1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የገንዝብ ድርጅት ለኢትዮጵያ 345 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቀደ

ማክሰኞ፣ መስከረም 21 2017

የአበዳሪው ድርጅት IMF ሰራተኞች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መክረው በደረሱበት ስምምነት በአራት ዓመት ውስጥ ከሚለቀቀው 3.4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የብድር አለቃቅ ውስጥ አሁን ላይ 345 ሚሊየን ዶላር ወይም የአጠቃላይ ብድሩ 10 በመቶ ገደማ ለመልቀቅ የሚያስችለው ውሳኔ ላይ ደርሷል

የኢትዮጵያ መንግሥትና የዓለም አቀፉ አበዳሪ ድርጅት ተወካዮች ለረጅም ጊዜ ሲደራደሩ ነበር
የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ) አርማ።ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ካቀደዉ ብድር 10 በመቶዉን ለመስጠት ወስኗል።ምስል Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance

የዓለም የገንዝብ ድርጅት ለኢትዮጵያ 345 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቀደ

This browser does not support the audio element.

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ኢትዮጵያ ከጠየቀችዉ የ3.4 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ብርድር  10 በመቶዉን ወይም 345 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ለማበደር ወስኗል።ዓለም አቀፉ አበዳሪ ድርጅቱን ብድሩን ለመስጠት የወሰነዉ የድርጅቱ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በተከታታይ ከተደራደሩ በኋላ ነዉ።የድርድሩን ሒደት የተከታታሉ ባለሙያዎች እንዳሉት ብድሩ መፈቀዱ ኢትዮጵያ ከአይ ኤም ኤፍ ጋር ያላት ግንኙነት መሻሻሉን ጠቋሚ ነዉ።

የአበዳሪው ድርጅት IMF ሰራተኞች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መክረው በደረሱበት ስምምነት በአራት ዓመት ውስጥ ከሚለቀቀው 3.4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የብድር አለቃቅ ውስጥ አሁን ላይ 345 ሚሊየን ዶላር ወይም የአጠቃላይ ብድሩ 10 በመቶ ገደማ ለመልቀቅ የሚያስችለው ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ አበዳሪው ድርጅት በዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫም ኢትዮጵያ ከባለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ የውጪ  ምንዛሪ ተመንን ለገቢያው ሁኔታ መተውን ጨምሮ አገር በቀል ያለችውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ በአዎንታዊነት መመልከቱን አሳውቋል፡፡ በማሻሻያው በባንኮች የምንዛሪ ተመንና በትይዩ የውጪ ምንዛሪ ገቢያ መካከል የነበረው ሰፊ ልዩነት አሁን በእጅጉ መጥበቡንም አይ.ኤም.ኤፍ መገምገሙን አስረድቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ።የዓለም ገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ ብድር ለመስጠት የወሰነዉ ኢትዮጵያ የብርን የምንዛሪ ዋጋ ከቀነሰች በኋላ ነዉምስል Seyoum Getu/DW

አይ ኤም ኤፍ ማሻሻያውን እንዴት ገመገመው?

የኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬታማ አተገባበርን ያሳየ የተባለው ይህ ሂደት ለማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት፣ ለውጪ ምንዛሪው ማግኛ እና ለአጠቃላይ የኢኮኖሚው እድገት ፋይዳው ጉልህ መሆኑንም አበዳሪው ድርጅት አሳውቋል፡፡ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናን መሃምድ አይ ኤም ኤፍ በመጀመሪያ ዙር ከለቀቀው 1 ቢሊየን ዶላር በተጨማሪ አሁን ከማሻሻው ጅማሮ ሁለት ወራት በኋላ የለቀቀው 345 ሚሊየን ዶላር ማሻሻያውን በአዎንታዊነት አምኖ መቀበሉን የሚያስረዳ ነው ብለውታል፡፡ “አይ ኤም ኤፍ 3.4 ቢሊየን ዶላሩን አንድ ጊዜ አይደለም ሚለቀው፤ በሂደት ነው” ያሉት ባለሙያው ኢትዮጵያ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ገቢራዊ ማድረግ ስትጀምር የአንድ ቢሊየን ዶላር ብድር መለቀቁንም አስተውሰዋል፡፡ አሁን ላይ በሁለተኛ ዙር የተለቀቀው ተጨማሪ ገንዘብም ድርጅቱ በኢትዮጵያው የኢኮኖሚ ማሻሻያው እምነት ማሳደሩን የሚያሳይም ነው ብለውታል፡፡

የኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤት በአይ ኤም ኤፍ እይታ

እንደ የዓለማቀፉ ገንዘብ ድርጅት (IMF) ሰሞነኛ መረጃ አልቫሮ ፒሪስ በተባለው የድርጅቱ ተወካይ የተመሩ ሰራተኞቹ ከመስከረም 07 እስከ 16 ፤ 2017 ኣ.ም. ለዘጠኝ ቀናት ግድም አዲስ አበባ ውስጥ ቆይተው ከኢኮኖሚው ማሻሻያ ወዲህ ቅድሚያ ተሰጥቶአቸው ማሻሻያ የተደረገባቸው ፖሊሲዎችን መገምገማቸውን፤ ብሎም ከሃላፊዎች ጋር መምከራቸውን አመልክቷል፡፡ የተደረገው ግምገማም በአዎንታዊነት በመወሰዱ US$345 ሚሊየን በቀጣይ ለኢትዮጵያ እንደሚለቀቅ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ ድርጅቱ በግምገማው ከሪፎርሙ ወዲህ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከሚስተዋል ውስን ልዩነት ውጪ የአንድ ዶላር ዋጋ ከብር አንጻር ከ57 ተነሰርቶ ወደ 112 ብር ግድም እንዲመነዘር መሆኑ ከትይዩ ገቢያው ጋር የነበረውን ሰፊ ልዩነት በእጅጉ ማጥበቡን ጠቅሶ ይህም አደገኛ ያለውን የውጪ ምንዛሪ እጥረቱን በመቅረፍ ለኢኮኖሚው አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክታል ነው ያለው፡፡

እንደ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ስርዓት ባለሙያው አብዱልመናን መሀማድ በቀጣይም የኢኮኖሚ ማሻሻያው ቀጣይ እርምጃዎች እየታዩ ቃል የተገባው የብድር መጠን በቀጣይ የሚለቀቅ ይሆናል፡፡ “በተለይም የውጪ ምንዛሪው የፖሊሲ ለውጥ እየሄደበት ያለው እርምጃ እንደ ዋነኛ ለውጥ ታይቶ ነው በኤ ኤም ቀጣይ ምዕራፍ ገንዘቡ የተለቀቀው” ብለዋል፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) ለኢትዮጵያ የ345 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ወስኗል።ምስል Muhammed Semih Ugurlu/AA/picture alliance

የዋጋ ንረትን ማረጋጋት፤ ቀጣዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያው የቤት ስራ?

አገር በቀል ኢኮኖሚክ ሪፎርሙ በቀጣይ ማክሮኢኮኖሚውን በማረጋጋት የዋጋ ንረትን እንደሚቀንስም በአበዳሪ ድርጅቱ እምነት አለ፡፡ ይህ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት በተለይም በበርካታ መንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ላይ የአገልግሎት ክፍያ ከፍተኛ ጭማሪ በማድረጉ ነው፡፡ ኢሚግሬሽን አገልግሎት፣ የኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮሚዩኒኬሽን፣ አየርመንገድ እና የተሸከርካሪ ፍቃድና ቅጣት እርከኖች ጭምር የአገልግሎት ክፍያቸው በብዛት እጥፍና ከዚያም በላይ ጨምሯል፡፡ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ስርኣት ባለሙያው ግን የተበላሸ ያሉት የውጪ ምንዛሪውን እልባት መስጠት ከዚህም በላይ አንገብጋቢ ነበር፡፡ “የውጪ ምንዛሪ ስርዓቱ በጣም ከመበላሸቱ የተነሳ የባንኮችና ትይዩ ገቢያ ልዩነት ሰፍቶ ነበርና ያ ደግሞ ባንኮችና የፋይናንስ ስርኣቱን ለከፍተኛ ብልሹ አሰራር ብሎም ሙስና ዳርጎ ነበር” በማለት ይህን እልባት መስጠት ቀዳሚ መሆኑን በአግባብነቱ አንስተውታል፡፡

አይ ኤም ኤፍ በሰሞነኛው የኢትዮጵያ ቆይታው ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ እና ምክትላቸው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዲሁም ከብሔራዊ ባንክ ገዢው ማሞ ምህረቱ ጋር ውጤታማ ያለውን ውይይት ማድረጉንም አስረድቷል፡፡

ስዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW