1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የዓሳ ሀብት አጥቃቀም በባሕር ዳርና በጋምቤላ

ዓለምነው መኮንን
ሐሙስ፣ መስከረም 8 2018

በአማራ ክልል ጣና ሐይቅ ባልተፈቀደ መረብ ዓሳ ማጥመድና ሌሎች ምክንያቶች ሀብቱን እያመናመኑት እንደሆነ ሲገለፅ፣ በጋምቤላ ክልል ደግሞ በመሠረተ ልማት ችግሮችና በዓሳ ማጥመጃና ማቀዝቀዣ ግብዓቶች እጥረት ሐብቱ እየባከነ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

ጣና ሐይቅ
ከጣና ሐይቅ በየዓመቱ እስከ 12 ሺህ ቶን ዓሳ ምርት ይገኝ እንደነበር አንድ የዓሳ ተመራማሪ ገልጠዋልምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የዓሳ ሀብት አጥቃቀም በባሕር ዳርና በጋምቤላ

This browser does not support the audio element.

በጣና ዳርቻ ዓሳ አጥበውና በልተው ለመሸጥ ሲዝጋጁ ያገኝናቸው አንድ እናት እንደነገሩን አሁን አሁን የዓሳዎች አካለ መጠን በጣም እየቀነሰ ነው፣ አካላቸውም ብቻ አይደለም ከሐይቁ የሚገኝ የዓሳ ምርትም ከጊዜ ጊዜ እየቀነሰ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል፣ ለዚህም ዓሳዎች መጠናቸው ሳያድግ እየወጡ ለገባያ በመቅረባቸው ሳይሆን እንዳልቀረ ግምታቸውን ነግረውናል፡፡

“በጣና ሐይቅ የዓሳ ሀብት እየቀነሰ ነው” የዓሳ ተመራማሪ

የባሕር ዳር ዓሳና የውሀ ውስጥ ህይወት ምርምር ማዕከል ተመራማሪና የዓሳ ሀብት አጠቃቀም አስተባባሪ አቶ ብንያም ኃይሉ በጣና ሐይቅ ከፍተኛ የዓሳ ሀብት ክምችት ቢኖርም ሀብቱን በአግባቡ መጠቀም ባለምቻሉ ሀብቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከጣና ሐይቅ እስከ 20ሺህ ቶን በዓመት የዓሳ ሀብት መጠቀም የሚያስችል አቅም ቢኖረም አሁን አሁን ግን ምርቱ እየቀነሰ እንደሆነ ነው ያስረዱን፡፡ በ2000 ዓም  እስከ 12 ሺህ ቶን በዓመት የመጠቀም አቅም የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች አሁን በዓመት የሚገኘው ምርት ከ7ሺህ እስከ 9 ሺህ ቶን መውረዱን ተናግረዋል፡፡

ለምርቱ መቀነስ ምክንያቶቹ በርካታ መሆናቸውን የገለፁልን አቶ ብንያም፣ በተለይ አንድ ዓሳ ራሱን ሳይተካ መያዝና መጠቀም ዝርያውን ከሚቀንሱ ምክንያቶች ዋናው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ያልተፈቀዱ መረቦችን መጠቀም ለዓሳ ምርት መቀነስ አንዱ ተጠቃሽ ነው” ባለሙያ

በዓሳ መሸጫ ቦታዎች በጣም አካለ መጠናቸው ያነሱ ዓሳዎች በብዛት እንደሚታዩ የተናገሩት ተመራማሪው፣ ይህም የሆነው ባለተፈቀደ የዓሳ ማውጫ መረቦች የተያዙ መሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል፣ ተጠቃሚው ህብረተሰብ ያልተፈቀዱ በጣም ጠባብ መረቦችን እየተጠቀመ ዓሳዎችን አውጥቶ የሚጠቀም ከሆነ ሀብቱ እስከአካቴው ከሐይቁ የማይኖርበት ጊዜ እንደሚኖርም ባለሙያወ አስጠንቅቀዋል፡፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የዓሳ ሀብት ቢኖርም በመሰረተ ልማት ችግር፣ በማቀዝቀዣ መሳሪያዎች እጥርት በዘማናዊ ጀልባዎች አለምኖርና በሌሎች ምክንያቶች ሀብቱን መጠቀም እንዳልተቻለ በጋምቤላ ጉር የወጣቶች ሁለገብ የዓሳ አምራቾች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ኦሞድ ኦሞድ ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ኦሞድ በማህበራቸው አማካይነት አዲስ አበባ ለሚገኘው ጋምቤላ ሆቴልና ኦሮሚያ ክልል መቱ ከተማ ምርት እንደሚልኩ ጠቁመው ሆኖም በክልሉ ሠፊ የዓሳ ምርት በመኖሩ በዘመናዊ አሰራር መታገዝ ከተቻለ ምርቱን ከኢትዮጵያ አለፎ ወደ ውጪ መላክ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ አሁን ግን ሠፊ የዓሳ ሀብት ከውሀ አካላት ሳይወጣ በውሀ ውስጥ ያለጥቅም ቀርቷል ነው ያሉት፡፡

አንድ ዓሳ ራሱን ሳይተካ መያዝና መጠቀም ዝርያውን ከሚቀንሱ ምክንያቶች ዋናው መሆኑን አንድ ተመራማሪ ተናግረዋል። ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

“በጋምቤላ በዓመት 17ሺህ ቶን ዓሳ ማምርት ቢቻልም አሁን እየተመረተ ያለው ከ5ሺህ ቶን አይበልጥም” የጋምቤላ ክልል እንስ ሳትና ዓሳ ህብት ልማት ቢሮ የጋምቤላ ክልል የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ለማት ቢሮ የእንስሳት እርባታ ተዋፅዖና መኖ ልማት ዳይሬክተር አቶ አንተነህ ተስፋዬ በክልሉ እስከ 17 ሺህ ቶን ዓሳ የማምርት አቅም ቢኖርም በግብዓት እጥረት ምክንያት የሚመረተው ካዚያ በጣም ያነሰ ነው ብለዋል፡፡

“በ2017 ዓም የተመረተው  4ሺህ 595 ቶን ብቻ ነው” ሲሉ አክለዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ዓሳ በየመንገዱ በብዛት ቢኖረም የመንገድ ችገሮች በመኖራቸው ሀብቱን ወደ ማዕከል ማምጣት እንዳልተቻለ ገልጠዋል፡፡

ሀብቱን በስፋት ለመጠቀም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል አክለውም፣ “ ዓሳ ላማስገር የሚያስፈልጉ ጀልባዎችና መረቦች፣ ምርቱ ሳይበላሽ እንዲቆይ የሚያደርጉ ፍሪጆች፣ የማያቋርጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ መንገዶችና ሌሎች መሠረተ ለማቶች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል” ነው ያሉት፡፡

በክልሉ በሚገኙ ወንዞችና ሐይቆች  107 ዓይነት የዓሳ ዝርያዎች ሲኖሩ 20 የሚሆኑት ለገብያ የሚቀርቡ እንደሆኑ ተነግሯል፣ በጋምቤላ በሚገኙ ይውሀ አካላት ከ150 እሰከ 200 ኪሎግራም የሚመዝን ዓሳ ይገኛል፡፡

ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW