1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩናይትድ ስቴትስና የቻይና ሽሚያ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 4 2015

አሜሪካኖችና ተከታዮቻቸዉ «አንድም ከኛ አለያም ከጠላቶቻችን» እያሉ መታበያቸዉ ያሳደረዉ ቅሬታ፣ግጭት፣ሁከትና አለመረጋጋትን ለማስቆም ምዕራባዉያን አለመቻላቸዉ ወይም አለመፈለጋቸዉ፣ እየከፋ የመጣዉ ድሕነት፣ ከቻይና የምጣኔ ሐብት ዕድገት ጋር ተዳምሮ የአረብ አፍሪቃ ፖለቲከኞች አማራጭ እንዲያማትሩ ሲያስገድድ----

Saudi-Arabien | Besuch chinesischer Staatschef Xi Jinping in Riad
ምስል Xie Huanchi/Xinhua/picture alliance

የቻይና ግስጋሴ፣የአሜሪካ ስልት፣የአረብና የአፍሪቃ ጥቅም

This browser does not support the audio element.

 

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ ሐገራቸዉ ስለመካከለኛዉ ምሥራቅ የምትከተለዉን የረጅም ጊዜ መርሕ «ለማረቅ» ለተባለለት ተልዕኮ ሰኔ 2009 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ካይሮን ሲጎበኙ፣ ቻይና ከአረቦች ጋር የነበራት ግኙነት አንድም በነዳጅ ዘይት-ሸመታ፣ሁለትም በጥንታዊ የንግድ ታሪክ ላይ የተንጠለጠለ ነበር።ኦባማ በ2014 የመጀመሪያዉን የአሜሪካ-አፍሪቃ  ጉባኤን ሲያተናግዱ፣ ሺ ጂፒንግ የአፍሪቃ፣የአረብና እስያን ምጣኔ ሐብት ከቻይና ጋር የሚያስተሳስሩበትን ዕቅድ አንደኛ ዓመት ይገመግሙ ነበር።ሺ መቀነትና መንገድ ባሉት ዕቅድ መሰረት የተቋቋመዉ የቻይና አፍሪቃ የትብብር መድረክ (FOCAC) 8ኛ የሚንስትሮች ስብሰባ ባለፈዉ ነሐሴ ሲደረግ፣ ጆ ባይደን ለአፍሪቃ አዲስ ያሉትን ስልት ይፋ አደረጉ።ባይደን ነገ ዋሽግተን ላይ ከአፍሪቃ መሪዎች ጋር የሚነጋገሩበትን ርዕስ እያነሱ ሲጥሉ ባለፈዉ አርብ ሺ ሪያድ ላይ የቻይና አረብን ስምምነት ተፈራረሙ ።የቻይና-አረብ፣ የአሜሪካ-አፍሪቃ ጉባኤዎች መነሻ፣ ዳራቸዉ ማጣቃሻ፣ የሲኖ-አሜሪካ እሽቅድምድም መድረሻችን ነዉ።
                                          
የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት አፄ ኃይለ ስላሴ «ፈረጅ ከምስራቅም መጣ-ከምዕራብ ስሙኒ ሰጥቶ አላድ የሚወስድ ነዉ» ይሉ ነበር-አሉ ያኔ የሰሙ።ለአፍሪቃ፣ለአረብ ይሁን ለሌላዉ አዳጊ ዓለም የሠላም፣የልማት፣ዕድገቱ አብይ መሰረት የየሐገሩ ሕዝብ የሚመራና የሚያስተባብረዉ ፖለቲከኛ እንጂ የዉጪ ኃይል ይሆንል ብሎ ማሰብ በርግጥ መጃጃል ነዉ።
በአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች ይማቅቁ የነበሩ የአፍሪቃ ሐገራትን ነፃ ለማዉጣት የሚታገሉ ቡድናትና ሾሻሊስታዊ ርዕዮተ-ዓለም የሚቃነቅኑ የአፍሪቃ መንግስታትን ከ1960ዎቹ ጀምራ ትረዳ የነበረችዉ ቻይና በ1990ዎቹ ምጣኔ ሐብቷ ሲጠረቃ በጥቁሮቹ አሐጉር እግሯን ለመትከል ብዙ መድከም አላስፈለጋትም ነበር።
የአረቦችና የቻይና ግንኙነት ደግሞ ከአፍሪቃና ቻይናም ራቅ ያለ ዘመን የሚያጣቅስ ነዉ።«የሐር ጎዳና» ይባል በነበረዉ የንግድ መስመር አማካይነት ከተሳሰሩ ከ2000 ዘመናት በላይ አስቆጥረዋል።የኦስማን ቱርክ አገዛዝ በብሪታንያና ፈረንሳይ ከተተካ በኋላ፣ የዘመን ሒደት ያዛገዉ የአረብ-ቻይኖች ግንኙነት በነገስታት-ኮሚንስታዊ ተቃራኒ ርዕዮተ ዓለም መካረሩ የለንደን-ፓሪሶችን ስፍራ ለወረሱት ለዋሽግተኖች የበላይነት ምቹ መደላድል ፈጥሯል።

ምስል Shen Hong/Xinhua News Agency/picture alliance

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ምስራቅ አዉሮጳን ለ50 ዘመናት ያክል ፈጥርቃ የያዘችዉ የሶቭየት ሕብረት መፈረካከስ የፈጠረዉ አዲስ አስተሳሰብ፣ አሜሪካኖችና ተከታዮቻቸዉ «አንድም ከኛ አለያም ከጠላቶቻችን» እያሉ መታበያቸዉ ያሳደረዉ ቅሬታ፣ግጭት፣ሁከትና አለመረጋጋትን ለማስቆም ምዕራባዉያን አለመቻላቸዉ ወይም አለመፈለጋቸዉ፣ እየከፋ የመጣዉ ድሕነት፣ ከቻይና የምጣኔ ሐብት ዕድገት ጋር ተዳምሮ የአረብ አፍሪቃ ፖለቲከኞች አማራጭ እንዲያማትሩ ሲያስገድድ የቤጂንግ  መሪዎች ብሶቱን እያራገቡ በየስፍራዉ ሰርስረዉ እንዲገቡ ጥሩ ስንጥቅ-ሽንቁር ሆኗል።

«አንድም ከኛ አለያም ከጠላቶቻችን» የሚለዉን ማስፈራሪያ እንደ በጎ መርሕ ሲያቀነቅኑ የነበሩት የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆር ደብሊዉ ቡሽና የብሪታንያዉ ወዳጃቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር የኢራቅን ገዢዎች በሐሰት ወንጅለዉ በ2003 ያቺን ሐብታም፣የጥንት ስልጣኔ ሐገር አስወርረዉ ሚሊዮኖችን አስፈጅተዋል።ብዙ ሚሊዮኖችን አሰድደዋል።ሐገሪቱን አጥፍተዋል።

የአንግሎ-አሜሪካ ወራሪዎች ያኔ የነገሩን  ኢራቅን ሰላም፣ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ ርትዕት የሰፈነባት ሐገር ለመመስረት ማቀዳቸዉን ነበር።የቡሽ-ብሌር እብሪት ማብረጃ የሆነችዉ ሐገር ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሺያ አል ሱዳኒ ዘንድሮ በሐያኛ ዓመቱ ከሺ ጂፒንግ ጋር ጉባኤ ሲቀመጡ ቤጂንጎችን አመሰገኑ።ሪያድ-ባለፈዉ አርብ።
«እንዲሕ ዓይነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ  ከጥልቅ መግባባት የመነጨ፣ ሚዛናዊና ሁሉን ያማከለ የዉጪ መርሕ የታየበትን ጉባኤ ማድነቅ እወዳለሁ።መርሑ ሕዝቦቻችንን፣ የኛን የአረብ መንግስታትን፣ የሐገራችን ኢራቅን ጥቅም የሚያስከብር፣ ፀጥታን፣መረጋጋትንና ብልፅግናን የሚያበረታታ (ነዉ።)»

ኢትዮጵያዊዉ የጂኦ-ፖለቲክስ ሊቀ-ሊቃዉንት መስፈን ወልደ ዩናይትድ ስቴትስ ስለ መካከለኛዉ ምስራቅ የምትከተለዉን መርሕ ከገንዘብ ወዳዱ የኮምፒዉተር አዋቂ ብልጠት ጋር ያመሳስሉታል።«የኮምፒዉተር አዋቂዉ በየኮምፒዉተሩ «ቫይረስ»  ይለቅና» አሉ መስፍን ባንድ መፅሐፋቸዉ « ፀረ-ቫይረስ» ፕሮግራም ይሸጥልሐል።አሜሪካኖችም ከጠላቶች ላንዱ ሁለንተናዊ ድጋፍ እየሰጡ ችግሩን ያንሩትና ሁለቱን ወገኖች ማስታረቅ ያለብን እኛና እኛ ብቻ ነን ይላሉ-የማይቻለዉን የሚቻል እያስመስላሉ።

በሜአሪካኖች ግፊት በ1993 የእስራኤልና የፍልስጤም ባለስልጣናት ኦስሎ ላይ በተፈረሙት ዉል መሰረት ከረመላሕ ከተማ ከንቲባነት ብዙም የማበልጠዉን ስልጣን ከቀድሞ አለቃቸዉ የወረሱት የፍልስጤሙ መሪ ማሕሙድ አባስ አንግሎ-አሜሪካ እስራኤልን ወነጀሉ።አባስ የራሳቸዉን ጥፋት፣የአረቦችን ስሕተት፣የተቀረዉን ዓለም ስግብግብነት፣ የቅርቡ ዘመንን ታሪክም አልፈዉ ለጥፋት-ስሕተቱ ሁሉ የ1917ቱን የባልፎር  አዋጅን ተጠያቂ ያደርጋሉ
                                                          
«በባልፎር አዋጅና አዋጁ በሰጠዉ ስልጣን የተሳተፉት ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ የፍልስጤም ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቁና ካሳም እንዲከፍሉ አጥብቀን እንጠይቃለን።እስራኤልም ይቅርታ መጠየቅና ካሳ መክፈል ይገባታል።»
 የመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት እንዳበቃ የታወጀዉ የባልፎር ደንብ የጦርነቱ አሸናፊዎች እስከዚያ ዘመን ድረስ «ፍልስጤም« ይባል በነበረዉ በኦስማን ቱርክ ግዛት የየሁዲዎች ብሔራዊ ሐገር መመስረቱን እንደሚደግፉ ያረጋገጡበት አዋጅ ነዉ።
ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ስልጣን በያዙ በመንፈቁ ካይሮ ላይ ያደረጉት  ንግግር ሐገራቸዉ ሲርቅ ከ1917 ሲቀርብ ከ1948 ጀምራ ስለመካከለኛዉ ምስራቅ የምትከተለዉን መርሕ ለማረቅ ወይም ከዘመኑ አስተሳሰብና የሕዝብ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም ያለመ መሆኑን አመልካች ነበር።ግን  ሰዉዬዉ ብዙ ብለዉ ምንም ሳያደርጉ ሥልጣናቸዉን ለተረኛ አስረከቡ።

ቻይና በዱባይ ኤክስፖ 2020 ምስል Wang Dongzhen/Xinhua News Agency/picture alliance

ተረኛዉ አክራሪዉ ሐብታም ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራም ነበሩ።ትራምፕ ስልጣን ከመያዛቸዉ በፊት ካሳጧቸዉ መሪዎች አንዱ የሳዑዲ አረቢያዉ ንጉስ ሰልማን ነበሩ።
                                     
«ሳዑዲ አረቢያን ከአደጋ እንጠብቃለን።ንጉሱን፣ ንጉስ ሰልማንን አወዳቸዋለሁ።ግን እላቸዋለሁ።ንጉስ ሆይ እኛ እንጠብቅዎታል።እኛ ባንኖር ስልጣን ላይ ሁለት ሳምንት እንኳን አይቆዩም።ለሚጠብቅዎችት ጦር መክፈል አለብዎት።»
ስልጣን ከያዙ በኋላ ግን መጀመሪያ የጎበኙት ሪያድን ነበር።የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደንም በምረጡኝ ዘመቻቸዉ ወቅት የሪያድ ገዢዎችን በተለይም አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማንን በነብሰ አስገዳይነት ሲወነጅሉ፤ ሲያወግዙ ሲያሳጡ ነበር።ባይደን ከፑቲን ጋር ሲለተሙ ግን ሪያድን ጎበኙ።የሪያድ ገዢዎች ለመጣ-ለሔደዉ የአሜሪካ መሪ ማጎብደዱ አሁን የሰለቻቸዉ ይመስላል።በተለይ በዩክሬን ሰበብ  ምዕራባዉያን ከሩሲያ ጋር በገጠሙት ተዘዋዋሪ ጦርነት ሳዑዲ አረቢያ የምታመርተዉን ነዳጅ ዘይት እንድትጨምር ዋሽግተኖች የሚያደርጉት ጠንካራ ግፊት ሪያዶችን ወደ ቤጂንግ እንዲያማትሩ ሳያስገድዳቸዉ አልቀረም።አልጋወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን ባለፈዉ ሳምንት ያስተናገዱትን የቻይና አረቦች ጉባኤን አዲስ ምዕራፍ አሉት።
«ይሕ ጉባኤ በሐገሮቻችን መካከል ላለዉ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት፣የጋራ ፍላጎታችንን  ለማርካት በሚጥቅሙን መስኮች ያለንን ወዳጅነት የሚያጠናክር፣ ሕዝቦቻችን ለወደፊቱ የሚመኙትን ለማሳካት የሚጠቅም ነዉ።መጪዉ ትዉልድ እንዲበለፅግ በአረብ መንግስታትና በቻይና መካከል  በመዋዕለ ነዋይ ፍሰት፣በንግድና በገንዘብ ያለዉን የሁለትዮችና ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ማጠናከር አለብን።በፖለቲካዉ መስከም በዓለም አቀፍ መድረክ ትብብራችንን ማጎልበት ይገባናል።»

ቻይና መካከለኛዉ ምስራቅ ዉስጥ ያላት የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት 273 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።ከነዳጅ ፍጆታዋ 17 ከመቶዉን የምትሸምተዉ ከሳዑዲ አረቢያ ነዉ።የአልጄሪያ፣ የግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና የንግድ ተሻራኪም ናት።ካንዲት ሳዑዲ አረቢያ ጋር የ30 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ልዉዉጥ በቀደም ተፈራርመዋል።ቻይና ለ70 ዓመታት የሚፀና የጋዝ ግዢ ከቀጠር ጋር ተስማምታለች።

ይሁንና አረቦች በተለይም የፋርስ ባሕረ-ሰላጤ አካባቢ ሐገራት አሁንም ቢሆን ከዘመናይ ጦር መሳሪያ እስከ ነዳጅ ማምረቻ ማሽን በገፍ የሚሸምቱት ከዩናይትድ ስቴትስና ከምዕራብ አዉሮጳ ሐገራት ነዉ።አፍሪቃ ዉስጥ ግን ምዕራባዉያን ሐገራት  የነበራቸዉ ጠንካራ መሰረት እየተሸረሸረ፣ተፅዕኖቸዉም እየረገበ ነዉ።
ቻይና አፍሪቃ ዉስጥ ያላት የመዋለ ንዋይ ፍሰት ከ70 ቢሊዮን በልጧል።ለአፍሪቃ ሐገራት አንደኛ አበዳሪ ሐገርም ቻይና ናት።
በ2014 የያኔዉ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የአፍሪቃ መሪዎችን ዋሽግተን ላይ ሰብስበዉ ልዕለ ኃያሊቱ ሐገር አፍሪቃን በእኩል ደረጃ እንደምታያት፣ አፍሪቃዉያንን እንደምትረዳ ቃል ገብተዉ ነበር።ይሁንና አፍሪቃ አሜሪካዊዉ መሪ የፓሪስ-ለንደን መሪዎችን ተከትለዉ የሊቢያን ጠንካራ ገዢ ባደባባይ ካስረሸኑ፣ሐብታም-አረብ አፍሪቃዊቱን ሐገር ለወርሮ በሎች ካስረከቡ በኋላ ለአፍሪቃ መሪዎች የገቡት ቃል ለአፍሪቃ ሕዝብ ከሽንገላ ብዙም ያለፈ አልነበረም።

ጆ ባይደን ከደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዝደንት ሲሪየል ራማፎዛ ጋር ምስል Pete Marovich-Pool/Getty Images

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ መርሕም በጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ዘመን ከነበረዉ ብዙ የተለየ አልነበረም።የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስቴር በቅርቡ እንዳስታወቀዉ አሜሪካ አሸባሪዎችን ለመዋጋት በሚል ከ2002 ጀምሮ በ22 የአፍሪቃ ሐገራት ዉስጥ ጦር አስፍራለች።

ከሞሪታንያ እስከ ሶማሊያ፣ከማሊ እስከ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ከኢትዮጵያ እስከ ሊቢያ ዛሬም በርስ በርስ ግጭትና በአሸባሪዎች ጥቃት ሺዎች ይረግፋሉ።ሚሊዮኖች ይሰደዳሉ።ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ማሊ፣ቡርኪና ፋሶ፣ጊኒ፣ ሱዳን፣ቻድ የተሳካ፣ ኒዠርና ጊኒ ቢሳዉ የከሸፈ መፈንቅለ መንግስት ተደርጎባቸዋል።በተለይ የማሊ፣የቡርኪና ፋሶና የጊኒ የሲቢል መሪዎችን ከስልጣን እያሰወገዱ የየሐገራቱን የመሪነት ስልጣን የያዙት የጦር መኮንኖች በአሜሪካ ጦር የሰለጠኑ ናቸዉ።

የፕሬዝደንት ጆ ባይደን መስተዳድር ባለፈዉ ነሐሴ ከሰሐራ-በስተደቡብ ለሚገኙ የአፍሪቃ ሐገራት አዲስ ያለዉን ስልት (ስትራቴጂ) መንደፉን አስታዉቋል።የአዲሱ ስልት ምንነት፣ጥቅም፣ ጉድለት ጉዳቱ ሲተነተን ግን ቻይና የመሰረተችዉ የአፍሪቃና የቻይና የትብብር መድረክ 8ኛዉ የሚንስትሮች ስብሰባ «በድል» መጠነቃቁ ተዘገበ።
ባይደን ነገ በሚያስተናግዱት የአፍሪቃና የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች  ጉባኤ ላይ የሚሉ-የሚደርጉትን ሲያሰላስሉ ሺ አረቦችን ሪያድ ላይ ሰብስበዉ አረቦች የሚፈልጉ፣የሚመኙ፣ ግን የማያደርጉትን ነገሯቸዉ።ከ1967ቱ ጦርነት በፊት በነበረዉ ድንበር ላይ  ነፃ የፍልስጤም መንግስት መመስረቱን እንደግፋለን አሉ።እስላም ጥላቻን እንቃወማለን።
                                      
«እስላም ጥላችን ለማስወገድ፣ ፅንፈኝነትን ለማለዘብ፣አሸባሪነትን  ከተወሰነ ኃይማኖት ወይም ጎሳ ጋር ማቆራኘትን ለማጥፋት በጋራ መጣር አለብን።ሰላም፣ልማት፣የፍትሕን የጋራ እሴት፣ርትዕትን፣ዴሞክራሲንና ለሰዉ ልጅ ሁሉ ነፃነትን መደገፍና የስልጣኔን አብነት አንዳችን ለሌላችን ያለንን አክብሮት ማበረታት አለብን።»

ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማምስል AP

ግን ሺንጂያግ በሚኖሩ የኡግሁሩ ሙስሊሞች ላይ ለሚፈፀመዉ ግፍና በደል ተጠያቂዉ ማን ይሆን።

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW