1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የካማላ ሐሪስ እና የዶናልድ ትራምፕ ሙግት

ታሪኩ ኃይሉ
ረቡዕ፣ መስከረም 1 2017

በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ የመጀመሪያውን የፊት ለፊት ክርክር አካሄዱ። ትናንት ምሽት በተካኼደው የጦፈ የምርጫ ክርክር፣እጩዎቹ በሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ በስደተኞች ጉዳይ፣ በምጣኔ ሃብትና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ተሟግተዋል።

USA Wahl2024| Philadelphia | TV-Duel - Trump gegen Harris
ምስል Alex Brandon/AP Photo/picture alliance

ካማላ ሐሪስ ወይስ ዶናልድ ትራምፕ?

This browser does not support the audio element.

ካማላ ሃሪስና ዶናልድ ትራምፕን ፊት ለፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ባገናኘው የትናንት ምሽቱ ፕሬዚዳንታዊ ክርክር፣ በእስራኤልና ሐማስ፣ ሩሲያ እና ዩክሬን መኻከል የሚካሄደውን ጦርነት እጩዎቹ  እንዴት ሊፈቱት እንደሚችሉ ክርክሩን ካሰናዳው ኤቢሲ ጋዜጠኞች ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር።
 

በውጭ የቀጠሉ ጦርነቶችን በተመለከተ የዕጩዎቹ አቋም

በእስራኤልና ሐማስ መኻከል ያለውን አለመግባባትን በተመለከተ፣ ዓለም ለእስራኤልና ፍልስጤም የሁለት ሃገር መፍትሄ ማበጀት አለበት የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ፣ እስራኤል ራሷን ለመከላከል ያላትም መብት እንደሚያከብሩ ገልጸዋል።

"እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት አላት፤ እኛም እናድርገዋለን። እንዴት የሚለው ግን ወሳኝ ነው። ምክንያቱም በጣም ብዙ ንፁሃን ፍልስጤማውያን መገደላቸው እውነት ነው።" እኔ ፕሬዚዳንት ብሆን በጋዛ የቀጠለው ጦርነት አይካሄድም ነበር ያሉት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፣ ካማላ ሃሪስ እስራኤልን ትጠላለች ሲሉ ተደምጠዋል። በውጭ ጉዳዮች ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የተሳሳቱና ደካማ ሲሉም ጠርተዋቸዋል።

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕምስል Win McNamee/UPI Photo via Newscom picture alliance

 

ካማላ ሃሪስ ይህን የዶናልድ ትራምፕን ክስ አስተባብለዋል

ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ቢመለሱ፣ ጦርነቶችን ወዲያው ሊያስቆሙ እንደሚችሉ ደጋግመው ቢናገሩም፣ እንዴት ለሚለው ቁልፍ ጥያቄ ግን የተጨበጠ ምላሽ ማቅረብ ተስኗቸዋል።  ከሩሲያ አኳያ በሚደረገው ጦርነት፣ ዩክሬን የበላይ እንድትሆን ይፈልጉ እንደሆን ሲጠይቁም፣ ጥያቄውን በቀጥታ ያልመለሱት ትራምፕ ይህን ጦርነት ማጠናቀቅ ለዩናይትድ የተሻለ ጥቅም ይመስለኛል ብለዋል።

"እኔ እንደማስበው፣ይህ ጦርነት በስምምነት እንዲጠናቀቅ ማድረጉ ለእኛ የተሻለ ጥቅም ነው።"

አሜሪካ አፍጋኒስታን

አሜሪካ ከአፍጋኒስታን የወጣችበት ውሳኔ ትክክለኛ እንደነበር የሞገቱት ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ፣ አሸባሪዎች ያሏቸው ታሊባኖችን ካምፕ ዴቪድ ድረስ ጋብዘው በመከራከራቸው ትራምፕን ወርፈዋቸዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው ከታሊባን ኀይሎች ጋር መደራደር ያስፈለገው፣ሰዎች በወቅቱ እየተገደሉ ስለነበር እንደሆነ በመግለጽ ራሳቸውን ተከላክለዋል።

በሌላ በኩል፣ሕገ ወጥ የስደተኞች አያያዝን አስመልክቶ በካማላ ሃሪስ ላይ የሰላ ሂስ በመሰንዘር፣ህጋዊ ያልሆኑ ስደተኞች፣  ከጥቁር እና ስፓኒክ አሜሪካዊያን ስራ እየወሰዱ በከተሞችም ወንጀል እንዲስፋፋ እያደረጉ ናቸው ብለዋል። "እንደዚህ ዓይነት ነገር በፍጹም ተደርጎ አያውቅም።ሃገራችን የተገነባችበትን መሠረት እያወደሙ ነው።በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገቡ እየተደረገ ነው።ከእኛ በስተቀር በመላው ዓለም ወንጀል እየቀነሰ ነው።"

ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ምስል Alex Brandon/AP Photo/picture alliance

የሁለትዮሽ የድንበር ደኅንነት ህግ

ድንበር ዘለል የወንጀል ድርጅቶችን በመክሰስ ያደረጉትን ጥረት የጠቀሱት ካማላ ሃሪስ በፊናቸው፣የሁለትዮሽ የድንበር ደኅንነት ህግ እንዳይኖር እንቅፋት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው በማለት ለችግሩ ተጠያቂ አድርገዋቸዋል።

"ያ ሕግ፣ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ድርጅቶችን፣የሰዎች የጦር መሣሪያና የተከለከሉ ዕጽ አዘዋዋሪዎችን ለመክሰስ ተጨማሪ አቅም ያስገኝልን ነበር።ግን ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?ዶናልድ ትራምፕ ስልክ ደውሎ በኮንግረስ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎችን ጠርተው፣ረቂቅ ሕጉን አስቁሙ አላቸው።ምክንያቱም እርሱ ችግሩን ከማስተካከል ይልቅ በችግሩ ላይ መረማመድን ይሻል።

ትራምፕ ከሌሎች ሃገሮች ጋር የንግድ ጦርነቶችን በመጋበዛቸው ምክንያት፣ በእርሳቸው የስልጣን ዘመን ከፍተኛ የንግድ ሚዛን ጉድለት መመዝገቡንም ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ገልጸዋል።

 

ታሪኩ ኃይሉ

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW