የዛክሰን አንሀልት ምርጫ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 1 2013ከትናንት በስተያ እሁድ «ዛክሰን አንሀልት» በተባለው የጀርመን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት በተካሄደው ምርጫ ወግ አጥባቂው የጀርመን «ክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ» ያልተጠበቀ ውጤት አግኝቷል። ውጤቱ የመስከረሙ የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ውጤት ምልክት ተደርጎ ተወስዷል።«ዛክሰን አንሃልት»ከአነስተኛዎቹ የጀርመን ፌደራል ክፍለ ግዛቶች አንዱ ነው። የቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን አካል የነበረው ይህ ግዛት የ2.19 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ ነው።ባለፈው ሳምንት በግዛቱ የተካሄደው አካባቢያዊ ምርጫ ውጤት፣ ከሦስት ወር በኋላ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ውጤት መስተዋት ተብሏል። ከመስከረሙ አጠቃላይ ምርጫ በፊት በተካሄደው በዚህ የጀርመን የመጨረሻ የአካባቢ ምርጫ የተጠበቀው ሳይሆን፣ ያልተጠበቀ ውጤት ተገኝቷል። ከምርጫው በፊት በተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት መነሻነት መጤ ጠሉ፣ ቀኝ ጽንፈኛው «አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ» በጀርመንኛው ምህጻር (AFD) ሊያሸንፍ ይችላል የተባለለት ይህ ምርጫ በወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር (CDU) ያልተጠበቀ ድል ተጠናቋል። ለድሉ አስተዋጽኦ አድርገዋል ከሚባሉት ውስጥ በኮሮና ተኅዋሲ የሚያዘው ሰው ቁጥር መቀነስ፣ እና የኮሮና ተኅዋሲ መከላከያ ክትባት በብዛት እየተሰጠ መሆኑ ይገኙበታል። የዛክሰን አንሀልት ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር ራይነር ሀዘልኦፍ ድሉ ከተበሰረ በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር፣ ግን ውጤቱ የተገኘው፣ ፓርቲው በህዝብ ዘንድ ባለው ተዓማኒነት ነው ብለዋል።
«በግዛቲቱ መንግሥት ውስጥ ለብዙ ዓመታት ሰርቻለሁ። ከዛሬ አስር ዓመት ወዲህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ። ሰዎች ያውቁኛል። መርሃ ግብሬንም ያውቃሉ፤ እንደ ግለሰብ ላበረክት የምችለውን የቆምኩለትንም ዓላማ እንዲሁ ያውቃሉ። እንደሚመስለኝ ይህ አመኔታ ለመጨረሻው ሰዓት ግፊት ወሳኝ ነበር። መላ ዜጎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ አብላጫ ድምጽ እንድናሸንፍ ስላደረጋችሁና ራሳችሁን ከቀኞች ስላራቃችሁ አመሰግናለሁ።በዛክሰን አንሃልት ጠንካራ ዴሞክራሲን ማስጠበቅ፣ የእኛ የዴሞክራቶች ገጽታ ነው።»
ያልተጠበቀው ድል CDUን ይበልጥ አነቃቅቷል። በራስ መተማመኑንም ከፍ አድርጓል።ባለፈው ሚያዚያ የፓርቲው እጩ መራሄ መንግሥት ሆነው የተመረጡት አርሚን ላሼት ትናንት እንደተናገሩት እሁድ የተገኘው ድል ሁለት ነገሮችን ያሳያል።
«ይህ የሚያሳየው «አማራጭ ለጀርመን» ፓርቲን በመቃወም የያዝነው ግልጽ አቋም ትክክለኛ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው ህዝብ ድጋፍ እንዳለውም ነው። እኛም ፓርቲያችን በሚከተለው የመሀል ቀኝ ፖለቲካ እንቀጥላለን። እኔም እንደ CDU መሪና የCDU እጩ መራሄ መንግሥት ለዚህ ነው የምቆመው። የመሀል ቀኝ ፖለቲካን መንገድ አንለቅም።»
CDU በዚህ ምርጫ 37.1 በመቶ ድምጽ በማሸነፍ ነው ቀዳሚውን ቦታ የያዘው። ይህም በከዚህ ቀደሙ ምርጫ ማለትም የዛሬ አምስት ዓመት ካገኘው ድምጽ ከ7 በመቶ በላይ ነው። የተፈራው ቀርቶ ያልተጠበቀው ውጤት እንዴት ሊገኝ ቻለ? ምንስ ያመለክታል? ጀርመን የሚሰሩትና የሚኖሩት የሕግ ባለሞያና የፖለቲካ ተንታኝ ዶር ለማ ይፍራሸዋ ያብራራሉ
ከክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ከCDU ጋር በምርጫው ዘመቻ ወቅት ከፍተኛ ፉክክር ሲያካሂድ የከረመው «ጀርመን ለጀርመናውያን ብቻ» የሚል አቋም የሚያራምደው «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው ፓርቲ 21 በመቶ ድምጽ በማግኘት ሁለተኛውን ደረጃ ይዟል።ፓርቲው በርካታ ደጋፊዎች እንዳሉት በሚታመንበት በዚህ ግዛት ያሸንፋል የሚሉ ትንበያዎች አስቀድመው ቢቀርቡም አልተሳካለትም። ያም ሆኖ ፓርቲው በውጤቱ መደሰቱን ነው ያሳወቀው። የፓርቲው ሊቀመንበር ቲኖ ችሩፓላ
«አክብሮት የሚሰጠው ውጤት ነው ያገኘነው።ይህም በጣም አስደስቶኛል።ያገነኘነው ድምጽ ከሃያ በመቶ በላይ ነው ።ውጤታችንን መሠረት አስይዘናል፤ጠንካራ መራጭ አለን፤ በዛክሰን አንሃልት ብዙ ድጋፍ ያለን ፓርቲ መሆናችንን በዚህ ምርጫ አሳይተናል።ራሳችንን አንድ ማድረግም ችለናል።»
በግዛቲቱ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በሙሉ ከAFD ጋር አብረን አንሠራም በማለታቸው በለስ ቀንቶት ቢያሸንፍ እንኳን ምንም ሊፈይድ አይችልም ነበር። የፖለቲካ ተንታኖች እንደሚሉት «አማራጭ ለጀርመን» በዛክሰን አንሃልቱ ምርጫ ቢሸነፍም ያገኘው ድምጽ ግን የሚናቅ አይደለም። ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት በመጋቢት ወር ምዕራብ ጀርመን በሚገኙ ሁለት ግዛቶች ካገኘው ከ10 በመቶ ካነሱ ድምጾች የእሁዱ እጅግ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ነው። ከዚህ ሌላ በግዛቱ ምክር ቤት ሁለተኛውን ቦታ የሚይዘው ፓርቲው አብላጭውን የተቃዋሚዎች ወንበር ማግኘቱም እንዲሁ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይሆንም ።ምንም እንኳን AFD በዛክሰን አንሃልቱ ምርጫ ቢሸነፍም ፓርቲው በመስከረሙ አጠቃላይ ምርጫ ስጋት መሆኑ አይቀርም እንደ ዶክተር ለማ
በእሁዱ ምርጫ የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ከፍተኛ ሽንፈት ነው የገጠመው።በታሪኩ ዝቅተኛ የሚባል 8 በመቶ ድምጽ ብቻ ነው ያገኘው። በጀርመንኛ መጠሪያው የግራዎቹ ፓርቲ (LINKE)ም 11 በመቶ ድምጽ ብቻ ነው ያሸነፈው ሁለቱን ፓርቲዎች ለሽንፈት የዳረገው ቃላቸውን ባለመክበራቸው ነው ይላሉ ዶክተር ለማ።
የመስከረሙ የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ መስታወት በተባለው በዛክሰን አንሃልቱ ምርጫ ያሸነፈው CDU ብቻውን መንግሥት መመስረት የሚያስችለው ድምጽ ስለሌለው ተጣማሪዎችን ማግኘት አለበት። ዶክተር ለማ CDU ከነፃ ዴሞክራቶች ፓርቲ በምህጻሩ FDPና ከሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ SPD ጋር ተጣምሮ መንግሥት ይመሰርታል የሚል ግምት አላቸው። በመጪው አጠቃላይ ምርጫም ይህ ሊደገም የሚችልበት እድል አለ ይላሉ። የዛክሰን አንሃልት ጠቅላይ ሚኒስትር ግን ከየትኛዎቹ ፓርቲዎች ጋር ተጣምረው መንግሥት እንደሚመሰርቱ እስካሁን ፍንጭ አልሰጡም። የሆነ ሆኖ ይህ ምርጫ ለጀርመንም ይሁን ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ ሃገራት ትምሕርት ሰጭ መሆኑን ዶክተር ለማ ያስረዳሉ።
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ