በኦሮሚያ ክልል የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ
ዓርብ፣ ኅዳር 13 2017
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች በንጹሃን ላይ የሚፈጸሙ ገግድያዎች እና ሰሞነኛው አስደንጋች ቪዲዮ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መጋራቱን ተከትሎ የተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞያቸውን አሰሙ፡፡ተማሪዎቹ ባሰሙት ተቃውሞ መንግስት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊት እንዲሰማ እንዲሁ ሰብዓዊ ተቋማት ድርጊቱ እንዲያወግዙትም ነው የጠየቁት፡፡
በዚህ ሳምንት አንድን ወጣትአሰቃቂ በሆነ መልኩ ስደገደል የሚሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት መጋራቱን ተከትሎ ድርጊቱን በመቃወም የተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በሰልፍ ተቃውሞያቸውን አሰምተዋል፡፡ ተማሪዎቹ በሰላማዊ ሰልፉ “መንግስት በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ግድያ በማስቆም የሰላማዊ ዜጎች ደህንነትን ማስከጠበቅ አለበት” ሲሉም በዚህ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
የተማሪዎች ተቃውሞ
የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ሰላልኩላ በተባለ አከባቢ ተፈጸመ የተባለውን አንድ ወጣት አሰቃቂ በሆነ መልኩ እንዲገደል ስፈረድበት የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምስል ተመልክተው ስሜት ውስጥ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡
በትናትናው እለት የተቃውሞ ሰለፉ ከተካሄደባቸውየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ “ቪዲዮውን ተመልክተን ነው ስሜት ውስጥ የገባነው” ያለው አንድ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ትናንት በጠዋቱ ተማሪዎች ማልደው በመነሳት ቁርሳቸውን ወስደው ካስቀመጡ በኋላ ቅሬታቸውን የገለጹበት የተለያዩ የተቃውሞ ጽሁፎች በዚያው ላይ ማስቀመጣታቸውን አስረድቷል፡፡ ትናንት የነበረውን ሁኔታን ያስረዳን ተማሪው፤ “ጠዋት ተቃውሞ ነገር ነበር፡፡ ተማሪዎች ወጥተው መፈክሮች እያሰሙ ጊቢ ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች ስገቡ ነው ግን ወዲያው የቆመው፡፡ በርካታ ተማሪዎች በቁርስ ሰዓት ላይ ቁርሳቸውን ከወሰዱ በኋላ በዚያው ላይ ተቃውሞያቸውን የገለጹበት የተለያዩ ጽሁፎችን አስቀምጠው ነበር ሳይበሉ የወጡት፡፡ የሌላ ትምህርት ክፍል ባላውቅም እኛ ክፍል ውስጥ ገብተን ተምረናል፡፡ ግን እንዲህ ያለ ነገር ስጋት ስለሚፈጥር ተማሪዎች በስጋት ነበር ወደ ክፍል ያመሩት” ብለዋል፡፡
ትናንት የተማሪዎቹ የተቃውሞ ሰልፉ ከተካሄደባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ሌላኛው በሆነው አምቦ ዩኒቨርሲቲ፤ በርካታ ተማሪዎች ተቃውሞያቸውን ለመግለጽ ምሳቸውን ወስደው ሳይበሉ አስቀምጠው መውጣታቸውን አንድ የዩኒቨርሲቲው መምህር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ “ጊቢ ውስጥ ጀምረው ወደ ውጪ በር አከባቢ እያመሩ ፖሊስ እንዳይወጡ አደረጋቸ፤ ከዚያን ተበትነው ወደ ክፍል ተመለሱ፡፡ ምሳ ሰዓት ላይ ደግሞ ምሳ ወስደው ነው አስቀምጠው የወጡት” ብለዋል፡፡
ተማሪዎችን ያሳሰበው አሰቃቂ ግድያ
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ትናንት ተማሪዎች በሰልፍ ቅሬታቸውን ገልጸው እንደነበር ለዶቼ ቬለ ያረጋገጡት የዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መንግስቱ ቱሉ፤ ዛሬ ላይ ግን የመማር ማስተማር ሂደቱ በነበረው መደበኛ ሁኔታ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ “እውነት ነው በአምቦ ዩኒቨርሲቲም እንዲህ አይነት ነገር ነበር፡፡ ክስተቱ በሰላሌ አከባቢ በተከሰተውና በቪዲዮ ስዘዋወር የነበረውን አሰቃቂ ግድያ በመቃወም ነው፡፡ ተማሪዎች በሰላማዊ ሁኔታ ድርጊቱን አውግዘው ወደ ትናንት ወደ አራት አምስት ሰዓት አከባቢ ወደ ክፍል ተመልሰዋል፡፡ አሁን መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ ቀጥሏል” ነው ያሉት፡፡
በወለጋ ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ የተማሪዎች ተቃውሞ ሰልፍ ትናንት እንደነበር የገለጸው አንድ ተማሪ፡ “እኛ የተቃወምነው ነገር ህዝባችን የነበረበትና አሁን የምገኝበት ነገር ነው፡፡ መንግስት ለዚህ ተጠያቂ መሆኑን እንዲሁም ለህዝብ ከራራ የማያዳግም እርምጃ ድርጊቱን በፈጸሙት ላይ እንዲወስድ ነው የጠየቅነው፡፡ ሌላው በአሁን ላይ አጠቃላይ የኦሮሞ ህዝብ በተለይም ደግሞ የኦሮሞ አርሶአደር ያለበትን ነገር በመረዳት ለሰው መብት የሚሟገት የትኛውም ተቋም ህዝቡ ሰላምና እውነተኛ ነጻነት እንዲያገኝ የበኩሉን እንዲወጣ በሚል ነው ድምጻችንን ያሰማነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቶናል፡፡
በመቱ፣ አርሲ፣ ቡሌሆራ፣ ሀሮማያ፣ ሰላሌ እና ሌሎችም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ተቃውሞዎች በትናትናው እለት ተስተጋብቷል፡፡ ዛሬም በቀጠለው የተማሪዎች ተቃውሞ ሰልፍ በደምቢዶሎ፣ ጅግጅጋ፣ ወራቤ እና ዋቻሞን በመሳሰሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በምእራብ ሸዋ ጊንጪ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሰሞኑን የተሰማውን አሰቃቂ ግድያ እና አጠቃላይም በግጭቶች መባባስ ህብረተሰቡ ያለበትን ሁኔታ ተቃውመዋል፡፡
የመንግስት ምላሽ
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በኮሚዩኒኬሽን ቢሮው በኩል ትናንት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ከሰሞኑ “በጽንፈኞች ጭካኔ በተሞላ አኳሃን የተወሰደው ዘግናኝ ግድያ” ያለው ተግባርን በጥብቅ እንደሚያወግዘው አሳውቆ፤ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሚሰራ ጠይቀዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ውስጥ መሳሪያ የታጠቁ አካላት አንድን ግለሰብ ፀያፍ ስድም እየተሳደቡ የፈጣሪንም ስም እየጠሩ እንዲታረድ ስፈርዱበት የሚሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጋርቶ ብዙዎችን አስቆጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ስዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
ፀሀይ ጫኔ