1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የዝናብ መዘግየት የገበሬዎች ስጋት በምዕራብ አማራ

ዓለምነው መኮንን
ሐሙስ፣ ሰኔ 12 2017

“የዳመና ሽፋን እየታየ ቢሆንም ዝናቡ ግን ሊጥል አልቻለም” ያሉን ደግሞ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የደሀና ወረዳ ነዋሪ ቄስ አማረ ወዳጅ ናቸው። አርሶ አደሩ ዝናብ ይጥላል በሚል ተስፋ ያለውን ዘር ማሳ ላይ በትኖ እየጠበቀ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

የምዕራብ አማራ ሚትዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል
የምዕራብ አማራ ሚትዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከልምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የዝናብ መዘግየት የገበሬዎች ስጋት በምዕራብ አማራ

This browser does not support the audio element.

በምዕራብ አማራ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ዝናብ በመዘግየቱ የዘር ጊዜ እንዳላፈባቸው አረሶ አደሮች ተናገሩ። የምዕራብ አማራ አየር ትንበያ ተቋም በበኩሉ በአንዳንድ ዝናብ በዘገየባቸው አካባቢዎች በቂ ባይሆንም ዝናብ ሰሞኑን መጣል ይጀምራል ብሏል። በዚህ ዓመት የክረምት ወቅት በአጠቃላይ በአገሪቱ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተቋሙ ትንበያ ሰጥቷል፡፡                                    
                                     
በዚህ ዓመት አርሶ አደሩ በማዳበሪያ ዋጋ መወደድ ከፍተኛ ጫና እንደደረሰበት ሲያማርር የቆየ ሲሆን አሁን ደግሞ በአንዳንድ የምዕራብ አማራ አካባቢዎች የክረምቱ ዝናብ በመዘግየቱ ቀድመው በሚዘሩ ሰብሎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል። “ዝናብ ይጥላል” በሚል እሳቤ ቀድመው የዘሩ አርሶ አደሮችም ቡቃያ ማየት እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን አርሶአደሮች መካከል  ከሰሜን ጎጃም ዞን አቸፈር ወረዳ አቶ አስማማው ሉሌ አንዱ ናቸው፡፡
እንደ አርሶ አደሩ ቀደም ሲል ባሉ ዓመታት ዝናቡ ቀድሞ ይጥል ስለነበር ቀድመው የሚዘሩ የቦቆሎና የገብስ ሰብሎች ይዘሩ እንደነበር አመልክተዋል። ዘንድሮ ግን ግንቦት ወር ላይ ባለመዝነቡ ቀድመው የሚዘሩ ሰብሎች አልተዘሩም ብለዋል፡፡

“ዝናብ ባይጥልም በተስፋ ዘር የዘሩ አርሶ አደሮች አሉ” አሰትያየት ሰጪዎች
ዝናቡ ባይጥለም በተስፋ ዘር የዘሩ በርካታ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ከምዕራብ ጎጃም ዞን አቶ ቃኜ አበባዬ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። አርሶ አደሩ ከዚህ በፊት ግንቦት እንደገባ ዝናቡ ይጥል እንደነበርና ቦቆሎና ገብስ ወዲያውኑ ይዘሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ዝናቡ ይጥላል በሚል ዘር ማሳቸው ላይ የዘሩ አርሶ አደሮችም ዝናቡ  ባለመጣሉ የተዘራው ዘር ሊበቅል እንዳልቻለ ነው የተናገሩት፡፡
በምስራቅ ጎጃም ዞን የየጁቤ ወረዳ አርሶአደር አቶ አንዷለም ጌቴ በተመሳሳይ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡ የዘር ወቅት እያለፈባቸው እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡

“የዳመና ሽፋን ቢኖርም ዝናብ ሊጥል አልቻለም” የዋግኽምራ አረሶ አደር
“የዳመና ሽፋን እየታየ ቢሆንም ዝናቡ ግን ሊጥል አልቻለም” ያሉን ደግሞ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የደሀና ወረዳ ነዋሪ ቄስ አማረ ወዳጅ ናቸው። አርሶ አደሩ ዝናብ ይጥላል በሚል ተስፋ ያለውን ዘር ማሳ ላይ በትኖ እየጠበቀ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

“በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ዝናብ ይጥላል” የምዕራብ አማራ አየር ትንበያ ተቋም
በኢትዮጵያ አየር ትንበያ ተቋም የምዕራብ አማራ አየር ትንበያ ባለሙያ አቶ መልካሙ በላይ የወቅያኖስ ሙቀትን መጨመር ተከትሎ በምዕራብ አማራ አንዳንድ አካባቢዎች የዝናብ መዘግየት መታየቱን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ከቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ጀምሮ በቂ ነው ባይባልም በበርካታ አካባቢዎች ዝናብ መጣል እንደሚጅምር፣ በአንፃሩ ደግሞ ቆላማ በሆኑ የምዕራብና ምስራቅ አማራ አዋሳኘ ቆላማ አካባቢዎች አሁንም ዝናቡ ሊዘገይ እንደሚችል የትንበያ መርጃዎችን ጠቅሰው አብራርተዋል፡፡

ክልሉ በአንድ ኩንታል ማድበሪያ የ3ሺህ 600 ብር ድጎማ በማድረጉ የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዋጋ ከ8,000  ብር እንዳይበልጥ መደረጉን ገጿል።ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

 “እንደ ሀገር በክረምቱ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጠበቃል”የኢትዮጵያ አየር ትንበያ ተቋም
በኢትዮጵያ አየር ትንበያ ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምነው ተሾመ ከሰኔ እስከ መስከረም ያሉ ወራት የክረምት ወቅቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አጠቃላይ በመጪው ክረምት ወቅት በመላ አገሪቱመደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብእንደሚኖር ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ በአንዳንድ የምዕራብ አማራ አካባቢዎች ዝናብ መጣል ጀምሯል ያሉት ዶ/ር አሳምነው፤ በምስራቅ አማራ አካባቢዎች ሊዘገይ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
ከማዳበሪያ ዋጋ መወደድ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ለዶይቼ ቬሌ መግለጫ የሰጡት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር ልማት አስተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ የማዳበሪያ ዋጋ ከዶላር ምንዛሬ ማደግ ጋር
ተያይዞ ዋጋው መጨመሩን ገልጠዋል። በዚህም ምክንያት የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዋጋ 12ሺህ 600 ብር እንደሚደርስ አመልክተዋል፡፡ ሆኖም ክልሉ በአንድ ኩንታል ማድበሪያ የ3ሺህ 600 ብር ድጎማ በማድረጉ የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዋጋ ከ8,000  ብር እንዳይበልጥ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ 
ክልሉ 9 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ማዳበሪያ እንደሚያስገባ የገለጹት ዶ/ር ድረስ፣ 3.5 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው ወደ አርሶ አደሩ እጅ ገብቷል ብለዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW