደሲር ለዶይቼ ቬለ" በጎንደር በተፈጠረው ድርጊት የተሳተፉ አካላትን መንግስት በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ተስፋ አለን ይህንንም ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄያችንን እያቀረብን እንገኛለን" ብሏል።
በረመዳን ወር የታየው የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ተግባር በዛሬው የበዓሉ እለት የተቸገሩትን በመርዳት እና በጋራ በመሆን እንዲከበር ጥሪ ቀርቧል።
በበዓሉ የተገኙትን የመስተዳድሩ ከንቲባ ከድር ጁሀርን ጨምሮ የእስልምና እምነት መሪዎች የከተማዋን የፍቅር እና የመቻቻል ለመጠበቅ ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠበቅ ያለ የፀጥታ ጥበቃ የታየበት የዕለቱ በዓል ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን የድሬደዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገፁ አስታውቋል ።
መሳይ ተክሉ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ