1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ክርክር በአትላንታ

ዓርብ፣ ሰኔ 21 2016

በአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ክርክር ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን ያሳዩት አቋም ፓርቲያቸውንና አሜሪካውያን መራጮችን ያስደነገጠና ስጋት ላይ የጣለ ሆኗል። አትላንታ በሚገኘው ሲኤንኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የፕሬዚንታዊዉ ክርክር፣ ባይደን ድምጻቸው ታፍኖ፣ ዐሳባቸውን ለመግለጽ ተቸግረው ሲደነቃቀፉ፣ትራምፕ ተረጋግተውና ራሳቸውን ተቆጣጥረው ቀርበዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ክርክር በአትላንታ 
የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ክርክር በአትላንታ ምስል Andrew Caballero-Reynolds/AFP/Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ክርክር በአትላንታ

This browser does not support the audio element.

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ክርክር በአትላንታ 


በአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ክርክር ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን ያሳዩት አቋም ፓርቲያቸውንና አሜሪካውያን መራጮችን ያስደነገጠና ስጋት ላይ የጣለ ሆኗል። አትላንታ በሚገኘው ሲኤንኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ትናንት ምሽት በተካሄደው የመጀመሪያው የፕሬዚንታዊ ክርክር፣ ባይደን ድምጻቸው ታፍኖ፣ ዐሳባቸውን ለመግለጽ ተቸግረው ሲደነቃቀፉ፣ትራምፕ ተረጋግተውና ራሳቸውን ተቆጣጥረው ቀርበዋል።  

በሥልጣን ላይ ያለና የቀድሞ ፕሬዚዳንት፣በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉት ሆኖ ተመዝግቧል፤የትናንት ምሽቱ ክርክር። ክርክሩ፣መራጮችን በሚያሳስቧቸው ዋና ዋና ጉዳዮች፣ማለትም  በኢኮኖሚ፣ የዋጋ ግሽበት፣ በህገወጥ የስደተኞች ጉዳይ፣ የጽንስ ማቋረጥ፣ እንዲሁም በውጭ ፖሊሲ በዩክሬንና በመካከለኛው ምስራቅ የቀጠሉ ጦርነቶችን የተመለከቱ አጀንዳዎች የተነሱበት ነበር።

የፕሬዚዳንቱ አስቸጋሪ ምሽት

ይሁንና፣በክርክሩ የብዙዎችን ትኩረት የያዘው፣የአዛውንቱ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን ያሳዩት ደካማ የተባለ አቀራረብ ነው። የባይደን የምርጫ ዘመቻ ተባባሪ ሊቀመንበር ሚች ላንድሪዩ፣ የትናንቱን ምሽት ለፕሬዚደንቱ "አስቸጋሪ ጊዜ" ብለውታል። በርግጥም ዕድሜ የተጫናቸው ጆሴፍ ባይደን፣በቀጥታ በቴሌቭዥን በተላለፈው ክርክር፣ቃላት ጠፍቶባቸው ሲደነቃቀፉና ዐሳባቸውን በትክክል ለመግለጽ ሲቸግሩ ታይተዋል። "የጤና አጠባበቅ ስርዓታችንን አጠናክረን መቀጠላችንን በማረጋገጥ፣እያንዳንዱን ብቸኝነትን ከኮቪድ ጋር ማድረግ ለቻልኹት ነገር፣ብቁ ማድረግ መቻልን በማረጋገጥ፣ይቅርታ፣....ማድረግ ያለብንን ነገር በማስተናገድ፣አስተውሉ፣...በመጨረሻ ሜዲኬርን አሸነፍን።" ጆሴፍ ባይደን፣ከቃላትና ዐሳብ መደነቃቀፍ በተጨማሪ በክርክሩ ወቅት ድምፃቸው እንደመታፍን ብሎ አስቸግሯቸው ነበር። የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸው አባላት በኃላ ላይ፣ፕሬዚዳንቱ ከጉንፋን ጋር እየታገሉ ክርክሩን ማድረጋቸዉን ገልጸዋል።

ተረጋግተው የቀረቡት ትራምፕ

በሌላ ወገን፣ትራምፕ ትናንት ምሽት ፍጹም በተረጋጋ ሁኔታ ራሳቸውን ተቆጣጥረው ቀርበዋል። በክርክሩ መኻልም፣ስለፕሬዚዳንቱ ዐሳባቸውን በሚገባ ለመግለጽ አለመቻል ሲናገሩ፣" በእርግጥም በእዚያ ዓረፍተ ነገር መጨረሻ ላይ የተናገረውን አላውቅም፣ እሱም የሚያውቀው አይመስለኝም።" ሲሉ ተሳልቀውባቸዋል። እርሳቸው ከባይደን የተሻለ አሜሪካን የማገልገል ችሎታ እንዳላቸውም፣ብቃታቸውን አስመልክቶ ለቀረብላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።

"ደኅና፤ሁለት ፈተናዎችን ወስጄያለኹ፣የግንዛቤ ፈተናዎች እኔ አካኼድኻቸው።እርሱ ምንም አልወሰደም።አንድ፣ አንድ ብቻ እውነተኛ ቀላል ፈተና ሲወስድ ማየት እፈልጋለሁ።" የዕጩዎቹ የእርስ በርስ ውንጀላዎች ትራምፕ ባይደንን በተለይ፣የምጣኔ ሃብትና የውጭ ፖሊሲ አፈፃፀማቸውን በመተቸት ተከራክረዋል። ባይደን በበኩላቸው።ትራምፕ እንደ ጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር በ 2020 የተካኼደውን ምርጫ ለመቀልበስ ያደረጉትን ሙከራ፣ እንዲሁም የወንጀል ክሳቸውን እያነሱ ለመሞገት ሞክረዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎች ክርክር በአትላንታ ምስል Yuri Gripas/abaca/picture alliance

"በዚህ መድረክ ላይ ወንጀለኛ ተብሎ የተፈረደበት ብቸኛ ሰው አሁን እያየኹት ነው።ከብልግና ወሲብ ተዋናይት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነትና የተለያዩ ነገሮችን ፈጽሟል።" ትራምፕ፣ባይደን ላቀረቡባቸው ለዚህ ክስ ሲመልሱ የሚከተለውን ብለዋል። "ቁጥር አንድ፣ከብልግና ወሲብ ፊልም ተዋናይት ጋር ወሲብ አልፈጸምኩም።ስለወንጀለኛ ስንናገር ግን ልጁ በከፍተኛ ሁኔታ ወንጀለኛ ነው።ጆ ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ የተፈረደበት ወንጀለኛ ሊሆን ይችላል።" በክርክሩ በትራምፕ በከፍተኛ  ሁኔታ ተበልጠው የታዩት ባይደን፣የትናንቱ አቋማቸው ፓርቲያቸውን እና ህዝቡን ያስደነገጠ እና ስጋት ላይ የጣለ ሆኗል።

ከዚህ አኳያ፣በቀጣይ ነሐሴ ወር በዕጩነት ያቀረባቸው የዲሞክራቲክ ፓርቲያው የሚያካሄደው ጉባኤ፣ በተለየ ሁኔታ የሚጠበቅ ሆኗል። የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሁለተኛ ዙር ክርክር፣በኢቤኤስ ቴሌቪዥን አስተናጋጅነት፣በመጪው በመስከረም ወር ላይ ይካኼዳል ተብሎ ይጠበቃል። 

ታሪኩ ሃይሉ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW