የዜና አቅራቢው እና ሙዚቀኛው ይድነቃቸው ብርሃኑ የስኬት ሕይወት ጅማሬ
እሑድ፣ ጥር 29 2014
በተፈጥሮ የታደሉትን ተሰጥዖ ገና በጠዋቱ ለራሳቸው አውቀውትም ሆነ በሌሎች ገፊነት አንቱታን ያተረፉ ጥቂት አይደሉም ፤ በሙዚቃው ዓለም በተፈጥሮ የታደሉትን ድምጽ አውጥተው ለመጠቀም ጊዜ ገዝተው ፣ በስለው ከቀረቡ በኋላም በአጭር ጊዜ ውስጥ ያንኑ ለመጎናጸፍ የታደሉ እንዲሁ ከብዙ በጥቂቱ ሲከሰቱ እያየን ነው። ለሁሉም ጊዜ አለውና ። ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን እንደምን ሰነበታችሁ በዛሬው የመዝናኛ ዝግጅታችን ከቴሌቪዥን የዜና አቅራቢነት ድንገት ወደ ሙዚቃው ዓለም ጎራ ብሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወዳጅነትን ካተረፈው ዜና አቅራቢ እና ድምጻዊ ይድነቃቸው ብርሃኑ ጋር ቆይታ ያደረግንበትን ዝግጅት ይዘን ቀርበናል ። መልካም ቆይታ ።
ይድነቃቸው ብርሃኑን ብዙዎች የሚያውቁት በኢ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን እየተዘጋጀ በሚቀርበው አዲስ ነገር የመረጃ ሰዓት በዜና አቅራቢነት ነው። በቴሌቪዥን ዜና አቀራረቡ ተወዳጅነትን ያተረፈው ይድነቃቸው በዚሁ ስራው ላይ እያለ በአንድ የበዓል ዝግጅት ላይ ሲያዜም ከታየ በኋላ የበርካቶችን ቀልብ ከመሳብ አልፎ ተወዳጅነትን ማትረፍ ችሏል። ነገር ግን ይድነቃቸው ይህን ተሰጥዖ ይዞ የት ቆየ የሚል ጥያቄን ሳያጭርባቸውም አልቀረ ፤ ይድነቃቸው ግን ለሁሉም ጊዜ አለው ሲል ለብዙዎች ጥያቄ መልስ ይሰጣል።
ይደናቀቸው የበኩር ስራውን በ2013 ዓ/ም መጀመርያ አካባቢ ነበር ለአድማጭ ተመልካች ያበቃው ፤ ሲያስባት የሚል, መጠርያ የሰጠው ይኸው የመጀመርያው ስራው ይድነቃቸውን በበለጠ ከአድማጭ ተመልካቹ ከማስተዋወቅ ባሻገር በለስላሳ አቀራረቡ አድናቆት ተችሮታል፤ በዩትዩብ መንደርም ሚሊዮኖች ተመልክተውለታል። ።
የመጀመርያውን የነጠላ ዜማ በሰራ በዓመቱ ሌላ የነጠላ ዜማ በቪዲዮ ክሊፕ ጭምር ሰርቶ ሰሞኑን ለአድማጭ ተመልካች ማቅረቡን የሚናገረው ይደነቃቸው ነጠላ ዜማው እንደወጣ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳስገኘለት ይናገራል። የሰውን ሙዚቃ ከመጫወት ወጣ ተብሎ በራስ ወጥ ስራ መምጣት ምንም እንኳ በራሱ ጥቂትም ቢሆን ፈተና ያለበት ቢሆንም ዉጤቱ ያማረ እንደሆነ ይድነቃቸው ይናገራል።
በሙዚቃ ስራ ስኬት ውስጥ ከድምጻዊው ተ,ሰጥዖ እና ብቃት ጀርባ ሁሌም ሊዘነጉ የማይገባቸው የሙዚቃ ሰ,ዎች አይጠፉም ፤ ይድነቃቸውም በሙዚቃ ስራዎቹ ውስጥ አሻራቸውን ያኖሩትን ጨምሮ በተለያየ መልኩ ድጋፋቸውን ሲያደርጉለት የነበሩትን ማመስገን ይሻል።
እንግዲህ አድማጮቻችን ለዛሬ ያልነው እና ከዜና አቅራቢ እና ድምጻዊ ይድነቃቸው ብርሃኑ ጋር የነበረን ቆይታም በዚሁ ተጠናቋል፤ ሳምንት በሌላ ዝግጅት እንጠብቃችኋለን ታምራት ዲንሳ ነኝ ቸር እንሰንብት ።
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ