1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዝቋላ ገዳም መነኮሳት ግድያ

ዓርብ፣ የካቲት 15 2016

በኦሮሚያ ክልል ምስራሰቅ ሸዋ ዞን የሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አራት መነኮሳት “ኦነግ ሸነ” በተባሉ ታጣቂዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክስርቲያን አስታወቀች፡፡ ቤተክስርቲያንዋ ከተገደሉት አገልጋዮች ጋር የተወሰዱት አምስተኛው አባት እስካሁን ያሉበት በውል ማወቅ አልተቻለም ብላለች፡፡

ፎቶ ማህደር፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ምዕመናን
ፎቶ ማህደር፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ምዕመናን ምስል picture alliance/AP Photo

የዝቋላ ገዳም አራት መነኮሳት “ኦነግ ሸነ” በተባሉ ታጣቂዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክስርቲያን አስታወቀች፡፡ አምስተኛዉ የደረሱበት አልታወቀም

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ምስራሰቅ ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አራት መነኮሳት “ኦነግ ሸነ” በተባሉ ታጣቂዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክስርቲያን አስታወቀች፡፡

ቤተክርስቲያንቱ ከተገደሉት አራቱ የገደሙ አገልጋዮች በተጨማሪ፤ ከተገደሉት አገልጋዮች ጋር የተወሰዱት አምስተኛው የቤተክርስቲያኑ አገልጋይ ያሉበትን እስካሁን በውል ማወቅ አልተቻለም ብላለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ኃላፊ መላከሰላም ቀሲስ ዳዊት ያሬድ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ቃለምልልስ ከተገደሉት አባቶች መካከል ያልተገኙ አንደኛው የቤተክርስቲያኑ አገልጋይም በህይወት እንደተመለሱ ታሳቢ ብደረግም እስካሁን ያሉበት አይታወቅም ብለዋል፡፡ “የገዳሙን መጋቢ አባተክለማርያምን አስራትን ጨምሮ አራቱ አባቶች ተገድለዋል፡፡ አምስተኛውና በህይወት ይኑሩ አይኑሩ ያልታወቀ አባት በተመለከተ ያልጠሩ ነገሮች ነበሩ፡፡ ግን እስካሁን እሳቸውም ያሉበት አይታወቅም” ነው ያሉት፡፡

ዱካቸው ስለጠፋው አገልጋይ አባት

የተገደሉ የገዳሙ አባቶች የገዳሙ መጋቢ፣ የገዳሚ ጸሃፊ፣ የገዳሙ ቀዳሽ እና በአመንክሮ ላይ ያሉ መናኝ ናቸው ተብሏል፡፡ ከተገደሉት አባቶች ጋር ተወስደው ዱካቸው የጠፋው አባትም የገዳሙ አገልጋይ መሆናቸው ተነግሯል፡፡ አባቶቹ ተይዘው የተገደሉበት መንገድ ላይ ለዶቼ ቬለ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት ቀሲስ ዳዊት፤ “መጀመሪያ ሁለት አባቶች ከተወሰዱ በኋላ የእንወያይ ጥያቄ ከቀረበባቸው በኋላ ሶስቱ በተጨማሪነት ሲሁዱ ነው ያገቷቸው” ብለዋል፡፡

ቤተክርስቲያኑ ላይ ከዚህም በፊት መሰል የደህንነት ስጋቶች በተደጋጋሚ መከሰቱንም ያወሱት የቤተክርስቲኗ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ኃላፊው መላከሰላም ቀሲስ ዳዊት ያሬድ፤ ቤተክርስቲያኗ የገዳሙ ህልውና ወደፊት በምን አይነት መልኩ ይጠበቃል በሚለው ላይ ማሳሰቢዋን ለመንግስት ማቅረቧንም አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም መነኮሳቱ እና የገዳሙ ቅርሶች አደጋ ላይ በመሆናቸው የፌደራል እና የክልሉ የፀጥታ አካላት ጥበቃ እንዲያደርጉ ቤተክርስቲያኒቱ ጥሪ ማቅረቧን ገልጸዋል። “የገዳሞች ህልውና ተከብሮ እንዲኖር ምን መደረግ አለበት በሚለው ለመምከር ከገዳሙ ያሉ አባቶችም መጥተው እንዲማከሩ ዛሬ ጠዋት ጠቅላይ ቤተክነት ምክክር ተደርጓል፡፡ ሀገሪቷንም የሚያስተዳድረው መንግስት የሁሉም እስከሆነ ድረስ በዚያው አግባብ መንግስት ገዳሙን በመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ነው በጉባኤው ተወስኖ የተላለፈው” ብለዋል፡፡

ስለገዳሙ ጥቃት የቤተክርስቲያኒቱ ይፋዊ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያኒያን የህዝብ ግንጙነት መምሪያ ትናንት ባወጣው መረጃ መሰረት ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ/ም ታጣቂዎቹ አባቶችን አግተው ወደ በረሃ ወስደዋል። መነኮሳቱ የተገደሉት መንግስት «ኦነግ ሸኔ» እያለ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መሆኑንም የመምሪያ መቅለጫ ጠቁሟል። የታገቱትን ለማስለቀቅ ገዳሙ ጥረት እያደረገ በነበረበት ወቅትም የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ/ም አራት መነኮሳት መገደላቸውን እና አብረው ከነበሩት ውስጥ አንድ አባት ብቻ በህይወት መትረፋቸውን አመልክቷል፡፡ ይሁንና በህይወት ተርፈዋል የተባሉት አምስተኛው የቤተክርስቲያኑ አገልጋይም በህይወት ስለመኖራቸው የታወቀ ነገር አለመኖሩን ያመለከቱት የመምሪያው የህዝብ ግንጙነት ምክትል ኃላፊ የተገደሉት አባቶችም ስልክ እስከ እሮብ ማታ ይሰራ ነበር ብለዋል፡፡ “በቀደም እሮብ ቀኑን ሙሉ ስልካቸው ይሰራ ነበር፡፡ ምሽት ላይ ግን ስልካቸው ተቋርጦ ትናንት ጠዋት ነው አራቱ መሞታቸው የተረጋገጠው” ነው ያሉት፡፡

በምስራቅ ሸዋ ኦሮምያ ክልል ባልታወቁ ሰዎች የተቃጠለዉ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ምስል Seyoum Getu/DW

ስለገዳም አባቶቹ ህልፈትና ገዳሙ ላይ ተደቅኗል ስለተባለው የህልውና አደጋ ከአከባቢው ባለስልጣናት በተለይም ከምስራቅ ሸዋ ዞን እና ሊበን ጩቃላ ወረዳ ፖሊስ መምሪያ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልሰመረም፡፡

ስለአባቶቹ ግድያ የመንግስት መግለጫ

የኦሮሚያ ጸጥታ እና አስተዳደር ቢሮ ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ግን አራቱ አባቶች የተገደሉት “ኦነግ ሸነ” በተባሉ ታጣቂዎች መሆኑን በመግለጽ፤ ግድያው የወረዳውን ነዋሪዎች በእጅጉ ያስደነገጠ መሆኑን ገልጿል፡፡ ቢሮው ፖሊስ የደረሱትን ጥቆማ በመያዝ እርምጃ እየወሰደም ይገኛል ብሏል፡፡ ቢሮው አክሎም የሚወሰደው እርምጃ ወደፊት ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ብጠቁምም እስካሁን የተወሰደው እርምጃ አይነትና የተገኘው ውጤትን በተመለከተ የሰጠው ማብራሪያ የለም፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ የሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በርካታ መነኮሳት እንዲሁም ቅርሶች የሚገኙበት ጥንታዊያን እና ታሪካዊ ገዳማት መካከል ስጠቀስ፤ በተለያዩ ጊዜያት ዘረፋ፣ ቃጠሎ እና ከባድ ጉዳቶችን እንደደረሰበትም ቤተ ክርስቲያኗ አስታውቃለች።

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW