የዓመት በዓል ገበያ በደሴ ከተማ
ረቡዕ፣ ጳጉሜን 5 2017
በደሴ ከተማ የዘንድሮዉ የዓመት በዓል ገበያ ከቀዳሚዎቹ ዓመታት በእጅጉ መወደዱን ሸማችች አስታዉቀዋል። ከነዋሪዎችዋ አንዷ «ዓመት በዓል ባይመጣ ይሻላል» በማለት የዋጋ ንረቱን አማርረዋል። እዚያዉ ደሴ ከተማ አጠገብ የተጠለሉ አንድ ተፈናቃይ ደግሞ «ከሞቱት ሰዎች እንሻላለን» ይላሉ። የመንግሥት ባለሥልጣናት በዓሉንና የደሞዝ ጭማሪን አስታክከዉ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉትን እየተቆጣጠሩ መሆኑን አስታዉቀዋል ።
አዲሱን ዓመት ለመቀበል በዋዜማ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የጎመን ምንቸት ውጣ የገንፎ ምንቸት ግባ እያሉ መጭውን ዘመን የሰላም እና የምርት ዘመን እንዲሆን ይመኛሉ፡፡ በአዲስ ዓመት ቤት ከማስዋብ እስከሚበላ እና እሚጠጣ ለመሸመት ገበያ መውጣት የተለመደ ነው በማለዳ የተገኘንበት የደሴ ከተማ ሮቢት የገበያ ስፍራም ሻጭ እና ገዥን እያገበያየ አርፍዷል ዘንድሮ ከጥንት የመጣ ልማድ ነውና በአዲሱ አመት ልማዳችንን አታስቀርብን ብለን ገበያው ቢወደድም በአቅማችን እንገበያለን ይላሉ አስተያየታቸውን ለዶቼቬለ የሰጡ የደሴ ከተማ ነዋሪ ።
“አዲስ አመት ዝግጅቴ ጥሩ ነው የአዲ አመት ገበያ ግን ከባድ ነው ግን ቢሆንም የዘመን መለወጫ በመሆኑ የግድ ያለንን ተሯሩጠን እንገዛለን”
ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየበት የበአል ገበያ
የበርካታ ሰዎች የበአል ግብይት ትኩረት የሆነውለእርድ የሚሆኑ እንስሳቶችን መግዛትን በዚሁም በሮቢት ገበያ ደርቷል ከ300,000 (ከሶስት መቶ ሽህ ብር) እስከ 30 ሽህ ብር ከበሬ እስከ ጥጃ ይገዛሉ በጉ ፣ ፍየሉ፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው መሸጫ ዋጋ መጨመር ታይቶበታል ይላሉ ገበያተኞቹ፡፡
“ ደሴ ላይ ጥሩ ነው የበግ ገበያም ከፍተኛ ከ35,000 (ከሰላሳ አምስት ሽህ ብር) እስከ 40,000 (አርባ ሽህ ብር) ዝቅተኛ ከ5000 እስከ 10,000 ይሸጣል፡፤ ከብት ትልቁ 1ኛ በሬ ከ300,000 እስከ 350,000 ይሸጣል፡፡ ዝቅተኛ ከ70,000 እስከ 50,000 ይገኛል”
ትርንጎ ፣ ጭሱ ፣ አደሱ ፣ አሪቲ ፣ አሽኩቲ ለበአሉ ድምቀት የሚገበዩ እናቶችም የሽንኩርት የእንቁላል እና የዶሮ ዋጋ ጭማሪ ያለው ቢሆንም ቤት ያፈራውን ዳቦውን ጠላውን አዘጋጅተን አዲሱን አመት በደስታ ልንቀበለው ወደናል ይላሉ
“ዶሮውን 2000 ብር ገዝተናል ሽንኩርት 120 ብር እያሉ ነው ግን እገዛን ነው ለበአሉ ዝግጅታችን ጥሩ ነው ፋፎ፣ ኑግ ፣ ዳቦ ፣ ጠላው ተዘጋጅቷል”
በበአል ግብይት ወቅት የመግዛት አቅም ያጡ የማህበረሱብ ክፍሎች
ለበአሉ የሚሆን የእርድ እና ሌሎች ግብአቶችን ለመሸመት መተው ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ እንደተቸገሩ የነገሩ ገበያተኞችን በአሉ በዋጋ መወደድ ምክንያት ቀዝቅዟል ይላሉ፡፡
“በአሉ ብዙ አያረካም በአሉ ባይመጣ ብያለሁ እየተጨናነቅን ነው በጣም እየጨነቀን ነው እንደፈለግን እንዳቅማችን መግዛት አልቻልንም አናርድም አንልም ግን በቃ ኪሎ ስጋ ለመግዛት አስቸጋሪ ነው”
በደሴ ከተማ የከተማው ነዋሪ አዲሱን አመት ለመቀበል ሽር ጉድ በሚልበት በዚህ ጊዜም ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢ ተፈናቅለው በደሴ ገራዶ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ ተፈናቃዮችን አዲሱን አመት ለመቀበል ያላቸውን ዝግጅት ጠየኳቸው፡፡
“ ቀበሌዎች ከየመንደሩ አሰባስበው ሁለት ወይፈን ሰተውናል ሌላ ነገር የለም ዋናው ነገር ሰላም ሆነን ማደራችን ነው በቤታችን ብዙ ነገር ነበረን እየተጠራራን የምንቃመስበት ብዙ ደስታ የምናሳልፍበት ነበር በአሉ ዙሮ ግን ከሞቱን እንሻላለን”
የደሴ ከተማ ንግድ እና ገበያ ልማትመምሪያ ኃላፊ አቶ ዮናስ እንዳለም 400,000 (አራት መቶ ሽ) ሊትር ዘይት ዱቄት እንቁላልን ጨምሮ ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ጀምሮ የዋጋ ንረት የሚፈጥሩ ህገወጦች ላይ እርምጃ እየወሰድን ነው ይላሉ፡፡
“እንቁላል፣ በርከት ያለ ዶሮ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ተሞክሯል ለከተማው ማህበረሰብም 400,000 (አራት መቶ ሽ ሊትር ዘይት) በማህበራት በኩል አሰራጭተናል፡፡ በአሉን ምክንያት በማድረግ የደመወዝ ጭማሪውን ለመጠቀም የዋጋ ጭማሪው እንዳይመጣ በየቀኑ የክትትል ስራ እየሰራን ነው፡፡”
ኢሳያስ ገላዉ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ