1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የዩናይትድ ስቴትስና የሳዑዲ አረቢያ ግንኙነት ወደ ልዩ ወዳጅነት አደገ

ነጋሽ መሐመድ
ረቡዕ፣ ኅዳር 10 2018

ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሠልማን ዩናይትድ ስቴትስን ሲጎበኙ ከ7 ዓመት ወዲሕ የመጀመሪያቸዉ ነዉ።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛዉ ምሥራቅ «ምትክ የሌላቸዉ» መሪ ላሏቸዉ ልዑል ያደረጉት አቀባበልም ልዩ ነዉ።ልዑሉ ራት ተጋበዙ፣ ዋይት ሐዉስ፣ ቀይ ምንጣፍ ተዘረጋ፣ የክብር ዘቡ ተሰለፈ፣ ማርሹ ተንቆረቆረ----

ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት ስምምነት መሠረት ሳዑዲ አረቢያ አንድ ትሪሊዮን ዶላር አሜሪካ ዉስጥ ሥራ ላይ ታዉላለች።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለሳዑዲ አረቢያ አልጋወራሽ ለልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን አቀባበል ሲያደርጉላቸዉ።ምስል፦ Evan Vucci/AP Photo/picture alliance

የዩናይትድ ስቴትስና የሳዑዲ አረቢያ ግንኙነት ወደ ልዩ ወዳጅነት አደገ

This browser does not support the audio element.

ዩናይትድ ስቴትስና ሳዑዲ አረቢያበንግድ፣ በቴክኖሎጂ፣ በጦር መሳሪያ ሽያጭና በመከላከያ ያላቸዉን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ።ዩናይትድ ስቴትስን የጎበኙት የሳዑዲ አረቢያ አልጋወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሠልማንና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባደረጉት ሥምምነት መሠረት ሳዑዲ አረቢያ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ሥራ ላይ ታዉላላች።F35 የተባለዉን የአሜሪካንን ዘመናይ ተዋጊ ጄቶችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን፣የቴክኖሎጂ ዉጤቶችንና ቅንጡ ሸቀጮችን ትሸምታለች።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

«ምትክ ለሌላቸዉ መሪ» የተደረገዉ ግብዣ

ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሠልማን ዩናይትድ ስቴትስን ሲጎበኙ ከ7 ዓመት ወዲሕ የመጀመሪያቸዉ ነዉ።ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛዉ ምሥራቅ «ምትክ የሌላቸዉ» መሪ ላሏቸዉ ልዑል ያደረጉት አቀባበልም ልዩ ነዉ።ልዑሉ ራት ተጋበዙ፣ ዋይት ሐዉስ፣ ቀይ ምንጣፍ ተዘረጋ፣ የክብር ዘቡ ተሰለፈ፣ ማርሹ ተንቆረቆረ----ተዋጊ ጄቶች በዋሽግተን ሰማይ ላይ አረበበ-ለትርዒት።ብርጭቆ፣ ሹካ፣ ማንካዉ ተቅጨለጨለ--ምን ቅጡ።

የጋዛዎች ዕልቂት፣ የየመኖች ፍጅት፣ የጀማል ኻሾጂ ግድያ---ተረስተዋል።እሷ ለትራም፣ ለክብር እንግዳቸዉም ምናልባት «ልክልፍልፍ» ብጤ ናት።ግን ጋዜጠኛ-----ጋዜጠኛዉን አስታወሰች ጠየቀችም።

         የኻሾጂ ጉዳይ የቀሰቀሰዉ ጥያቄና አፈፀፋዉ ቁጣ

«ግርማዊነትዎ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የስለላ ድርጅት፣ ጋዜጠኛዉ ባሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደል እርስዎ አቀነባብረዋል ብሎ ደምድሟል።የ9/11 ቤተሰቦች እርስዎ እዚሕ ኦቫል ኦፊስ በመገኝትዎ ተበሳጭተዋል።አሜሪካኖች እርስዎን ለምን ያምናሉ።»

ጥያቄዉ ለአልጋ ወራሹ ነበር።መላሹ ግን አስተናጋጃቸዉ ናቸዉ።ዶናልድ ትራምፕ።«ማነሽ አንቺ?» ጠየቁ ትራምፕ ጠያቂዋን።

«ከABC ነኝ ጌታዬ?»

ትራምፕ ቀጠሉ---

ጋዛ ሕዝብ ምግብ፣ መጠለያም፣ መስፈሪያም ተነፍጎት በፍርስራሽና ቁሻሻ መሐል ለመዋል ማደር ተገድዷል።የአሜሪካና የሳዑዲ አረቢያ መሪዎች ሥለ ጋዛ ተኩስ አቁም ተነጋግራዋል።ሁነኛ ርምጃ ለመዉሰድ ግን አልወሰኑምምስል፦ Omar Al-Qattaa/AFP

«ሐሰተኛ ዜና፣ ABC ሐሰተኛ ዜና።በዚሕ ሥራ ከመጥፎዎቹ አንዱ ነዉ።ለማንኛዉም ጥያቄዉን ልመልስልሽ----የሆነ ሰዉ (ጀማል ኻሾጂን) ጠቅሰሻል፣ በጣም አወዛጋቢ ነበር።ወደድሺዉም ጠላሺዉም የጠቀስሺዉን ሰዉዬ ብዙ ሰዎች አይወዱትም ነበር።የሆነዉ ሆኗል።እሳቸዉ ግን የሚያዉቁት ነገር የለም።»

እያሉ---የሰዎች እኩልነትን፣ ሰብአዊ መብትን፣ የጋዜጠኝነት ነፃነትን በማክበር-ማስከበር፣  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማስረፅ-ማስጠበቅ «ከኔ በላይ ላሳር» የምትለዉ ትልቅ ሐገር ትልቅ መሪ ሟችን እየወነጀሉ በአስገዳይነት የሚጠረጠሩትን ልዑል ማወደሳቸዉን ቀጠሉ።ሥራም ያዉ እንደወትሮዉ ቀጠለ።

ሳዑዲ አረቢያ አሜሪካ ዉስጥ 1 ትሪሊዮን ዶላር ትወርታለች

ትራምፕ በሐገራቸዉ ነባር የንግድ ሸሪኮች ሸቀጦች ላይ ቀረጥ በመጨመራቸዉ የተቀዛቀዘዉን የዉጪ መዋዕለ ነዋይ ፍሰት ለማጠናከር ሳዑዲ አረቢያ 600 ቢሊዮን ዶላር አሜሪካ ዉስጥ ሥራ ላይ እንድታዉል ሪያዶችን ባለፈዉ ግንቦት ቃል አስገብተዉ ነበር።አልጋወራሹ አሁን 600 ቢሊዮኑ ወደ አንድ ትሪሊዮን ከፍ ማለቱን አስታወቁ።

«እንደማምነዉ፣ ክቡር ፕሬዝደንት የ600 ቢሊዮን ዶላሩ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ወደ 1 ትሪሊዮን ከፍ እንደምናደርግ ዛሬና ነገ ይፋ እናደርጋለን።»

የመዋዕለ ነዋይ ፍሰቱ ከቴስላ መኪኖች እስከ መዋቢያ ቅባታ-ቅባት፣ ከሆሊዉድ አክተሮች እስከ AI ቴክኖሎጂዎች የሚሸመትበትና ለ,ጉብኝት የሚዉል ነዉ።ከዚሕ በተጨማሪ ሳዑዲ አረቢያ F35 ተዋጊ ጄቶች፣ 300 ታንኮችና ሌሎች ጦር መሳሪያዎችን ከአሜሪካ ለመግዛት ተዋዉላለች።«F35 ጄቶችን ይገዛሉ።የሚገዙት ከሎክሒድ ነዉ።በጣም ጥሩ አዉሮፕላኖች ናቸዉ።» አሉ ትራምፕ።

ዋይት ሐዉስ፣ ከግራ ወደ ቀኝ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የሳዑዲ አረቢያዉ አልጋወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማንምስል፦ Saul Loeb/AFP

ዩናይትድ ስቴትስ «ለሰላማዊ አገልግሎት» የሚዉል የኑክሌር ተቋም ለሳዑዲ አረቢያ ለመንገንባት ትራምፕ ተስማምተዋልም።የሪያድ-ዋሽግተኖች ወዳጅነት ፀንቶ ሳዑዲ አረቢያ ከእንግዲሕ ለአሜሪካ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አብል ያልሆነች ልዩና ትልቅ ወዳጅ ናት።

ሁለቱ መሪዎች በዉይይታቸዉ ለዓመታት እየተነሳ የሚጣለዉን የእስራኤል ፍልስጤም የሁለት መንግሥት ጉዳይ፣ የኢራን አሜሪካኖችን የኑክሌር  ዉዝግብ፣ የጋዛ ተኩስ አቁምንም አዉስተዋል።ግን እንደ መናጆ።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW