1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ  

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ሰኔ 4 2013

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዳችን ሰሞኑን ኔዘርላንድስ ሄንገሎ ከተማ ውስጥ በ1500 ሜትር ከቤት ውጪ የሴቶች የሩጫ ውድድር የዓመቱን ምርጥ ሰዓት ያስመዘገበችው ፍሬወይኒ ኃይሉ ናት። ፍሬወይኒ በዚሁ ውድድር የራሷን ምርጥ ሰዓትም አሻሽላለች።

Freweyni Hailu
ምስል CTK Photo/Vladimir Prycek/'dpa/picture alliance

በ1500 ሜትር ሩጫ ተስፋ የተጣለባት አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ

This browser does not support the audio element.

ያለፈው የሳምንት መጨረሻ እና የዚህ ሳምንት መጀመሪያ በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ኔዘርላንድስ ሄንገሎ ከተማ ውስጥ በተካሄዱ ውድድሮች አቅማቸውን የፈተሹበት ነበር። አትሌት ለተሰንበት ግደይ ለሁለት ቀናት ብቻ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ በትውልድ ደግሞ ኢትዮጵያዊት በሆነችው ሲፋን ሀሰን ተይዞ የቆየውን የ10,000 ሜትር የዓለም ክብረወሰን ሰብራ የዓለም መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስባለች። ይሁንና ኔዘርላንድስ ሄንገሎ ከተማ ውስጥ በተካሄዱ የተለያዩ ሩጫዎች ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ስኬታማ ሆነዋል። ከነዚህ አንዷ የመካከለኛ ርቀት ሯጭ የሆነችው ፍሬወይኒ ኃይሉ ናት። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ስለ ስፖርት ዓለም ህይወቷ አጫውታናለች።
ፍሬወይኒ ማክሰኞ ማታ ኔዘርላንድስ ሄንገሎ ከተማ ውስጥ የተካሄደውን የ1500 ሜትር ውድድር ያሸነፈችው 3 ደቂቃ ከ 57 ሰከንድ ከ 33 ማክሮ ሰከንድ በመሮጥ ነው። ይህም ውጤት በዚህ በጎርጎሮሲያዊው 2021 ከቤት ውጪ ከተካሄዱ የሴቶች ውድድሮች ምርጥ የተባለው ሰዓት ነው። ፍሬወይኒን ለስኬት ያበቃት ሚስጥር « ተጋግዘን ስለሮጥን ፈጣን ሰዓት ለመሮጥ ችለናል» 
አብረዋት የሮጡት ድርቤ ወልተጂ ከዓለም ምርጥ ሰዓት 3ኛውን ቦታ ይዛ ስታሸንፍ፤ ለምለም ኃይሉ ደግሞ 5ኛውን ቦታ ለመያዝ ችላለች። ኢትዮጵያውያቱ በውድድሩ ሰዓት ተባብረው መሮጣቸው እና ፍሬወይኒ እንደምትለው በውድድሩ ቦታ የነበረው ምቹ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ያደረገችውም ልምምድ ትልቁን ሚና ተጫውቷል።  « ከነ ጉዳፍ ጋር ነው ልምምድ የማደርገው። ጎበዝ አትሌቶች ናቸው። » ትላለች። አብረን እንሰለጥናለን ያለቻት ጉዳፍ ፀጋይ የመካከለኛ እና ረዥም ርቀት አትሌት ናት። ባለፈው የካቲት ወር ፈረንሳይ ሀገር በተካሄደው የዓለም አትሌቲክ የቤት ውስጥ የ1500 ሜትር ውድድር አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችላለች።  ከፍሬወይኒ አርያዎች አንዷ ናት።  ሌሎች አርዓያዎቿ  ደግሞ ወደ ሩጫው ዓለም እንድትገባ ምክንያት ሆነዋል። « በወቅቱ ስለሩጫ ብዙ አላውቅም ነበር። የነገንዘቤን የነጥሩነሽን ዜና ስሰማ ነው እኔም ቀስ እያልኩ ወደ ሩጫ የገባሁት።» እነ ገንዘቤ እና ጥሩነሽ ዲባባ ናቸው ሯጭ እንድሆን አርዓያ የሆኑኝ የምትለው ፍሬወይኒ፤ ኋላም 800 ሜትር ለመሮጥ ወሰነች። ለምን ይህን እንደወሰነች ግን ዐታውቅም።  « እንዳይደክመኝ ብዬ ነው መሰለሽ። እኔንጃ። ከ 400 ጀመርኩ እና ከዛ ወደ 800 ቀየርኩ» በእርግጥ ፍሬወይኒ ከ400 ተነስታ ወደ 1500 መሸጋገሯ ጠቅሟታል እንጂ አልጎዳትም። በአንድ በኩል የምትሳተፍባቸውን የሩጫ ቡድን አይነቶች መጨመር ስትችል በሌላ በኩል ደግሞ ስኬቷም እየጨመረ ነው። ወጣቷ አትሌት ለ1500 ሜትር ሩጫዎች አዲስ ትሁን እንጂ እንደነገረችን ከሆነ በሩጫ ስትሳተፍ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። « ብዙ ውጤት አልነበረኝም እንጂ ቆይቻለሁ። አንድ ሰባት ዓመት ሆኖኛል።» በወቅቱ ሯጭ መሆን ቀላል ይመስላት የነበረችው ፍሬወይኒ ወደ ሩጫው ዓለም የገባችው እንደ በርካታ አትሌቶች ገና ትምህርት ቤት ሳለች ነው።
ፍሬወይኒ ተወልዳ ያደገችው መቀሌ አካባቢ ነው። ኑሮዋን በአዲስ አበባ ካደረገች ገና ግማሽ ዓመቷ እንደሆነም አጫውታናለች። « ትውልድ ቦታዬ ከከተማው አንድ 10 ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ ነው።  ወንድም እና እህቶች አሉኝ። ስምንት ነን። እኔ ደግሞ ሰባተኛ ልጅ ነኝ።» የ19 ዓመቷ ወጣት አትሌት «ቤተሰቦቼ ጎበዝ በርቺ እያሉ ያበራታቱኛል» ትላለች። የሩጫ ተሳትፎዋን የሚቃወም የለም። ፍሬወይኒ እስከ 10ኛ ክፍል ከተማረች በኋላ አሁን ትምህርቱን አቋርጣለች። ይህም ሩጫ እና ትምህርቱን አብሮ ማስኬድ ስለከበዳት ነው።  ትኩረቷን በአንድ ነገር ላይ ያደረገችው ፍሬወይኒ ዘንድሮ በ800 አንድ ጊዜ በ1500 ሜትር ደግሞ ሁለት ጊዜ ልታሸንፍ ችላለች። ከእነዚህ ውድድሮች አንዱ ባለፈው ግንቦት ወር በቼክ ሪፐብሊክ ኦስትራቫ ያሸነፈችው ነው። 
ፍሬወይኒ እንደሷ መሮጥ የሚፈልጉ ወጣቶችን ጠንክረው እንዲሰሩ ትመክራለች።  «ሩጫ ብዙ ውጣ ውረድ አለው። በአንድ ጊዜ ውጤት አይመጣም። አሰልጣኝ የሚሉትን መስማት ያስፈልጋል። ዕረፍት ማድረግ ያስፈልጋል። ምግብም እንደዛው። ያንን ካደረጉ ያሰቡበት መድረስ ይችላሉ» የፍሬወይኒ የወደፊት ሕልም በኦሎምፒክ የዓለም ሻምፒዎና ተሳትፋ ሜዳሊያ ማግኘት ነው። ለዚህም ባለፈው ማክሰኞ ያስመዘገበችው ውጤት የግል ጥሩ ውጤቷ ብቻ ሳይሆን በኦሎምፒክ ለመሳተፍ የሚያስችላትም ነው። እስከዛው እሷም ሌሎችን እንደምትመክረው ጠንክራ መስራት ይጠበቅባታል።

ምስል Privat
ምስል CTK Photo/Vladimir Prycek/'dpa/picture alliance

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW