1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የአሜሪካኖች የምርጫ ዘመቻ

ሰኞ፣ ጥር 27 2016

ከፖለቲካዉ ጥበብ፣ ከሴራ-ሸፍጥ፣መጠላለፉ ይልቅ ገዝቶ መሸጥን፣ ሸጦ የማትረፍ፣ የመክበር መንሰሩን ንግድ፣ ድለላ የተካኑበት ዶናልድ ጆን ትራምፕ ዳግም ዋይት ሐዉስ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት-ፉክክር ከሥልጣን ፍላጎት፣ ወይም የፖለቲካ መርሕን ሥራ ላይ ከማዋል ጉጉት በላይ ቁጭት፣ እልሕና ሽንፈትን መበቀል ነዉ።

ሁለቱ አዛዉንቶች የሚያደርጉት ፉክክር ከ2020 ከተደረገዉ ብዙም የተለየ የመርሕ ለዉጣ መታያቱ እያጠራጠረ ነዉ
በመጪዉ ሕዳር በሚደረገዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ይፎካከራሉ ተብለዉ የሚጠበቁት ባይደንና ትራምፕ

ማሕደረ ዜና፣ የአሜሪካ ምርጫ፣ ዉዝግብና ክሱ

This browser does not support the audio element.

አሜሪካኖች በዕለት-ከዕለቱ ኑሮ ዉጣ ዉረድ፣ በሩጫ ጥድፊያ ወከባዉ፣ መሐል የመሪዎች ምርጫ እያሉ ነዉ።ልዕለ ኃያሊቱ ሐገር ከምጣኔ ሐብቱ ዕድገት-ዉድቀት፣ከማስወረድ-መብት መነፈግ-አለመነፈግ፣ ከስደተኞች መቀበል-አለመቀበል በተጨማሪ ከአዞቮ ባሕር ጠረፍ እስከ ቀይ ባሕር ግርጌ፣ ከጋዛ ሰርጥ እስከ ኮሪያ ልሳነ ምድር የተዘፈቀችበት ጦርነትና ዉዝግብ ብዙዎች እንዳሉት ሕዝቧን አለቅጥ ከፋፍሎታል።በመጪዉ ሕዳር 5፣ 2024 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሊደረግ በታቀደዉ ፕሬዝደንታዊዉ ምርጫ ይፎካከራሉ ተብለዉ የሚጠበቁት ፖለቲከኞች ተንታኞች እንደሚሉት እድሜያቸዉ ለፆም-ፀሎት-ምሕላ እንጂ ለፖለቲካዉ ዉጣ ዉረድ ያረጁ-ያፈጁ፣ መርሐቸዉ የተሞከረ-ምናልባትም የሰለቸ በመሆኑ ብዙም አዲስ ነገር እይጠበቀም።አንዳዶች የመሪ ዳግም አገልግሎት ሪሳይክል ሲሉት በሐረሮች አገላለፅ የዓለም መሪዋ ሐገር መሪ «እየገረበች ነዉ» ያሰኝም ይዟል።ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።
ከፖለቲካዉ ጥበብ፣ ከሴራ-ሸፍጥ፣መጠላለፉ ይልቅ ገዝቶ መሸጥን፣ ሸጦ የማትረፍ፣ የመክበር መንሰሩን ንግድ፣ ድለላ የተካኑበት ዶናልድ ጆን ትራምፕ ዳግም ዋይት ሐዉስ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት-ፉክክር ከሥልጣን ፍላጎት፣ ወይም የፖለቲካ መርሕን ሥራ ላይ ከማዋል ጉጉት በላይ ቁጭት፣ እልሕና ሽንፈትን መበቀል ነዉ።
ቱጃሩ ፖለቲከኛና ደጋፊዎቻቸዉ እንደሚሉት በ2020 በተደረገዉ ምርጫ ለሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣን ባደረጉት ፉክክር የተሸነፉት ወይም ተሸንፈዋል የተባለዉ ተቀናቃኞቻቸዉ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች የተሰጠዉን ድምፅ በማጭበርበራቸዉ ነዉ።የምርጫዉን ዉጤት በመቃወም ትራምፕ አደራጁት የተባለዉ ሰልፈኛ ሕዳር 6፣2021 የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤቶች መቀመጫ ሕንፃ ካፒቶልን በመዉረሩ የሰዉ ሕይወት ጠፍቷል፣ ሐብት ንብረትም ወድሟል።

በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ  «አሳፋሪ» የተባለዉ ያ አመፅ፣ ጥቃትና ሥርዓተ አልበኝነት የ77 ዓመቱን አዛዉንት ዛሬም ድረስ እያሳደነ-እያሳደዳቸዉ ነዉ።ባለፈዉ ዓመት የኮሎራዶ ግዛት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ የ2021ዱን አመፅ-ጥቃትና ጥፋት አነሳስተዋል በሚል በምርጫዉ መወዳደር እንደሌለባቸዉ  አግዶ ነበር።

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ በከፊልምስል Brian Snyder/REUTERS

 

የፍርድ ቤቱ ክስና የትራምፕ ተስፋ

 

ሰዉዬዉ እንደ ድለላ-ንግድ ትርፉ ሁሉ ለክስ፣ ሙግት፣ ክርክር እንግዳ አይደሉም።በቅርቡ አዲት ሴት አበሻቅጠዋል በሚል ወንጀል 83 ሚሊዮን ዶላር ተቀጥተዋል።ከሴቶች መድፈር-እስከ ግብር ማጭበርበር የሚደርሱ ብዙ ክሶች ተመስርተዉባቸዋልም።የኮሎራዶዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔ እንደተሰማም ለዩናይትድ ስቴትስ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቀዉ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ለፊታችን ሐሙስ ቀጥሯል።
ትራምፕ ሥልችት ያላቸዉ ይመስላል።« አንዱን ሲሉት አንዱ» ይላሉ።«አንዱን ስለዉ ሌላዉ ይመጣል።የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ከኮሎራዶ ተቀብሎ ይዞታል።እና እነሱ ይወስናሉ።»

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የፊታችን ሐሙስ የሚሰጠዉ ብይን የዘንድሮዉን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ይወስናል።አብዛኛ ዳኞች በሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዝደንቶች የተሾሙ በመሆናቸዉ ትራምፕ ለፕሬዝደንትነት ከመወዳደር አይታገዱ ይሆናል የሚል ግምት አሳድሯል።ጉዳዩን የሚከታተለዉ የአሶስየትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ማርክ ሸርማን  እንደሚለዉ ፍርድ ቤቱ ለትራምፕ ከወሰነ የትራምፕ ስምና ዝና ይናኛል።
«ትራምፕ ክሱን ካሸነፉና የሪፐብሊካን እጩነታቸዉ ከተረጋገጠ  በመላዉ ሐገሪቱ የምርጫ ካርድ ላይ ስማቸዉ በጉሉሕ ይታያል።ዉሳኔዉ ከዚሕም በተጨማሪ በእጩነት ምርጫዉ ትራምፕ መወዳደር አለመወዳደራቸዉን የሚበይንም ነዉ።»
ትራምፕን ከፖለቲካ ተቀናቃኝነት በላይ እንደ ደመኛ ጠላት የሚቆጥሩት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ትናንት ኒቫዳ ላይ እንዳሉት  ትራምፕ በየትኛዉም መገንድ ቢሆን አይመረጡም።
«በዚሕ ከልብ በመነጨ ቀላል መልዕክት እጀምራለሁ።አመሰግናለሁ፣ አመሰግናለሁ፣ አመሰግናለሁ።የአሜሪካ ፕሬዝደንት መሆን የቻልኩት በእናንተ በሁላችሁም ምክንያት ነዉ።ካሜላ ሐሪስ ታሪካዊ ምክትል ፕሬዝደንት የሆነችዉ በናንተ ምክንያት ነዉ።ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞዉ ፕሬዝደንት የሆኑት በናንተ ምክንያት ነዉ።ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ተሸናፊ እንዲሆኑ ምክንያቱ እናንተ ናችሁ።»

የሪፐብሊካን ፓርቲን ለመወከል የሚፎካከሩት ኒኪ ሔሊይ በዉድድሩ የቀድሞ አለቃቸዉን እየተከተሉ ነዉምስል Robert F. Bukaty/AP Photo/picture alliance

የሪፐብሊካኖቹ ዕጩዎች

 

ዶናልድ ትራምፕ መጀመሪያ የሪፐብሊካን እጩ አከታትሎ ዳግም ፕሬዝደንት የመሆን ተስፋቸዉን የሚቀናቀኑት ፕሬዝደንት ባይደን፣ የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት፣ ወይም የኮሎራዶን የመሳሰሉ ዳኞችና ፍርድ ቤቶች ብቻ አይደሉም።ትራምፕ በዘመነ -ሥልጣናቸዉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር አድርገዉ የሾማቸዉ ኒኪይ ሐሌይ የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ለመሆን ከትራምፕ ጋር እየተፎካከሩ ነዉ።

«ለዶናልድ ትራምፕ ሁለት ጊዜ ድምፅ ሰጥቻለሁ።በእሳቸዉ አስተዳደር ወቅት አሜሪካንን በማገልገሌ በማጥም እኮራለሁ።ይሁንና ሁል ጊዜ (ትራምፕን) ብጥብጥ ይከተላቸዋል።ሁላችሁም ታዉቋቸዋላችሁ።ለተጨማሪ 4 ዓመታት ሐገራችን የተመሰቃቀለች፣የብጥብጥና ዓለምም እሳት የሚነድባት ሊሆኑ አይገባም።ልንድን አንችልም።»
የሪፐብሊካን እጩዎችን ለመለየለት  በተደረገዉ ፉክክር 14 ፖለቲከኞች ተሳትፈዉ ነበር።አሁን የቀሩት የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የቀድሞዋ አምሳደር ኒኪይ ሔሊ ናቸዉ።ትራምፕ ሄሊንም በሰፊ ልዩነት እየመሩ ነዉ።

ትራምፕ በፍርድ ቤቱ ሙግት፣ በዴሞክራቶቹ ጫና፣ በሔሊ ትችትና ፉክክር መሐል ያስመዘገቡት ታላቅ ድል በተቀናቃኞቻቸዉ ላይ ለሚያወርዱት ስድብና አሽሙር ጥሩ ዱላ ሆኖላቸዋል።ከዚሕ ቀደም «እንቅልፋሙ» እያሉ የሚወርፏቸዉ ባይደንን «ጠማማ ወይም ተንኮለኛ» ብለዋቸዋል።ለሔሊም ማጣጣያ አላጡም። 
«ባለፉት ሶስት ወራት ዉስጥ ጠማማዉን ባይደንን በያንዳዱ ምርጫ አሸንፈናቸዋል።እያንዳዱን ምርጫ በሚባል ደረጃ።እሷ ግን እነዚያን ምርጫዎች አላሸነፈችም።ይሕ ለንናንተ የተለመደዉ የድል ንግግር ሊሆን አይችልም።ይሁንና በጣም መጥፎ ሌሊት ያሳለፈች ሴትዮ  አሸነፍኩ ማለት አይገባትም።በጣም መጥፎ ሌሊት አሳልፋለች።»
የምጣኔ ሐብት እንድገት፣ የድንበር ፀጥታና የስደተኖች ይዞታ፣ የዉጪ መርሕ፣ ፅንሥ የማስወረድ መብት፣ ጤና ትምሕርት በዘንድሮዉ ምርጫ የመራጮችን ክፍተኛ ትኩረት የሚስቡ ናቸዉ።
የኮቪድ 19 ሥርጭት ያደቀቀዉ ኤኮኖሚ፤ ከቻይና የገጠመዉ ጠንካራ ፉክክር፣ ለዉጪ መንግስታት ለጦር መሳሪያ ድጋፍ ከሚሰጠዉ ገንዘብ ጋር ተዳምሮ የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት ከፍተኛ ፈተና ዉስጥ እንደጣለዉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።ባይደን ሥልጣን እንደያዙ ማሻቀብ የጀመረዉ የዋጋ ንረትም አሁንም እየተንቻረረ ነዉ።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ካደረጉት የምርጫ ዘመቻ አንዱምስል Nathan Howard/Getty Images

የባይደን መስተዳድር ድክመቶች

 

ባይደንግን መስተዳድራቸዉ ጠንካራ ኤኮኖሚ መንገንባቱን ይናገራሉ።እንዲያዉም ባይደን ትራምፕን በ1920ዎቹ ማብቂያ ዩናይትድ ስቴትስ ከታላቁ የምጣኔ ሐብት ድቀት ዶለዋታል ከሚባሉት ከፕሬዝደንት ኸርበርት ሁቨር ጋር ያመሳስሏቸዋል።

«ጠንካራ ኤኮኖሚ መገንባታችንና አሁን እየተጠናከረ መሆኑን ትራምፕ ያዉቁታል።ይሕ ለአሜሪካ ጥሩ የመሆኑን ያክል ለእሳቸዉ ፖለቲካ መጥፎ መሆኑን ያዉቁታል።ትራምፕ የኸርበርት ሑቨር ፕሬዝደት አይነት መሆን እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።ወዳጄ ዶን ! መጥፎ ዜና ላሰማሕ።በጣም ዘገየሕ፣ በአሜሪካ ታሪክ ሥልጣን ሲይዙ ከነበረዉ ሥራ በጣም ጥቂት ብቻ ትተዉ ከስልጣን የተሰናበቱ ሁለት ፕሬዝደንቶች ኼርበት ሁቨርና አንተ ናችሁ።ኼርበርት ሁቨር።አዎ።ዶናልድ ኼርበርት ሁቨር ትራምፕ።»
ጆ ባይደን 81 አመታቸዉ ነዉ።ዶናልድ ትራምፕ 77።ለአሜሪካ ፖለቲካዊ ባሕል ሙት መዉቀስ፣ተቀናቃኝን ማበሻቀጥ ለአዛዉንቶች ጭምር እንግዳ አይነት አልሆነም።ዶናልድ ትራምፕ ግን ምጣኔ ሐብቱ በቅርቡ የተነቃቃዉ በኔ ጥረት እንጂ በባይደን አስተዳደር መርሕ አይደለም ባይ ናቸዉ።
«የሚቀጥለዉ የትራምፕ የምጣኔ ሐብት እድገት የሚጀምረዉ ሕዳር 5፣ 2024 ነዉ።እስካሁን እነሱ ያላቸዉ የአክሲዎን ገበያዉ ከፍ ማለቱ ነዉ።አክሲዎኑ ከፍ ያለዉ በዚሕ ምርጫ እኛ እንደምናሸንፍ ሰዎች ስለሚያስቡ ነዉ።ትናንት አይታችሁ ከሆነ አላዉቅም፣ የቻይና ምጣኔ ሐብት ወድቋል።ይኽ የሆነዉ እኛ የአይዋዉን ምርጫ ሥላሸነፍኩ ነዉ።እዉነቴን ነዉ።» 
ፅንስ ማስወረድ ደንብ ወይም ሕግም ብዙ አወዛጋቢ ርዕስ ነዉ።ፅንስ የማስወረድ መብት በዘንድሮዉ ምር|ጫ ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገዉ ሁለት ፍርድ ቤቶች ፅንስ የማስወረድን መብት የሚያግዱ ዉሳኔዎች በማሳለፋቸዉ ነዉ።የድንበር ፀጥታና በተለይ ከደቡብ አሜሪካ ሐገራት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገቡ ስደተኞች ጉዳይም የመራጮችን ትኩረት፣ የተመራጮችን መርሕ የሚያስፈትሹ ርዕሶች ናቸዉ።
የፕሬዝደንት ጆ ባይደን መስተዳድር የሚከተለዉ የዉጪ መርሕ ከመጀመሪያዉ ጀምሮ ብዙዎችን ያስከፋ፣በምርጫ ዘመቻዉ ወቅት ባይደን የገቡትን ቃል ያሳጠፈ ዓይነት ነዉ።ባይደን የሐገራቸዉን የቅርብ ወዳጆችና ተባባሪዎች አዉሮጶችን እንኳን በቅጡ ሳያማክሩ አፍቃኒስታን ዉስጥ የሰፈረዉን የአሜሪካ ጦር ማስወጣታቸዉ ብዙ ቀዉስ አስከትሏል።
የባይደን ዉሳኔ ለ20 ዓመታት ያክል ከአሜሪካኖች ጎን ቆመዉ የቀድሞዉን የአፍቃኒስታን አማፂ ቡድን ታሊባንን ሲወጉ የነበሩ የአፍቃኒስታን መንግስትን ባለስልጣናት፣ ወታደሮች፣ ሌሎች የፀጥታ አስከባሪዎችንና የአሜሪካ ሰላዮችና አስተርጓሚዎችን ለአደጋ ያጋለጠ ነዉ።የአዉሮጳና የሌሎች የኔቶ አባል ሐገራት ጦርም ድንገት በታዘዘዉ ሽሽት መሰል ዉሳኔ ብዙ ተመሰቃቅሏል።
ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯም ለባይደን መስተዳድር ከፍተኛ ፈተና ነዉ-የሆነዉ።ባይደን ገና ሥልጣን እንደያዙ የሩሲያዉን አቻቸዉን ቭላድሚር ፑቲንን «ገዳይ» በማለት መወንጀላቸዉ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከወራራዉ በፊትም ሆነ በኋላ ዩክሬን ላይ የደረሰዉን ዓይነት ጥፋት ለማስቀረት ወይም ሰላማዊ መፍትሔ ለመፈለግ በተለይ በሞስኮዎች ዘንድ ብቃት ያለዉ መሪ እንዳጣች አስቆጥሮባታል።
የሩሲያን ወረራ በድርድርና የሩሲያን ስጋት በሚያቃልል መልኩ ከማስወገድ ይልቅ በሩሲያ ላይ የተዥጎደጎደዉ ፕሮፓጋንዳ፣ ማዕቀብ፣ ለዩክሬን የሚጋዘዉ ጦር መሳሪያ፣ የስልለላና የጦር ኃይል ሥልጠና እስካሁን ዩክሬን ለዉድመት፣ አዉሮጳ ለጦርነት ሥጋት፣ አሜሪካን ለኪሳራ፣ ዓለምን ለክፍፍል ከመዳረግ ባለፍ የተከረዉ የለም።
ጋዛን በሚያወድመዉ ጦርነትም የባይደን መስተዳድር የያዘዉ አቋም ሰላማዊ አማራጭን የሚጋፋ፣የሰላማዊ ሰዎችን እልቂት፣መራብና መፈናቀልን የሚደግፍ መስሏል።እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ሕብረትና ተከታዮቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤሙ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ ባለፈዉ ጥቅምት ደብባዊ እስራኤልን ማሸበሩ በርግጥ ብዙዎችን ያስደነገጠ፣ ያስቆጣ፣ በብዙዎችም ዘንድ የተወገደ ክስተት ነዉ።
የእስራኤል ከጉርጓድ-ሕንፃ የሚሽለኮሎክ  ተዋጊ ቡድንን በማጥፋት ሰበብ ጋዛና ምዕራባዊ ዮርዳኖ ወንዝ ዳርቻ ላይ የከፈተችዉ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ያደረሰዉ እልቂት፣ጥፋትና የተዋለዉ ግፍ ብዙዎች እንደመሰከሩት በዓለም የቅርብ ዘመን ታሪካ ታይቶ አይታወቅም።የፕሬዝደንት ጆ ባይደን መeተዳድር ሰላማዊ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ  ለእስራኤል ሁለንተናዊ ድጋፍ መስጠቱ አሜሪካን ከጦርነቱ ዶሎ የአሜሪካ ወታደሮችን ሕይወት እስከማስገበር ደርሷል።

በጋዛዉ ጦርነት መዘዝ ዮርዳኖስ ዉስጥ የተገደሉ የአሜሪካ ወታደሮችን አስከሬን ባይደን ሲሸኙምስል MICHAEL MCCOY/REUTERS

ዩናይትድ ስቴትስ 34 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳ አለባት

 

የባይደን መስተዳድር የዉጪ መርሕ ክሽፈት ለወትሮዉ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩን የሚመርጡት የዉጪ ዝርያ ያላቸዉ አሜሪካዉያን ለፕሬዝደንት ባይደን ድምፃቸዉን እንደሚነፍጉ በግልፅ እየተናገሩ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ከሰሜን ኮሪያ፣ከቻይናና ከኢራን የገጠመችዉን ዉዝግብ ለመፍታትም የባይደን አስተዳደር ምንም ያደረገዉ የለም።
ዩናይትድ ስቴትስ እዚሕም እዚያም በተለኮሱ ግጭትና ጦርነቶች ዘላ መግቧቷ በምጣኔ ሐብቱ ላይ ያደረሰዉ ጉዳትም ቀላል አይደለም።የሪፐብሊካኑ ፓርቲ እጩ ለመሆን የሚፎካከሩት ኒኪ ሄሊ እንደሚሉት ዩናይትድ ስቴትስ ወጪዋን ለመሸፈን ከቻይና ሳይቀር ለመበደር ተገድዳለች።

«34 ትሪሊዮን ዶላር ዕዳ አለብን።ያለብንን ወለድ ለመክፈል ብቻ ገንዘብ እንበደራለን።ከነዚሕ ዕዳዎች የተወሰኑት የቻይና ናቸዉ።ይሕን ያደረገዉ ባይደን መሆኑን ልነግራችሁ እወዳለሁ።»
ዶናልድ ትራምፕ ግን ለሁሉም ተቀናቃኞቻቸዉ ምህርት የላቸዉም።ባይደንም፣ ሔሊም፣ ደጋፊዎቻቸዉንም ቻይናን የሚደግፉ፣ ጦርነትን የሚያራምዱ፣ ድንበርን የሚከፍቱ ይሏቸዋል።
«ከኒኪ ሔሊ በስተጀርባ ያሉት ሰዎች ምሕረት ይደረግ፣ ድንበር ይከፈት የሚሉ የቻይና ደጋፊዎች፣ ጦርነት አራማጆች ናቸዉ።ጦርነት አንፈልግም።ከጦርነት መዉጣት እንፈልጋለች።አይሲስን መትተነዋል።የባይደን ደጋፊዎች ናቸዉ።»
የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፊታችን ሐሙስ በሚሰጠዉ ብይን ትራምፕ በምርጫዉ መወዳደር ከቻሉ የባይደን ቀንደኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ በሰፊዉ ይታመናል።የሁለቱ አዛዉንቶች ፉክክር ደግሞ 2020ን ከዓራት ዓመት በኋላ እንደገና የሚያሳይ ነዉ የሚሆን።

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW