የዓሊ ቢራ ሽኝትና ቀብር
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 29 2015
ኢትዮጵያዊዉ ዕዉቅ ድምፃዊ ዓሊ መሐመድ ቢራ ዛሬ በትዉልድ ከተማዉ ድሬዳዋ ዉስጥ ተቀበረ። ዓሊ ስምዝና ካተረፈበት ከኦሮሚኛ በተጨማሪ በሰባት የሐገር ዉስጥና የዉጪ ቋንቋዎች ከ60 ዘመናት በላይ ያዜመ ተወዳጅ ድምፃዊ፣ የግጥምና የዜማ ደራሲ፣ ጊታር ተጫዋችም ነበር። የዓሊ አስከሬን ወደ ድሬዳዋ ከመጓዙ በፊት አዲስ አበባ ዉስጥ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ወዳጅ ዘመዶቹና በርካታ አድናቂዎቹ በተገኙበት ሽኝት ተደርጎለታል። ዓሊ በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ያረፈዉ ባለፈዉ እሑድ ነዉ። 75 ዓመቱ ነበር።
የክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራ ለ60 ዓመታት በዘለቀው የሙዚቃ ህይወቱ ስለነጻነት፣ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት፣ ስለፍቅር፣ ስለተፈጥሮ እና ስለአገር በርካቶች በሚወዱት አንጸባራቂ ድምጹ አንጎራጉሯል፤ በጉልህም ታውቆበታል፡፡ ለዓመታት ፀንቶበት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሆስፒታል ያቆየው ህመሙ ከትናንት በስቲያ እሑድ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ህይወቱ እንዲያልፍ ምክኒያት ሆኗልም፡፡
አቀላጥፎ መናገር በሚችለው ስድስት ቋንቋዎች 267 ሙዚቃዎችን ዘፍኖ በ75 ዓመቱ ይህችን ዓለም የተሰናበተው አሊ ዛሬ ስንብት እና የአስከሬን ሽኝት የተደረገለት በብሔራዊ ጀግንነት አሸኛኘት ስርዓት ነው፡፡
ጠዋቱን ቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኘው ከመኖሪያ ቤቱ ወደ አዲስ አበባ የተወሰደው የአሊ ብራ አስከሬን፤ ረፋዱን ብሔራዊ የሽኝት ስርዓት ወደ ተዘጋጀበት አዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ ደርሶ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ ባለሥልጣናት፣ የሙያ አጋሮቹ እና በርካታ አድናቂዎቹ በተገኙበት የሽኝት እና የክብር ስርዓት ተከናውኖለታል፡፡
በአሸኛኘት መርሃ ግብሩ ሙዚቀኞችን ወክለው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ፕሬዝዳንት የክቡር ዶ/ር ዳዊት ይፍሩ አርቲስት አሊ ብራን ስራዎቹ እንዳይሞቱ አድርጎ የሰቀለ ሙዚቀኛ ሲሉ አሞካሽተውታል፡፡
የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሃት ደግሞ አሊ ብራን ባለ ምጡቅ አዕምሮ የድንቅ ድምጽ ባለበት ሲል ነው የገለጸው፡፡ ባለሙያው አሊ ብራ ከሚዘፍንበት ቋንቋ ተናጋሪዎች ባሻገር ማንንም በአድናቆት ያሰለፈ የሙዚቃን ምስጥር ከመሰረቱ የተረዳ ባለሙያ ነው ብሎታልም፡፡
አሊ ቢራ በሙያው ለአገሩ ታላቅ ነገርን ያደረገ ሲሉ ያወደሱት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ናቸው፡፡ አቶ ሽመልስ “አርቲስቱን እራሱ ኢትዮጵያ ነው” ሲሉም ገልጸውታል፡፡
የእውቅ ድምጻዊ ሙዚቀኛ አሊ ብራ ብሔራዊ የአስከሬን አሸኛነት መርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲነባ አዳነች አቤቤ፣ የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ እና ሌሎች ባለሥልጣናት እና የሙያ አጋሮቹም ንግግርና ስንብት አድርገውለታል፡፡
ከአሊ ጋር ሙዚቃን ለመጫወትና በቅርበት የአብሮ መስራት እድል ካገኙ ድምጻውያን ደገሞ ድምጻዊት ሄለን በርሔ እና ድምጻሚ አቡሽ ዘለቀ ይገኛሉ፡፡ ሙዚቀኞቹም አሊን ታላቅ የሙዚቃ አባት ሲሉ ይገልጹታል፡፡
ለ6 አስርት ኣመታት ሙዚቃን በመጫወት ታላቅ እውቅናን ያተረፈው አሊ ቢራ ለሥራዎቹ ከ ጂማ እና ዲሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክቴሬት አግኝተዋል፡፡ ከዲሬዳዋ በመነሳትም በርካታ ውጣውረዶችን በማለፍ ከስውዲን-ሳውድ አረቢያ፣ ከአሜሪካ እና ካናዳ እስከ ተለያዩ ሃገራትም ተዘዋውሮ ኑሮ በመግፋት በመጨረሻም በአገሩ ለበክብር ሽኝት በቅቷል፡፡
ስርዓተ ቀብሩም ዛሬ ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ,ም ማምሻውን በትውልድ ስፍራው ዲሬዳዋ ለገሃሬ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የቀብር ስፍራ ተከናውኗል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ