የዓለም የገንዘብ ተቋም የበላይ ኃላፊ ስለ ኢትዮጵያ
ሰኞ፣ የካቲት 3 2017
የዓለም የገንዘብ ተቋም የበላይ ኃላፊ ስለ ኢትዮጵያ ምን አሉ?
ኢትዮጵያ የጀመረችው ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሐ ግብር የመጀመሪያ ወራት አፈጻጸም የሚደነቅ መሆኑን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የበላይ ኃላፊ ክሪስታሊና ጆርጅየቫ ተናገሩ። እንዲያም ሆኖ ማሻሻያው ሙሉ በሙሉ በታሰበው ልክ እንዲሳካ ጊዜ እና ቁርጠኝነት የሚፈልግ፤ የመንግሥትን የፖለቲካ ይሁንታ እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ድጋፍ የሚጠይቅ ስለመሆኑ ኃላፊዋ አዲስ አበባን ከጎበኙ በኋላ አስታውቀዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ መንግሥት ለዚህ ሥራ ውጤት "ጤናማ የምጣኔ ሀብት አስተዳደር" ለማድረግ ቁርጠኛ ስለመሆኑ ገልፀዋል። በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የገንዘብ ባለሙያ ይህ ተቋም የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማገዝ "ትልቅ ቁርጠኝነት ውስጥ የገቡ ይመስላል" ብለዋል።
የተጀመረውን የማሻሻያ ሥራ ማስቀጠል ይገባል - ወይዘሮ ክሪስታሊና
የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ትናንት እሑድ ያጠናቀቁት የዓለም የገንዘብ ተቋም (IMF) የበላይ ኃላፊ ወይዘሮ ክሪስታሊና ጆርጅየቫ የጉብኝታቸውን ውጤት ሲያብራሩ እስካሁን ተገኘ ባሉት ስኬት "ኢትዮጵያ የምትኮራበት ብዙ ነገር" መኖሩን ዘርዝረዋል። የኢትዮጵያ ያለፈው ዓመት የሀገር ውስጥ ምርት 6.1 በመቶ ተገምቶ በ8.1 በመቶ ማደጉን፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት ምርታማነት ዕድገት መመዝገቡንም አብራርተዋል። የሚመሩት ተቋም ለኢትዮጵያ እስካሁን 1.5 ቢሊዮን ዶላር መልቀቁንም ገልፀዋል። ምንም እንኳን ተጽእኖው ቀላል ባይሆንም በዚህ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ኢትዮጵያ ከፊቷ ብሩህ ተስፋ እንደሚጠብቃት እምነታቸውን የገለፁት ኃላፊዋ እርምጃው እጅግ ጠቃሚ እና በጎ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል። "በቀጣይ የሚሆነው የተጀመረውን ሥራ ማስቀጠል ነው። ኢኮኖሚን መለወጥ ጊዜ የሚፈጅ፣ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው፤ በተጨማሪም የመንግሥትን የፖለቲካ መሻት እንዲሁም የኢትዮጵያን ሕዝብ ድጋፍ የሚጠይቅ ነው።" በማለት ሀገርቱ በኢኮኖሚ እንደምታድግ ያላቸውም እምነት ገልፀዋል።
ጤናማ የምጣኔ ሀብት አስተዳደር እንዘረጋለን - መንግሥት
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የግዙፉ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ጉብኝት በኢትዮጵያ እና በተቋሙ መካከል ላለው ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል። መንግሥት የጀመራቸውን የገንዘብ አስተዳደር ሕግጋትና የአሠራር ለውጦች የዘረዘሩት ሚኒስትሩ አይ.ኤም. ኤፍን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ለዚህ ማሻሻያ መሳካት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚጠብቁ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። "እየተከናወነ ያለው የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሐ ግብር ውሎ አድሮ ለሕዝባችን ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ እና ለወጣቶቻችን በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የተመሰረተ የተረጋጋ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር በፅኑ እናምናለን። ግቦቻችን ሙሉ በሙሉ እውን እስኪሆኑ ድረስ የዚህ ማሻሻያ ቀጣይነት ያለው እድገትን ለማረጋገጥ ጤናማ የምጣኔ ሀብት አስተዳደር ለማድረግ ቁርጠኞች ነን።"
ስለ ጉብኝቱ የገንዘብ ባለሙያ አስተያየት
የባለሥልጣኗን የኢትዮጵያ ጉብኝት ክብደት በተመለከተ ምልከታቸውን የጠየቅናቸው የገንዘብ ባለሙያው አቶ ኢድሪስ ሰዒድ ጉዳዩን በበጎ ተመልክተውታል። "በሌሎች ሀገሮች ላይ እንደዚህ አይነት [የገንዘብ አለቃቀቆች] የሚደረጉት ሰፋ ባለ ጊዜ ነው። ለኢትዮጵያ ግን የ አራት ዓመት መርሐ ግብር ቢሆንም በአጭር ጊዜ ሦስት ጊዜ ሰጥተዋቸዋ።" በማለት ተቋሙ ለኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የበላይ ኃላፊ ክሪስታሊና ጆርጅየቫ በሰጡት መግለጫ አንድ ነገር ላይ በይበልጥ አጽንዖት ሰጥተዋል። ሕዝብ የሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያውን ውጤት በትዕግስት እንዲጠብቅ። ይህ ምን ማለት ነው ? የገንዘብ ባለሙያውን አቶ ኢድሪስ ሰዒድን ጠይቀናቸዋል።
"ይህ ማሻሻያ ያለምንም ህመም አይደለም [የሚፈፀመው]። የራሱ የሆነ ህመም ስለሚኖረው ነው ትንሽ ታገሱ የሚለውን የተናገሩት" የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያው ዓለማ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ፣ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ መፍጠር፣ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን ብሎም የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ የሚሉትን በምክንያትነት አስቀምጧል። ሁለቱ ግዙፍ የዓለም የገንዘብ ተቋማት - አይ.ኤም ኤፍ. እና ዓለም ባንክ ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ የበላይ ኃላፊ ሆነው የመሯቸው አውሮፖች እና አሜሪካዊያን ብቻ ናቸው።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ