የዒድ ጥሪ ለዲያስፖራ ማህበረሰብ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 20 2014የኢትዮጵያ መንግስት ለአገር ገጽታ ግንባታ ጉልህ ሚና ይጫወታል በሚል ከአገር ውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም ጥሪ ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ጥሪው በኢትዮጵያውያን መካከል አንድነትን በመፍጠር የኢኮኖሚ አቅምንም ለመገንባት ጉልህ ድርሻ ያለው ነው ይባልለታል፡፡ ከኢድ እስከ ኢድ በሚል በቅርቡ ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን በተደረገው የአገር ቤት መመለስ ጥሪ መሠረት ወደ አገሪቱ ለተመለሱ ኢትዮጵያንም አቀባበል ተደርጓል፡፡
ያሲን ሳሌህ አብዱራሃማን በአውሮፓ ስዊድን አገር ለ46 ኣመታት ያህል ኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ የወቅቱ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የረመዳን ወርን ተከትሎ ወደ አገር ቤት ጉዞ እንዲያደርጉ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት መምጣታቸውንም ይገልጻሉ፡፡ አሁን በችግሮች ብዛት ተተብትባ በምትገኝ አገር ውስጥ ተስፋ እንደሚታያቸውና ይህም በአገራቸው ለመስራት እንዳነሳሳቸው አውስተዋል፡፡
ከኢድ እስከ ኢድ በሚል በእስልምና ሃማኖት ተከታዮች ዘንድ እንደ ቅዱስ ወር በሚታየው በረመዳን ፆም ወቅት የወደ አገር ቤት ጥሪን ተከትሎ ለመጡ ትናንት በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ በተደረገው የእንኳን ደህና መጣችው መርሃ ግብር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ በመልእክታቸው መገፋፋትና ጽንፈኝነትንም አውግዘው ለአንድነት እና መተባበር ተማጽነዋል፡፡
በዚሁ የእንኳን ደህና መጣችሁ መድረክ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የጉዞ ጥሪው የኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባትና የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ጉልህ ሚና ያለው ነው ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻል ዘመናትን ያለፈ ታሪክ ያለው መሆኑን ገልጸው ሰሞኑን በጎንደር የተከሰተውን ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ግጭት የማይገልፀን ብለው ኮንነውታል፡፡ ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪውም መንግስታቸው እየተገበረ የሚገኘው የአዲስ የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋልም፡፡
ሥዩም ጌቱ
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ