የዓይነ-ማዝን ማጥፋት ይቻላል
ማክሰኞ፣ የካቲት 8 2008የዓይነ- ማዝ ወይም ትራኮማ በሞቃት አካባቢ ከሚገኙና የተዘነጉ ከሚባሉ 17 በሽታዎች አንዱ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ድርጅቱ የዓይነ-ማዝን ጨምሮ 17ቱንም በሽታዎች እስከመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2020 ድረስ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ወይም ፈፅሞ ለማጥፋት አቅዷል።
የዓይነ-ማዝ በመላዉ ዓለም በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ 1,8 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎችን ለዓይነ ስዉርነት የዳረገ በተለይም ድህነት ባጠቃቸዉ የተለያዩ ሃገራት ገጠራማ አካባቢ የተስፋፋ በሽታ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃዎች ያስረዳሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓይነ-ማዝ የተስፋፋባቸዉን አካባቢዎች በካርታ ለማስፈር ቅኝት ያካሄደዉ ፕሮጀከት እንደሚለዉ፤ በሽታዉ ከአንዱ ሰዉ ወደሌላዉ በልብስ፤ በእጅ ንክኪ ወይም በዝንብ አማካኝነት በቀላሉ ይተላለፋል። ለመስፋፋቱ በዋነኛ ምክንያት የንፁሕ ዉኃ አቅርቦት ማጣት እና የአካባቢ እና የግል ንፅሕና አለመጠበቅ ይጠቀሳሉ። እንደዘገባዉ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ዉስጥ በበሽታዉ በሚያዙት ቁጥር በአስደንጋጭ መልኩ እየጨመረ ነዉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጂ በዓይን ህክምና ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ትልቅ ሰዉ ተሾመ የዓይነ-ማዝ በሀገሪቱ ዋነኛ የዓይነስዉርነት መንስኤ መሆኑን ቢገልፁም ቁጥሩ እየጨመረ ነዉ የሚለዉ ለማለት ግን ያዳግታል ይላሉ።
ሳይትሴቨር የተሰኘዉ መንግሥታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት ያካሄደዉ ጥናት እንደሚለዉ የዓይነ-ማዝ ሊስፋፋባቸዉ ይችላል ተብለዉ በተገመቱ እንደናይጀሪያ፤ ላኦስ፣ ካምቦዲያ እና ግብፅ የመሳሰሉ ሃገራት በበሽታዉ የተጎዱት ሰዎች ቁጥር ቀንሶ ነዉ የተገኘዉ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይም በአንዳንድ አካባቢ ከማኅበረሰቡ ሃምሳ በመቶዉ የዓይነ-ማዝ ተጠቂ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል። ዶክተር ትልቅ ሰዉ ተሾመ ዘገባዉ ትክክል ነዉ ይላሉ።
ትራኮማ ወይም የዓይነ-ማዝን በቀጣይ አምስት ዓመታት ዉስጥ ፈፅሞ ለማጥፋት የተቆረጠ ይመስላል። በሽታዉ የሚገኝባቸዉን አካባቢዎች በማጥናት ይዞታ እና የጉዳት ስፋቱን የመዘገቡት ወገኖች ይህን ማድረጉ አይከብድም የሚል ተስፋ ሰንቀዋል። ዋቢም ይጠቅሳሉ፤ ፈንጣጣን ከዓለም ማጥፋት ተችሏል፤ ባይ ናቸዉ። እናም የዓይነ-ማዝም ከጥቂት ዓመታት በኋላ የዓይን ብርሃን የማሳጣት አቅም አይኖረዉም። ይቅናቸዉ። ዝርዝሩን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ