1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ምግብ ድርጅት ርዳታ ኢትዮጵያ ለሰፈሩ ስደተኞች

ረቡዕ፣ መስከረም 30 2016

ድርጅቱ ከዚህ ቀደም የእርዳታ እህል ያለአግባብ በባለስልጣናት ተጠልፎ ለገቢያ ውሏል በሚል እንደ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ካሉ ዓለማቀፍ ረጂ ተቋማት ጋር በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ካቋረጠ ከወራት በኋላ ነው አሁን በስደተኞች ካምፕ አደረኩ ባለው ማጣራት እና በዘረጋው የቁጥጥር ስልት መሰረት ድጋፍ ለመቀጠል መወሰኑን ያስታወቀው፡፡

ርዳታዉ ተሰርቋል በሚል ተቋርጧል
የዓለም ምግብ ድርጅት በትግራይ ጦርነት ለተቸገሩ ከጠዉ ርዳታ በከፊልምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ድርጅቱ ርዳታ የሚሰጠዉ ለስደተኞች ብቻ ነዉ

This browser does not support the audio element.

 

የኣልም ምግብ ድርጅት  (WFP) ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሠፈሩ 900 ሺህ ገደማ ስደተኞች የሚሰጠዉን ርዳታ  እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡ድርጅቱ፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሚገኙ ስደተኞችና ተፈናቃዮች መሰጠት የነበረበትርዳታ ተሰርቋክ ወይም ለሌላ አገልግሎት ዉሏል በማለት ርዳታዉን ካለፈዉ ሰኔ ጀምሮ አቋርጦ ነበር።ይሁንና ዓለም አቀፉ ድርጅት አሁን ባወጣዉ መገለጫ በተለይ የስደተኞች ሕይወት ለአደጋ በመጋለጡ ርዳታዉን ለመቀጠል መወሰኑን አስታዉቋል።በድርጅቱ መግለጫ መሰረት ርዳታዉ የሚሰጠዉ ለስደተኞች እንጂ ለሐገር ዉስጥ ተፈናቃዮች አይደለም።ኢትዮጵያ ዉስጥ ከ20 ሚሊዮን የሚበልጡ ተፈናቃዮች ርዳታ ይሻሉ።

የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ድርጅት  (WFP) በኢትዮጵያ 900 ሺህ ለሚጠጉ ስደተኞች ምግብ ማሰራጨት መጀመሩን ያሳወቀው ከሰሞኑ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ነው፡፡ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም የእርዳታ እህል ያለአግባብ በባለስልጣናት ተጠልፎ ለገቢያ ውሏል በሚል እንደ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ካሉ ዓለማቀፍ ረጂ ተቋማት ጋር በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ካቋረጠ ከወራት በኋላ ነው አሁን በስደተኞች ካምፕ አደረኩ ባለው ማጣራት እና በዘረጋው የቁጥጥር ስልት መሰረት ድጋፍ ለመቀጠል መወሰኑን ያስታወቀው፡፡

WFP ከሱዳን ኢትዮጵያ የደረሱ አዲስ ፍልሰተኞችን ጨምሮ በአገሪቱ አምስት ክልሎች ውስጥ ያሉ ስደተኞች የምግብ እርዳታ መቀበላቸውን አሳውቋል፡፡ ይህም ረጂ ተቋሙ የእርዳታ ድጋፍ በስፋት ተሰርቋል በሚል ባለፈው ሰኔ ድጋፉን ካቋረጠ በኋላ ያደረገው የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ መሆኑ ነው፡፡

የዓለም ምግብ ድርጅት ቻድ ዉስጥ ለሰፈሩ የሱዳን ስደተኞች የሚሰጠዉ ርዳታምስል Mahamat Ramadane/Reuters

ዶይቼ ቬለ ለተጨማሪ ማብራሪያዎች በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች ያሉትን የተቋሙን ኃላፊዎች አስተያየት በዚህ ዘገባ ለማካተት በስልክ እና በኢሜይል ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሻቸውን ማግኘት አልቻለም፡፡

ተቋሙ በጽሁፍ ባወጣው መግለጫ ግን የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ረዳት ቫሌሪ ጉዋርኔሪ “ተቋማቸው ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ምግብን አብዝቶ ለሚፈልጉ ለማድረስ በየሰዓቱ ያለመታከት ይሰራል” ማለታቸውን አትቷል፡፡ ቫሌሪ አክለውም “ምግብ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ስደተኞች ህይወት ለመቀጠል ወሳን በመሆኑ ድጋፉን የማስቀጠል ውሳኔ ላይ ደርሰናል” ብለዋልም፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ግን ስለ ረጂ ተቋሙ ሰሞነኛ መግለጫ የማውቀው ነገር የለም ይላል፡፡ የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አታለል አቦሃይ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለስደተኞች አደረኩ ባለው ባሁኑ ድጋፍ የኮሚሽኑ ቋት ውስጥ የገባ ነገር የለም፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በሱዳን ባለው ጦርነት ሰበብ ከ35 ሺህ በላይ ፍልሰተኞች ኢትዮጵያ መድረሳቸውን ያሳወቀው WFP ኢትዮጵያ በበኩሏ ከሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትሪያ የተቀበለቻቸው 850 ሺህ ስደተኞች መኖራቸውንም አመልክቷል፡፡ ረጂ ተቋሙ የእህል፣ የአትክልት ዘይትና ጨው የመሳሰሉ የምግብድጋፉን ያሰራጨው በሶማሊ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና ደቡብ ክልሎች ላሉ እርዳታ ፈላቂ ስደተኞች መሆኑንም ነው ያስረዳው፡፡ የተወሰኑ ስደተኞች ድጋፉን በገንዘብም መቀበላቸው ነው የተገለጸው፡፡

ድርጅቱ የምግብ እርዳታውን ዳግም ሲጀመር የተለያዩ አዳዲስ የመቆጣጠሪያ ስልት መዘርጋቱንም ነው ያሳወቀው፡፡ በየስደተኞች ካምፕ ያሉ ማከማቻዎች 24 ሰዓት በሙሉ በተቋሙ በራሱ እንዲጠበቁ ማድረግ፣ ስደተኞችን በዲጂታል በተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ቋት መመዝገብ፣ ከስተተኞቹ ግብረ-መልስ መሰብሰብ፣ ከሌሎች መንግስታዊ ካልሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በምግብ ስርጭቱ መስራት እና ስለስደተኞች ጥልቅ መረጃ መያዝ የሚሉ አዲስ የአሰራር ለውጥ ስራ ላይ መዋሉም ነው የተብራራው፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ውስጥ በግጭትና በተለያዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ለተፈናቀሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚያደርገውን ድጋፍ ግን አሁንም እንዳቋረጠ ቀጥሏል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ቃል አቀባዩ አቶ አታለል አቦሃይ ይህ የረጂ ተቋማት ድጋፍ ማቆም በመንግስት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳለው የሚሸሸግ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ “ጫና እንደሚያሳድር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ መንግስት ለሌሎች የልማት ዓላማ የያዘውን 4.5 ቢሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ ከሰሞኑ ብቻ በትግራይ እና አማራ ክልል ሰቆጣ አድርጓል፡፡ ይህ አከባቢ ከዚህ በፊት ሙሉ በሙሉ በጨዓለም ምግብ ፕሮግራም የሚሸፈን ነበር፡፡”

የዓለም ምግብ ድርጅት ለኢትዮጵያ ተፈናቃዮችና ኢትዮጵያ ለሚኖሩ ስደተኞች የሚሰጠዉ ርዳታ ከተከማቸበት መጋዘን አንዱምስል Florian Gaertner/photothek/picture alliance

ይሁንና የዓለም ፕሮግራም በሰሞነኛ መግለጫው ድጋፉን ለመቀጠል የሚያስችሉ ያሏቸው የቁጥጥር ስራዎችን በመከወን ተስፋ ሰጪ ሂደቶች ላይ እንደሚገኝ አሳውቋል፡፡ እነዚህ ሂደቶች በጣም ተጋላጭ የማህበረሰብ አካላት ድጋፍ የሚያገኙበትን መንግድ ለመፈለግ ከማህበረሰብ ጋር በመሆን የመስራት ውጥን መኖሩ ነው የተመላከተው፡፡ በዚህም መረዳት የሚገባቸው የቤሰተሰብ አባላት ከሚሰራጨው ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

ከባለፈው እሁድ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ላይ የነበሩ የዓልም ፍልሰተኞች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኤሚ ፖፕ የዓለማቀፍ ረጂ ተቋማት ድጋፋቸውን በኢትዮጵያ ማቋረጥ በተቋማቸውም ላይ ጉሊህ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡

ስዩም ጌቱ 

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW