1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox) ምንነት እና ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከለከል የጀመረችው ጥረት

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 21 2016

የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox) ዓለም አቀፍ አሳሳቢ የሕዝብ ጤና ሥጋት መሆኑን ያወጀው ሰሞኑን ነው። የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከልም ከማዕከላዊ አፍሪካ እስከ ምሥራቁ የአህጉሩ አካባቢ በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘው ይህ በሽታ፣ የአፍሪካ አሳሳቢ የጤና አደጋ መሆኑን አሳውቋል።

Infektion mit "Monkeypox Virus" Affenpocken - 1971
ምስል፦ Gemeinfrei/CDC's Public Health Image Library

የዝንጆሮ ፈንጣጣ የዓለም የጤና ሥጋት ሆኗል

This browser does not support the audio element.

የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox) ዓለም አቀፍ አሳሳቢ የሕዝብ ጤና ሥጋት መሆኑን ያወጀው ሰሞኑን ነው። የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከልም ከማዕከላዊ አፍሪካ እስከ ምሥራቁ የአህጉሩ አካባቢ በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘው ይህ በሽታ፣ የአፍሪካ አሳሳቢ የጤና አደጋ መሆኑን አሳውቋል።

በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተያዘ ሰው የለም ያለው የጤና ሚኒስቴር፣ በሽታውን ለመከላከል የቅኝትና የልየታ፣ የፍተሻ ላብራቶሪዎችን የማብዛት እንዲሁም የለይቶ ማቆያና የህክምና ቦታዎች በማዘጋጀት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

የዝንጆሮ ፈንጣጣ የዓለም የጤና ሥጋት ሆኗል

በስፋት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወደ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ እንዲሁም ኡጋንዳ እየተዛመተ ይገኛል።

እ.ኤ.አ በ 1970 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (DRC) የተከሰተው ይህ ቀደም ሲል የዝንጆሮ ፈንጣጣ በሚል ይታወቅ የነበረው በሽታ ችላ ተብሎ መቆየቱን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። በመካከለኛው እና በምዕራብ አፍሪካ እየተስፋፋ ያለው ይህ ተላላፊ በሽታ ከጊዜ ሂደት በኋላ በ 2022  ዓለም አቀፍ ወረርሽኝን አስከትሏል።

በወቅቱ ይህ በሽታ ቫይረሱ ተከስቶባቸው የማያውቁ በነበሩት የአውሮፓ እና የእስያ አገራትን ተከስቶ እንደነበር ይነገራል።

የዓለም የጤና ሥጋት የሆነው የዝንጆሮ ፈንጣጣ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Bihlmayerfotografie/IMAGO

የዝንጀሮ ፈንጣጣ የአሁኑ (Mpox) በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ የነበረ ቢሆንም በዚህ ወቅት ከሰው ወደ ሰው የሚዛመት መሆኑ ተነግሯል። አፍሪካ ውስጥ ባሉ ጥቅጥቅ ጫካዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ያለማቋረጥ ሄድ መለስ እያለ የሚከሰተው ይህ በሽታ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሰዎችን ይለክፋል። በመቶዎች የሚቆጠሩትም በየዓመቱ የበሽታውን ሕመም መቋቋም እየተሳናቸው ይሞታሉ።

የበሽታው የሥርጭት አድማስ እና እያደረሰ ሳለው ጉዳት

የዓለም ጤና ድርጅት ይህ በሽታ የዓለም አሳሳቢ ድንገተኛ የጤና አደጋ መሆኑን ከሳምንት በፊት አውጇል።  ኢትዮጵያዊው የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ይህንን አሳሳቢ ወረርሽኝ ለመከላከል እና ለማስቆም የተቀናጀ ያሉት ዓለም አቀፍ ምላሽ ያስፈልጋል ብለዋል። የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል አፍሪካ ሲዲሲ በአሕጉሩ ከጥር ወር መጀመሪያ እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ ባሉት ሰባት ወራት ከ14,500 በላይ ሰዎች በዝንጀሮ ፈንጣጣ መያዘቸውን አስታውቋል። ይህም የበሽታው መስፋፋት እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን፣ በወረርሽኙ ተይዘው የሚሞቱት ሰዎችም ጥቂት ቀላል በማይባል መጠን መጨመሩን አመልካች እንደሆነ አሳይቷል።

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ያጋራው መረጃ እንደሚጠቁመው አፍሪካ ሲዲሲ በ13 የአፍሪካ ሀገራት፣ 2,863 ሰዎች በዚሁ በሽታ መያዛቸው እና 517 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸዉ መረጋገጡን እና ስርጭቱን ለመከላከል የሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የጋራ እርምጃን የሚጠይቅ መሆኑ ጠቁሟል።

የጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዝግጅቶች

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ይህንኑ በሽታ ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት እና ዝግጅት አስመልክተው ከቀናት በፊት መግለጫ ሰጥተው ነበር። አሳሳቢው በሽታ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የቅኝት፣ የልየታ፣ የላብራቶሪ ማጠናከር፣ የለይቶ ማቆያ እና የህክምና ሥፍራዎችን የማዘጋጀት እና መሰል የመከላከል እና የመቆጣጠር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። ይህንንም እያደረጉ ያሉት ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መሆኑን ገልፀዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ይህ በሽታ የዓለም አሳሳቢ ድንገተኛ የጤና አደጋ መሆኑን ከሳምንት በፊት አውጇል። ተሐዋሲው ይህን ይመስላል ምስል፦ Planet Pix/ZUMA Press/picture alliance

"ዛሬ ላይ ብቻ አይደለም ሥራውን የጀመርነው። በ 2022 ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥርጭቶች እንዳይጨምሩ የቁጥጥር ሥራዎች፣ የተቀናጁ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል" ።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ የአሁኑ (MPox) በሽታ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የዕጢ እብጠት፣ የጡንቻ እና የጀርባ ህመም፣ ሽፍታ፣ የቆዳ ቁስለት እንዲሁም የአቅም ማጣትን የመሳሰሉ ጉልህ ምልክቶች አሉት። ውሎ ሲያድርም በእጅ መዳፍ እንዲሁም በእግር የታችኛው ክፍል ብሎም በመላ የሰውነት አካል ላይ ጎልቶ የሚታይ ሽፍታን ያስከትላል።

ይህንኑ በሽታ ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ብሔራዊ ጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉን ጠይቀናቸዋል።

"ፕሮቶኮል አላት ሀገሪቱ [ኢትዮጵያ] እንደዚህ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ። በዚያ ፕሮቶኮል መሠረት የብሔራዊ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከል አለ በተጠንቀቅ ላይ እናደርጋለን።"

ሁለቱ ብሔራዊ የጤና ተቋማት  የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታእስካሁን በኢትዮጵያ ተከስቶ እንደማያውቅ ገልፀዋል። ይሁንና አፍሪካ ሲዲሲ በሽታው በመላው አፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ መሆኑን ማስታወቁ ብርቱ ጥንቃቄ እንዲደረግ አስገዳጅ አድርጎታል።

ይህም ብቻ ሳይሆን የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካዎቹ በኬንያ፣ በሩዋንዳ፣ በኡጋንዳ እና በቡሩንዲ መከሰቱ ኢትዮጵያ ማድረግ ያለባት ጥንቃቄ የተጠናከረ እንዲሆን የሚያስገድድ ጭምር ይመስላል።

"ሀገራችን የዓለም አቀፍ የጤና ደንብ ፈራሚ ሀገር እንደመሆኗ መጠን በዚያ መሠረት እነዚህ አባል ሀገራትም ይተባበራሉ። መረጃዎችን እንለዋወጣለን። በየ ቀኑ በአፍሪካ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠሪያ ማዕከልም በኩል የሚቀርቡ መረጃዎችን እየተከታተልን በጋራ ይሠራል"።

በስፋት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ የተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወደ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ እንዲሁም ኡጋንዳ እየተዛመተ ይገኛልምስል፦ Arlette Bashizi /REUTERS

የድንበር ቁጥጥር እና የልየታ ሥራ

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ  በሽታን ለመከላከል  ከሕክምና ቁሳቁስ እስከ የባለሙያ ዝግጅት እና የድንበር ቁጥጥር እየተደረገ ነው ያሉትን ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

"ስምንት የየብስ ኬላዎች አሉ። ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያገናኙን። ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገራችን የሚመጡና የሚወጡ ሰዎች ያሉባቸው። የዓለም አቀፍ ግንኙነት ደግሞ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የምናደርገው የማጣራት ሥራ ነው። ለእነዚህ የሚያስፈልጉት ስልጠናዎች ተሰጥተዋል"።

ጥቆማ መስጫ አማራጮች

በቫይረስ አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው Mpox ከዚህ በፊት ከተከሰተው የዝንጆሮ ፈንጣጣ በላቀ አደገኛ መሆኑ፣ በሰውነት ንክኪ፣ በወሲባዊ ግንኙነትን፣ በቆዳ ንክኪ እንዲሁም በሽታው ከያዛቸው ሰዎች ጋር በሚኖር የቅርበት ግንኙነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ነው መባሉ በመላው ዓለም ሥጋት መደቀኑ አልቀረም። የጤና ሚኒስቴር ማንኛውም ሰው እነዚህ ምልክቶችን ሲመለከት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ እንዲያሳውቅ፣ 952 እና 83 35 በተባሉ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግም ጠይቋል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW