የካንሰር ህክምና በኢትዮጵያ
ማክሰኞ፣ ጥር 27 2017
የዓለም ካንሰር ቀን በየዓመቱ በጎርጎሪዮሳዊው የካቲት 4 ቀን ይታሰባል። የካንሰር ቀን ዛሬ ሲታሰብ መሪ ቃሉ «ታማሚዎችን ማዕከል ያደረገ ህክምናን መስጠት» የሚል ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ይታያል። ለምን ይሆን? የካንሰር ህክምናውስ እንዴት ነው?
ዓለም አቀፍ የካንሰር ቀን መረጃ
የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር ከጊዜወደጊዜ እየጨመረ መሄዱን የሚያመላክቱ መረጃዎች እየተበራከቱ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው ካንሰር ለሰዎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ከሆኑ ህመሞች ቀዳሚው ሆኗል። የጡት ካንሰር፤ የሳንባ፤ የአንጀት፣ የፊንጢጣ እና ፕሮስቴት ካንሰርም በብዛት ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙ የካንሰር ዓይነቶች መሆናቸውንም የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ኢትዮጵያ ውስጥ የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ ለመሄዱ አንድም የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ምክንያት መሆኑን የገለጹት በአዳማ ሆስፒታል የህክምና ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት የካንሰር ህክምና ባለሙያው ዶክተር ቢንያም ተፈራ የህክምና ምርመራው ስልት መሻሻልም ሌላው ምክንያት ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚበረከቱት የካንሰር ዓይነቶች
የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እየበረከተ ነው ቢባልም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመመዝገብና የመረጃ አያያዝ ሁኔታው የተጠናከረ እንዳልሆነ የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው የሚገልጹት ጉዳይ ነው። የተለያየ ማኅበረሰብና ባህል ባለባት ኢትዮጵያ የካንሰር ስርጭት ከቦታ ቦታ እንደሚለያይ የሚገልፁት ዶክተር ቢንያም፤ በተደራጀ ሁኔታ የካንሰር ታማሚዎችን ሁኔታ የሚመዘግቡ የህክምና ተቋማት ውሱን መሆናቸውን ነው የነገሩን። እሳቸው እንደሚሉት የዓለም የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የካንሰር ሁኔታን የሚገልፅ መረጃን የሚያገኘው ከአዲስ አበባ ካንሰር መመዝገቢያ ነው። በሆስፒታል ደረጃ ደግሞ እሳቸው የሚያገለግሉበት የአዳማ ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅም እንዲሁ እንደሚመዘግብ ገልጸውልናል። እንደ አዲስ አበባው ካንሰር መመዝገቢያ ከሆነ፤ በብዛት ቀዳሚው የጡት ካንሰር ሲሆን፤ የማሕጸን በር ካንሰር ሁለተኛ ደረጃን ይይዛል። በሦስተኛነት የአንጀት ካንሰር መሆኑን ያመለክታል።
ከሶማሌ ክልል ሳይቀር ታማሚዎችን የሚያስተናግደው የአዳማ ሆስፒታል ምዝገባ መሠረት ደግሞ አሁንም የጡት ካንሰር ቀዳሚው መሆኑን ነው ዶክተር ቢንያም የተናገሩት። አዳማ ላይ በሁለተኛነት የሚገኘው የጉሮሮ ካንሰር ሲሆን ሦስተኛው የጉበት ካንሰር ነው። እንዲህ ያለው መረጃ የመመዝገብ ሥርዓት በሁሉም የኢትዮጵያ የህክምና ተቋማት መለመድ ያለበት መሆኑን ያመለከቱት የካንሰር ህክምና ባለሙያው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ነው የሚሉት።
በኢትዮጵያ የካንሰር ህክምና ይዞታ
ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የካንሰር ሀኪሞች ቁጥርእጅግ ጥቂት ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ባለሙያ ሀኪሞች እየተበራከቱ ለካንሰር የሚሰጠው የህክምና አገልግሎትም እየተሻሻለ መሄዱን በአዳማ ሆስፒታል የህክምና ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት የካንሰር ህክምና ባለሙያው ዶክተር ቢንያም ተፈራ ያስረዳሉ።
እሳቸው እንደሚሉት በህመሙ ተጎድቶ ለሞት ከመዳረግ አስቀድሞ ካንሰርን ቶሎ የማግኘቱ ሃላፊነት ከባለጉዳዩ አንስቶ የህክምና ባለሙያዎች ብሎም የመገናኛ ብዙሃንም ሚና አለበት። የዘንድሮው የዓለም ካንሰር ቀን መሪ ቃል «ታማሚዎችን ማዕከል ያደረገ ህክምናን መስጠት»ን ይመለከታል።
ካንሰር በዓለም ደረጃ ገዳይ ከሚባሉ ህመሞች ተርታ ቀዳሚ ነው ቢባልም ሳይባባስ ቀድሞ ከተደረሰበትና ተገቢው ህክምና ከተገኘ የመዳን እድሉ ሰፊ እንደሆነ በእማኝነት አደባባይ ወጥተው እራሳቸውን ለሌሎች አርአያነት ያቀረቡ ጥቂት አይደሉም። የካንሰር ህክምና ኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመሆኑም ለህክምና ባለሙያዎቹ ጆሮ መስጠቱ ይመከራል። የካንሰር ህክምና ኢትዮጵያ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሆኑን የገለጹልንን የዘርፉን ህክምና ባለሙያ ዶክተር ቢንያም ተፈራን እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ