1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የዝናብ እጥረት የቀነሰው የአንበጣ ወረራ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 5 2013

በምሥራቅ አፍሪቃና በአካባቢው በቅርቡ የታየው የዝናብ እጥረት ባለፉት ወራት አሳሳቢ የነበረው የአንበጣ ወረራ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉ እየተነገረ ነው። በተለይ በኢትዮጵያ የበልግ ወቅት ዝናብ የሚያገኙ የሀገሪቱ ክፍሎች ዘንድሮ ደረቅ በመሆናቸው አንበጣ እንዳይራባ መርዳቱም ተገልጿል።

Infografik Heuschrecken EN

«በምሥራቅ አፍሪቃ የበልግ ወቅት ደረቅ ሆኖ ከርሟል»

This browser does not support the audio element.

ከየካቲት እስከ ግንቦት ያለው የዓመቱ ክፍል የበልግ ወቅት ተብሎ ይታወቃል። በዚህ ጊዜ ዝናብ የሚጠበቅ ቢሆንም ዘንድሮ ግን የታየው ደረቅ የአየር ጠባይ በመሆኑ ምሥራቅ አፍሪቃን አስጨንቆ የሰነበተው የአንበጣ መንጋ ወረራ መቆሙን መረጃዎች ያሳያሉ። በኢትዮጵያም የታየው ይኽ መሆኑን የሚመለከታቸው ባለሙያ ይናገራሉ።

በኬንያው ሬፍት ቫሊ ክፍለ ሀገር ቀደም ብሎ የአንበጣ መንጋ መከማቸቱን ያመላከተው የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO ካለፉት ዓመታት በተለየ ዘንድሮ ባለፈው ደረቅ የአየር ጠባይ ምክንያት አንበጣ አስጊ እንዳልሆነ ከሰሞኑ ገልጿል። FAO እንደሚለው በኬንያ ብቻ ሳይሆን በጎረቤት ኢትዮጵያም ያለተው ተመሳሳይ ደረቅ የአየር ሁኔታ በአካባቢው ተበራክቶ የከረመው አንበጣ እንዳይራባ እንቅፋት እንደሆነበትም አመልክቷል። አንበጣ ርጥበት እና ልምላሜ እንደሚስመው የሚናገሩት በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ደረቅ የአየር ጠባይ ባለፈው የታየውን አይነት የአንበጣ ወረራ የሚደግም አይደለም ይላሉ።

ያለፉት ጊዜያት የዘንበጣ ወራር ትውስታምስል፦ Baz Ratner/REUTERS

አቶ በላይነህ እንደሚሉት ዝናብ አለመኖሩ፣ የአፈሩን እርጥበት ስለሚያሳጣ ይኽ ደግሞ ሳሩንም ሆነ ሌላውን እጽዋት ልምላሜ እንዳይኖረው በማድረጉ የአንበጣው የመራባትም ሆነ አድጎ ጉዳት ለማድረስ እንዲበቃ ዕድል አሳጥቶታል። ይኽ የአየር ጠባይ በኢትዮጵያ አጎራባት ሃገራትም ተመሳሳይ በመሆኑ ከሌላ አካባቢ የሚመጣ የአንበጣ መንጋ እንዳይኖርም ምክንያት እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል። እሳቸው እንዳሉት የዘንድሮው የበልግ ወቅት ደረቅ እንደነበረ ነው ከብሔራዊ ሜቴሪዎሎጂ ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው። የበልግ ወቅት የሚባለው ከየካቲት እስከ ግንቦት መጨረሻ መሆኑን የመለከቱት በብሔራዊ ሜቴሪዎሎጂ የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ጫሊ ደበላ ላኒኛ የተባለው የአየር ንብረት ክስተት የዝናብ እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉን ይናገራሉ።

በነገራችን ላይ በቅርቡ የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት እና የዓለም የምግብ መርሃ ግብር ባወጡት ዘገባ ባለፉት ወራት የአንበጣ መንጋ፣ ግጭት እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተሉት ተጽዕኖ ከ20 በሚበልጡ ሃገራት ውስጥ በቀጣይ አሳሳቢ የረሃብ አደጋ ማንዣበቡን ጠቁመዋል። ችግሩ ያሰጋቸዋል ከተባሉት አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት ሲሆኑ ኢትዮጵያም ተጠቅሳለች። ለሰጡን ማብራሪያ ባለሙያዎቹን በማመስገን ለዕለቱ ያልነውን በዚሁ እናብቃ።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW