1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የዓመቱ ምርጥ መጽሐፍ» የኦነግ ባለሥልጣን በእስር ላይ ሆነው የጻፉት

ዓርብ፣ ኅዳር 20 2017

ከጥቂት ወራት በፊት ከእስር ከተለቀቁ ሰባት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ለሚ ቤኛ እስር ላይ ሆነው የጻፉት መጽኃፍ ለውድድር ቀርቦ በዓመቱ ምርጡ ተብሎ ተመረጠ።

የዳያ መጽሐፍ ደራሲ ለሚ ቤኛ
የዳያ መጽሐፍ ደራሲ ለሚ ቤኛ ምስል Seyoum Getu/DW

«የዓመቱ ምርጥ መጽሐፍ»

This browser does not support the audio element.

በተማሪዎች አመጽ ላይ በማጠንጠን የኦነግ ባለሥልጣን እስር ላይ ሆነው የጻፉት «ዳያ» የተባለው ታሪካዊ ልብወለድ መጽሐፍ በጎርጎሮሳዊው 2024 በአፋን ኦሮሞ ከተጻፉ በርካታ መጽሐፍት ምርጡ ነው ተብሎ የሽልማት እውቅና ያገኘው በኦሮሞ ደራሲያን ማሕበር ነው።

ፖለቲከኛው በእስር ላይ ሆነው በማስታወሻ ደብተራቸው ላይ የጻፉት ረቂቅ ጽሑፍ ወደ ውጪ አገር ተልኮ በመጽሐፍ እስኪታተም ድረስም ከእስር አልተለቀቁም። «እኔ እስር ቤት ሆኜ የጻፍኩት ሁለት መጽሐፍ ነው። ሁለቱም የተጻፉት በአፋን ኦሮሞ ነው። አንደኛው የኦሮሞ መሠረታዊ ጥያቄ የሚል የፖለቲካ መጽሐፍ ሲሆን ሁለተኛው ዳያ የሚል መጠሪያ የሰጠሁት ታሪካዊ ልብወለድ መጽሐፍ ነው» ብለዋል።

ሁለቱንም መጽሐፍት በጎርጎሮሳዊው 2022 መጻፋቸውን የሚገልጹት ለሚ «ዳያ» የተባለው ታሪካዊ ልብወለድ በ2023 መጨረሻ ታትሞ በመውጣት ዘንድሮ ለውድድር በቅቶ ማሸነፉን አስረድተዋል። «መጽሐፉን የጻፍኩት ለወንድሜ ማስታወሻ እንዲሆን ነው» የሚሉት ፖለቲከኛው በእስር ላይ ሳሉ «ባለ ብሩህ አዕምሮ» ያሉት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የነበረ የ18 ዓመት አዳጊ ወንድማቸው መገደሉን አስታውሰዋል። በመጽሐፉም የተማሪዎች አመጽ ሁናቴዎች በስፋት እንደተዳሰሱ ነው ያስረዱት።

ለመጻፍ የነበረው ውጣውረድ

የተራዘመ እስር ላይ ከነበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ፖለቲከኞች አንዱ የነበሩት አቶ ለሚ ቤኛ በእስር ቤት ቆይታቸው በተለያዩ ስፍራዎች እየተዘዋወሩ ሲታሰሩ እንደነበር አይዘነጋም። በመሆኑም ፖለቲከኛው ለእውቅና ጭምር የበቃውን ይህን መጽሐፍ ሲጽፉ ምቹ ሁኔታስ ነበር ወይ ተብለው ተጠይቀው ሲመልሱ፤ «እውነት ለመናገር በተለይም የመጀመሪያው ሁለት ዓመታት የነበርንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነበር። እኔ ራሴ ወደ 15 ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ተዘዋውሬ ታስሬያለሁ። ያ ጊዜ እንኳን አሰላስሎ መጽሐፍ ለመጻፍ ለማንበብም አስቸጋሪ ነበር። ነገር ግን የመጨረሻዎቹን ሁለት ዓመታት አንድ ቦታ ቡራዩ ፖሊስ ጣቢያ የተቀመትንበትን አጋጣሚ ነው የተጠቀምኩበት» ብለዋል።

የ«ዳያ» ትኩረት

ጸሐፊው እንደሚሉት ዳያ ማለት ራዕይ ማለት ነው። «እኛ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ስናካሄድ ራዕይ ነበርን። ለሕዝባችን ነጻነት፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲ፤ያንን ራዕይ ይዘን ነው የተነሳነው። እኔ በብዛት ሕይወቴን ያሳለፍኩት በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ነው። የዛሬ የፖለቲካ አመለካከቴም ከዚያ የተቀረጸ ነው። ያንን ራዕይ ይዘን ደግሞ የተሳካ ነገር ሠርተናል ማለት እችላለሁ። ምክንያቱ ዛሬ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ማንነቱን እንዲናገር ያ አግዞታል። እናም ያንን ራዕይ ለማስቀጠል በማሰብ ነው ለመጽሐፉ ይህንን ስም የሰጠሁት» ብለዋል።

ለዓመታት በእስር ላይ የቆዩት የመጽሐፉ ደራሲ ለሚ ቤኛ «እኛ የታሰርነው ከቤት ተወስደን ሲሆን ምንም ወንጀል ውስጥም አልተሳተፍንም» ነው ያሉት። ምስል Seyoum Getu/DW

የመጽሐፉ ለሽልማት መብቃት የፈጠረው ስሜት

ጸሐፊው «አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ጻፍኩ» ያሉት መጽሐፉ ለሽልማት እና እውቅና መብቃቱ ልዩ የደስታ ስሜት እንደፈጠረለት ያስረዳል። አወዳዳሪ አካል የኦሮሞ ደራሲያን ማሕበርም ይህን መጽሐፍ በምርጥነት ሲመርጥ መጽሐፉን ለውድድር ያቀረቡት፤ አንድ መጽሐፉን ያነበቡ ግለሰብ እንጂ እሳቸው በወቅቱ ከእስር ስላልተለቀቁ ስለውድድሩም የሚያውቁት እንዳልነበርም ገልጸዋል። ባለፈው ሳምንት መጽሐፉ ለሽልማት እንዳበቃቸው እስከተነገራቸው ድረስም ምንም መረጃ እንዳልነበራቸውም ነው የገለጹት።

ስለእስር ቤት ቆይታቸውም በአጭሩ ያጋሩን ፖለቲከኛ እና ጸሐፊ ለሚ ቤኛ በ2012 ዓ.ም. ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስደው መታሰራቸውን ነው የገለጹት። «እኛ ታሰርነው ከቤት ተወስደን ሲሆን ምንም ወንጀል ውስጥም አልተሳተፍንም» ሲሉም የነበረውን ለማስረዳት ሞክረዋል። «ስንታሰርም ወንጀለኛ ናችሁ ያለን አካል የለም። መደበኛ ምርመራም አልተካሄደብንም» ብለዋል። ከእሳቸው ጋር የታሰሩ አብዛኞቹ የኦነግ አመራሮች መደበኛ ፍርድ ቤትም እንዳልቀረቡ ያስረዱት ለሚ፤ «በአደራ ነው አብዛኛው አብዛኛውን አራት ዓመት ያሳለፍነው፤ ማን በአደራ እንዳስቀመጠን ባናውቅም» ነው ያሉት።  ከባልደረባቸው ዳዊት አብደታ ጋር ግን ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አስታውሰው በተደጋጋሚ እስከ ሰበር ፍርድ ቤት በነጻ መሰናበታቸውንም ገልጸው፤ ያም ሆኖ ግን ያለ ፍርድ አራት ዓመት እስር ላይ መቆየት ፈተናው ቀላል እንዳልነበር ተናግረዋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW