1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የየካቲት 2 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 2 2018

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለም መድረኮች የብርቱ ፉክክር ዐሳይተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል የማሸነፍ እድሉን የማታ ማታ በማንቸስተር ሲቲ አስነጥቋል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባዬር ሙይንሽን ሆፈንሐይምን የግብ ጎተራ አድርጎታል ። የሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች የፊታችን ሳምንት ይከናወናሉ ።

በሱፐር ቦውል ፍጻሜ ሲያትል ሲሃውክስ ድል ተቀዳጅቶ ያነሳው ዋንጫ
በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ እግር ኳስ ሊግ (NFL) ዓመታዊ የፍፃሜ ጨዋታ ማለትም ሱፐር ቦውል ፉክክር ፍጻሜ ኒው ኢንግላንድ ፓትሪዮትስንድል በመንሳት ሲያትል ሲሃውክስ ዋንጫ አንስቷልምስል፦ Ronald Martinez/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለም መድረኮች የብርቱ ፉክክር ዐሳይተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል የማሸነፍ እድሉን የማታ ማታ በማንቸስተር ሲቲ አስነጥቋል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባዬር ሙይንሽን ሆፈንሐይምን የግብ ጎተራ አድርጎታል ። የሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች የሚቀጥለው ሳምንት ይከናወናሉ ። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በበርካቶች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆነው የአሜሪካ እግር ኳስ ፍጻሜ ውድድር ማለትም ሱፐር ቦውል  በትናንትናው እለት በሴያትል ሲሐውክስ አሸናፊነት ተጠናቅቋል ።

ጀርመን ካርልስሩኸ ውስጥ የተከናወነው የአትሌቲክስ ፉክክር

ጀርመን ካርልስሩኸ ውስጥ ትናንት በ12 ዘርፎች በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያዊዎቷ አትሌት ብርቄ ሀየሎም 1500 ሜትሩን በ(4፡00.88 ደቂቃ) በማጠናቀቅ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። በውድድሩ የብሪታኒያዋ ጆርጂያ ሀንተር-ቤል በ4፡00.04 ደቂቃ አጠናቅቃ አሸንፋለች ። የማድሪድ እና ኦስትራቫ የቤት ውስጥ አሸናፊዋ ብርቄ በብሪታንያዋ ሯጭ የተቀደመችው ለጥቂት በ84 ማይክሮ ሰከንድ ነው ።

በዚሁ ውድድር ፈረንሳዊቷ አጋቴ ጊሌሞ በ4፡02.12 በመግባት ሦስተኛ ደረጃ ስትይዝ አዲስ ብሔራዊ ክብረወሰን በማስመዝገብ ጭምር ነው ።  ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሳሮን በርሀ 4:03.55 በመሮጥ 4ኛ ደረጃ አግኝታለች ። በተመሳሳይ ርቀት በወንዶች ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት መለስ ንብረት 3:38.96 በመሮጥ 8ኛ ደረጃ አግኝቶ ውድድሩን አጠናቅቋል ።

ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በ1500 እና 3000 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድሮች ተሳታፊ ነበሩ ።  በ3000 ሜትር ፉክክር አትሌት የኔዋ ንብረት 8:38.90 በመግባት 3ኛ፤ አትሌት አክሱማይት አምባዬ 8:40.38 በማጠናቀቅ 4ኛ ደረጃ ይዘዋል ። በወንዶች የ3 ሺህ ሜትር ውድድር፦ አትሌት ጌትነት ዋለ 7: 41:13.00 ሮጦ በመግባት 8ኛ ደረጃ፤ አትሌት ኃይለማሪያም አማረ 7:57.49 በመሮጥ 10ኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን አጠናቅቀዋል ። በዚህ ውድድር አሸናፊው የኔዘርላንድ ሯጭ ስቴፋን ኒልሰን (7:38:48) ነው ። 3,750 ተመልካቾችን በሚይዘው እና ቲኬቱ ሙሉ በሙሉ ተሽጦ ባለቀበት የአውሮጳ ሀለ የመወዳደሪያ ሥፍራ እጅግ በከፍተኛ ደረጃ አጓጊ ውድድሮች ተስተናግደዋል ። የጥር 18 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ፎቶ ከማኅደር፦ የአትሌቲክስ ተፎካካሪዎች በ1500 ሜትር ውድድርምስል፦ Leah Kohring/Beautiful Sports/IMAGO

ፈረንሳይ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የሜትዝ የሴቶች 3ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል ።  በዓለም አትሌቲክስ የብር ሜዳልያ በተሰጠው በዚህ የቤት ውስጥ ውድድር፦ አትሌት ብርቱካን ሞላ በ8:40.49 በመግባት አሸናፊ ሁናለች ። አትሌት ሽቶ ጉሜ በ8:41.18 ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ።  አትሌት አስቴር አረሪ ደግሞ 8:41.75 በመሮጥ 3ኛ ደረጃ ይዛለች ።  አትሌት ቤተልሔም ኦላና 6ኛ ደረጃ ይዛ ውድድሩን አጠናቃለች።

በወንዶች ምድብ 7:44.83 ሮጦ ያጠናቀቀው አትሌት አብዲሳ ፈይሳ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ። አትሌት ኤርሚያስ ግርማ በ7:51.80 አምስተኛ እንዲሁም አትሌት ለሚ ተሾመ በ7:55.07 ሰባተኛ ደረጃ ይዘው ውድድራቸውን አጠናቅቀዋል ።

የዱባይ ቡርጅ ግማሽ ማራቶን

በዱባይ ቡርጅ ግማሽ ማራቶን የኡጋንዳ እና ኬንያ ሯጮች ትናንት በወንድ እና በሴት አሸነፉ ። ኢትዮጵያ  በሴቶች ሦስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ፤ በወንዶች ደግሞ አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ አግኝታለች ። በትናንቱ ፉክክር፦ ኡጋንዳዊው ሯጭ ጆሹዋ ቼፕቴጊ (59: 26) በመሮጥ አንደኛ ወጥቷል ። ኬኒያዊው አትሌት ኒኮላስ ኪፕኮሪር (59: 28) ሁለተኛ እንዲሁም የታንዛኒያው ሯጭ አልፎንሴ ሲምቡ (59: 30)   ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቅቀዋል ። ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ሉሉ ነገራ እና አክሊሉ አስፋው ኬኒያዊው ኤኖስ ኪፕሩቶን ተከትለው ነው በአምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ያጠናቀቁት ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሐፍቱ ተክሉም በውድድሩ ዘጠነኛ ደረጃ ነው ያገኘው ።

ብርቱ ፉክክር በታየበት የሴቶች ተመሳሳይ ሩጫ፦ (1:06:57) በመሮጥ ለድል የበቃችው ኬኒያዊቷ አትሌት ኢሪኔ ቼፕቲን ናት ። የአገሯ ልጅ ዳይሲላህ ጄሮኖ በሁለት ሰከንድ ብቻ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፍታው ዘራይም አንደኛ ከወጣችው ኢሬኔ በ4 ሰከንዶች ብቻ ተበልጣ ለጥቂት የሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ።  ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሴባ ዲባ ፦ ኬኒያዊቷ ካጃክሊን ቼሮኖ እና የብሪታንያዋ ሯጭ አሌክሳንድራ ቤል በመከተል ስድስተኛ ደረጃ አግኝታ አጠናቅቃለች ።

በሐዋሳ ግማሽ ማራቶን ሩጫ ደግሞ፤ በወንዶች ፉክክር ሰምቼው ወልዴ (1:02:14,)1ኛ ወጥቶ አሸንፏል ። በሴቶች ፉክክር፦ 1:10:42 የሮጠችው ቤቴልሔም አስማረ አሸናፊ ሁናለች ። የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃውን፦ በወንዶች ጌታቸው ቄኒ እና ሡልጣን አብደላ እንዲሁም በሴቶች ትነበብ በጋ እና ዛተኔ ኮሬሞሽ አግኝተዋል ።

የቀድሞው የሊቨርፑል አጥቂ ሉዊስ ዲያዝ ለባዬር ሙይንሽን ሦስት ተከታታይ ግቦችን ሆፈንሀይም መረብ ላይ ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርቷልምስል፦ Frank Hoermann/Sven Simon/IMAGO

ሊቨርፑል የማታ ማታ በማንቸስተር ሲቲ ጉድ ሁኗል

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሲመራ የቆየው ሊቨርፑል በamንቸስተር ሲቲ ሽንፈት ገጥሞታል ። በምሽቱ ግጥሚያ የሊቨርፑሉ ዶሚኒክ ሶቦስላይ ከረፍት መልስ በ74ኛ ደቂቃ ላይ የተገኘችውን ቅጣት ምት በድንቅ ሁኔታ ከመረብ በመሳረፍ ነበር ቡድኑ 1 ለ0 እንዲመራ ያስቻለው ። ሆኖም ይህ ውጤት ብዙም አልዘለቀም ።

የሊቨርፑል ተጨዋቾች መከላከሉን ችላ ብለው በይበልጥ ወደ ማጥቃቱ በማዘንበላቸው በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ተደጋጋሚ ግቦች ተቆጥሮባቸዋል ። ግብ አዳኙ ኧርሊንግ ኦላንድ ፍጹም ቅጣት ምቱን በአሊሰን ቤከር ቀኝ ጥግ አክርሮ በመምታት ከመረብ አሳርፏል ። የሊቨርፑል መዘናጋት በኋላ ላይም በርናርዶ ሲልቫ እና ይኸው ኧርሊንግ ኦላንድ ሁለት ተጨማሪ ግቦችን እንዲያስቆጥሩ ሰበብ ሁኗል ። የማታ ማታም ሊቨርፑል መሪነቱ ተነጥቆ 3 ለ1 ጉድ ሁኗል ። የጥር 11 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቅቆ በጭማሪው የተገኘችው ሦስተኛዋ ግብን ኧርሊንግ ኦላንድ እንዳያስቆጥር ዶሚኒክ ሶቦስላይ ጥፋት ከሠራ በኋላ ምንም እንኳ እሱም ዶሚኒክን በመጎተኢትዮጵያየስፖርት ዘገባት ጥፋት ሠርቶ የተቆጠረች ቢሆንም በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ። ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር ለማጥቃት ወደ ባላጋራ ቡድን ሄዶ በነበረበት ወቅት ኧርሊንግ ኦላንድ በመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ ለማስቆጠር ሲሮጥ ይከተለው የነበረው ዶሚኒክ ኳሷን እንዳያጨናግፍ በመጎተቱ ግቧ ተሰርዛለች ። በዚህም ማንቸስተር ሲቲ ሊቨርፑልን 2 ለ1 ድል አድርጎ ወሳኝ ነጥብ ሰብስቧል ።

ሔሪ ኬን እስካሁን 24 ግቦችን በማስቆጠር በኮከብ ግብ አግቢነቱ በብቸኝነት እየመራ ነው ምስል፦ Frank Hoermann/Sven Simon/IMAGO

የትናንቱ ወሳኝ ድል ተደምሮለት ማንቸስተር ሲቲ አሁን በ50 ነጥቡ ከመሪው አርሰናል በስድስት ነጥብ ብቻ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።  ቅዳሜ ዕለት ሠንደርላንድን 3 ለ0 ያሸነፈው አርሰናል በ56 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡን ይመራል ። በበርመስ ሜዳ ቅዳሜ ዕለት አንድ እኩል የተለያየው አስቶን ቪላ በ47 ነጥብ እንዲሁም ቶትንሀምን 2 ለ 0 የሸኘው ማንቸስተር ዩናይትድ በ44 ነጥብ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ።  ቸልሲ ዎልቭስን 3 ለ1 ድል አድርጎ ነጥቡን 43 አድርሷል ። ሊቨርፑልን ከስሩ አድርጎ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ሊቨርፑል በ39 ነጥቡ ተወስኖ በስድስተኛ ደረጃ ይቃትታል ። ዌስትሀም ዩናይትድ፤ በርንሌይ እና ዎልቭስ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ ።

ጀርመን ቡንስሊጋ፦ መሪው ባዬር ሙይንሽን ትናንት ወደ አሊያንትስ አሬና ሜዳው የመጣው ሆፈንሀይምን 5 ለ1 ጉድ አድርጎ ሸኝቷል ። በእርግጥ ሆፈንሀይም ገና ጨዋታው በተጀመረ 17ኛ ደቂቃ ላይ ነበር ኬቪን አክፖጉማ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶበት በዐሥር ተጨዋቾች ውድድሩን ለማጠናቀቅ የተገደደው ። የቀድሞው የሊቨርፑል አጥቂ ሉዊስ ዲያዝ ለባዬር ሙይንሽን ሦስት ተከታታይ ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርቷል ። እስካሁን ከመረብ ያሳረፋቸው ኳሶች ብዛትንም 13 አድርሷል ። ቀሪዎቹ ሁለት ግቦች የግብ አዳኙ የሔሪ ኬን ናቸው ። ሔሪ ኬን እስካሁን 24 ግቦችን በማስቆጠር በኮከብ ግብ አግቢነቱ በብቸኝነት እየመራ ነው ። ለሆፈንሀይም ብቸኛዋን ግብ በ35ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው አንድሬ ክራማሪች ነው ።

የትናንቱ ባዬር ሙይንሽን ድል በቡንደስሊጋው የደረጃ ሠንጠረዥ በስድስት ነጥብ ቀዳሚ እንዲሁን አስችሎታል ።  ከስሩ 48 ነጥብ የሰበሰበው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ይከተለዋል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ ዕለት ቮልፍስቡርግን 2 ለ1 አሸንፏል ። ትናንት ጉድ የሆነው ሆፈንሀይም በ42 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ኮሎኝን ትናንት በገዛ ሜዳው 2 ለ1 ያሸነፈው ላይፕትሲሽ በ39 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 13 ነጥብ ብቻ ይዞ በ18ኛ ላይ የሰፈረው ሐይደንሀይም ከመሪው ባዬር ሙይንሽን በ41 ነጥቦች ይበለጣል ። ሌላኛው ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ሳንክት ፓውሊ ሐይድንሀይምን የሚበልጠው በአራት ነጥብ ብቻ ነው ።

በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ  የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች የነገ ሳምንት ይከናወናሉ ። የቱርኩ ጋላታሳራይ ከጣሊያኑ ጁቬንቱስ፤ የፈረንሣዮቹ ሞናኮ እና ፓሪ ሳንጃርሞ እንዲሁም የስፔኖቹ ቤኔፊካ እና ሪያል ማድሪድ በጥሎ ማለፉ ይፋለማሉ ። የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከጣሊያኑ አታላንታም የሚጫወቱት በተመሳሳይ ቀን ነው ። የረቡዕ ሳምንትም አራት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ይከናወናሉ ። የግሪኩ ኦሎምፒያኮስ ከጀርመኑ ባዬር ሌቨርኩሰን ፤ የአዘርባጃኑ ቃራባግ ከእንግሊዙ ነውካስል፤ የኖርዌይ ቦይዶ ግሊምት ከጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ፤  የቤልጂጉ ክለብ ብሩጅ ከስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ይፋለማሉ ። 

ሲያትል ሲሐውክስ ኒው ኢንግላንድ ፓትሪዮትስን ያሸነፈው 29 ለ13 በሀነ ልዩነት ነውምስል፦ Carlos Barria/REUTERS

በሱፐር ቦውል ፍጻሜ ሲያትል ሲሃውክስ ድል ተቀዳጀ

በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ እግር ኳስ ሊግ (NFL)ዓመታዊ የፍፃሜ ጨዋታ ማለትም ሱፐር ቦውል ፉክክር፦ ሲያትል ሲሃውክስ ድል ከማድረግም ባሻገር በኒው ኢንግላንድ ፓትሪዮትስ ላይ የደረሰባት ሽንፈት በተሳካ ሁኔታ መበቀል ችሏል ። ወትሮ እጅግ ድምቀት እና ብርቱ ፉክክር የሚታይበት ጨዋታው ረዘም ላለ ጊዜ ሞቅ ደመቅ ብሎ ባይታይም ከእረፍት ጊዜ መልስ የነበረው ጨዋታው ግን አስደናቂ ነበር ። የጥር 4 ቀን፣ 2018 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በትናንቱ የፍጻሜ ግጥሚያ፦ ሲያትል ሲሐውክስ ኒው ኢንግላንድ ፓትሪዮትስን ያሸነፈው 29 ለ13 በሀነ ልዩነት ነው ። በውድድሩ እንደሚያሸንፍ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ሲያትል ሲሐውክስ  በሱፐር ቦውል ድል ሲቀዳጅ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ። ሁለቱ ባላንጣ ቡድኖች በአሜሪካ ፉትቦል ታሪክ ለተደጋጋሚ ጊዜያት በሱፐር ቦውል ተፋጥጠው ያውቃሉ፥ ቀደም ሲልም ኒው ኢንግላንድ ፓትሪዮትስ ሲያትል ሲሃውክስን አሸንፎ ስለነበር የትናንቱ ድል ደጋፊዎቹን እጅግ አስቦርቋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW